ራስ አባተ ቧ ያለው አነጣጣሪው መድፈኛ

ራስ አባተ ቧ ያለው

ከአድዋ በፊት የመቀሌዋ ስትራቴጅካዊ የውሀ ምንጭ መያዝ (ራስ አባተ ቧ ያለው እና ደጃዝማች ባልቻ አባ ሳፎ ጀብዱ)

አፄ ምኒልክ ጦራቸው መቀሌ ደርሶ ሰፈሩን ተከፋፍሎ ከያዘ በኋላ በጣልያን ምሽጉ ዙሪያ ራቅ እያለ ሰፈረ። ድንኳን በሚተከልበትና ጭነት በሚራገፍበት ጊዜ አንድ በቅሎ ፈርጥጦ ወደ ጣልያኖች ምሽግ ሮጠ። አንድ ሰው ሊመልሰው ሲሮጥ ባዩ ጊዜ ጣልያኖቹ የመድፍ ተኩስ ጀመሩ። ጣልያኖቹ አብዝተው መተኮሳቸውን ንጉሰ ነገስቱ በተመለከቱ ጊዜ ሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለውን እና በጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎን ሂዱ እናንተም ተኩሱባቸው ብለው አዘዙ እና የምሽቱ ጊዜ በመድፍ ተኩስ አለፈ። ወደ ማታ ንጉሱ እንደገና ሊቀ መኩስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻን ጠርተው “እነዚህን ጣልያኖች ከጉድጓዳቸው ሳላስወጣ የትም አልሄድም እናንተም የጠላት መድፍ ጥይት የማይደርስበትን ስፍራ መርጣችሁ ከዚያ ሆናችሁ ምሽጉን በመድፍ ምቱት” ብለው አዘዟቸው።

ሊቀ መኳስ አባተ ጦራቸውን ይዘው በምሽጉ በስተግራ የጣልያኖችን ቃፊር ጠባቂ አባርረው ምሽግ አበጅተው መድፍና መትረየሳቸውን እንደጠመዱ በጅሮንድ ባልቻም በስተቀኝ በኩል ሌሊቱን ምሽግ ሰርተው መድፍ እና መትረየሳቸውን ጠመዱ። ጣልያኖችም የእነሱን መጠጋት ባወቁ ጊዜ የመድፍ እና የጠመንጃ ተኩስ አበረከቱ። አነጣጥሮ በመተኮስ የተመሰገኑት ሊቀ መኳስ አባተም በሩቅ በሚያሳየው መነጸራቸው ጣልያኖች ታቦቱን አስወጥተው መድፍ በመትከል የመሸጉበትን ቤተክርስትያን ህንፃ በመመልከታቸው አስተካክለው ቢተኩሱ የመድፉ ጥይት በቤተክርስትያኑ መስኮት ገብቶ የጠላትን መድፍ እግር ሰባበረው። ጣልያኖችም ከተበላሸው መድፋቸው ጭስ እየጨሰ ባዩ ጊዜ በአፀፋው የመድፍ ጥይት ሊቀመኳስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻ ባሉበት ቦታ ላይ እንደ በረዶ አወረዱባቸው። ነገር ግን አንድም ሰው አልቆሰለም። ይህን ውጊያም አፄ ምኒልክ፣ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት እና ሌሎችም መኳንንቶች ከድንኳናቸው ወደላይ ካለው ከፍተኛ ስፍራ ላይ ሆነው በመነፀር ሲመለከቱ ነበር።

እቴጌ ጣይቱም የድንኳናቸውን መጋረጃ ገልጠው ሁኔታውን ሲመለከቱ ስለነበር በአቅራቢያቸው ወደ ነበሩት አዛዥ ዘአማኑኤል ፊታቸውን አዙረው “ሂድ እና ከሊቀ መኳሥ አባተ ጋር እየተመካከርክ የውሀውን ምንጭ ለመያዝ ትችል እንደሆነ ሞክር” በማለት አዘዟቸው። እሳቸውም ወዲያው በመሄድ እንደታዘዙት ከሊቀ መኳስ አባተ ጋር ቢነጋገሩ ሊቀ መኳሱ “የምንጩ ስፍራ ጥልቅና ወደ ጠላት ምሽግ የቀረበ ነው፤ በምንጩ እና በጠላት ምሽግ መካከል አንድ መቶ ሃምሳ ክንድ የሚሆን ርቀት አለ ቢሆንም ግን መተላለፊያውን በመድፍ ሳስጠብቅ እቆይና ከዚያ በሌሊት ወታደር ልኬ ምንጩን አስይዛለሁ” ብለው መለሱላቸው።

አዛዥ ዘአማኑኤልም የተባለውን ለእቴጌይቱ ሲነግሯቸው በጣም ደስ ስላላቸው ወዲያው ለአፄ ምኒልክ ሹክ አሏቸው። ንጉሱም “መልካም ነው” ብለው ስለ መለሱ እቴጌይቱ በምሽግ ውስጥ ያለው ጦር ያለ ውሀ መኖር እንደማይችል በመገንዘብ ለወታደሮቻቸው “. . . . . . . ጠላት ውሀ እንዳይቀዳ ምንጩን ጠብቁ እናንተም እስካሁን እምሽግ ገብተን እንዋጋለን የምትሉት የሜዳን ጦርነት እንደማትፈሩ ተስፋ አለኝ። በዚህ ጦርነት ተዋግተው ለተረፉት ደስ የሚያሰኝ የክብር ሽልማት እሰጣቸዋለሁ፡ ለሞቱትም ተዝካራቸውን አወጣለሁ፣ ልጆቻቸውንም አሳድጋለሁ እግዚአብሄር ከእናንተ ጋር ይሁን” ብለው ወደ እነ ሊቀ መኳስ አባተ አሰናበቷቸው።

እቴጌይቱ በዚህ ንግግር ካሰናበቷቸው በኋላ ወታደሮቹ የጦር መሳሪያቸውን በደንብ አዘጋጅተው እንደተቆጣ ነብር መስለው ከቀኑ በ11ኛው ሠዐት ወደ ምንጩ ተጓዙ። ጣልያኖቹ ምንጩ ወደ እነሱ ምሽግ በመቅረቡ ይያዛል ብለው አላሰቡም ነበር ነገር ግን ሁኔታው በገባቸው ጊዜ ሐሙስ ከማታው በሦስት ሠዐት ባለ ጠመንጃወቹ ጭምር መድፋቸውን እየጎተቱ ወጥተው ምንጩን በሚጠብቁት ላይ ድንገት ተኩስ ከፈቱባቸው፤ ጠባቂዎቹም ጠንክረው ከመዋጋታቸው የተነሳ ጣልያኖቹ ወደመጡበት መመለስ ግድ ሆነባቸው። በማግስቱ ሊቀ መኳስ አባተ ከበጅሮንድ ባልቻ ጋር ተስማምተው ጣልያኖቹ ያሉበትን እና መድፋቸውን የጠመዱበትን በመነፀር ተመልክተው በመድፍ መቱት። ጣልያኖቹ ዕቃቸውን መድፍ ወደማይደርስበት አዛወሩ። ሊቀ መኳስ አባተ እና በጅሮንድ ባልቻ በምሽግ ያሉትን በጥብቅ እየጠበቁ ወዲያና ወዲህ እየተዘዋወሩ በመድፍ እና በመትረየስ እየመቱ ጠላት ምሽጉን እስኪለቅ ድረስ ለአሥር ቀን ድረስ ሳይተኙ እና ከመሳሪያቸው ሳይለዩ ሰነበቱ።

በዚያን ሳምንት ሊቀ መኳስ አባተ እና በጅሮንድ ባልቻ የሰሩትን ሥራ ማንም ሊሠራው አይችልም ነበር። እቴጌ ጣይቱም በየቀኑ ከሌሊቱ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሠዐት ድረስ ባለው ጊዜ ውሀውን ለሚጠብቁ ወታደሮች መጠጥ የያዘ እንሥራ እና በመሶብ እንጀራ ሥጋ እየጨመሩ ይልኩ ነበረ። በሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለውን እና በበጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎ የሚመሩት የጦር ወታደሮችም እየበሉ እየጠጡ ሕይወታቸውን ለሀገራቸው እና ለንጉሳቸው ለመሰዋት ሲሉ አንድ ቀንም መሳሪያቸውን ትተው ሳይተኙ ጠላት ውሀ እንዳይወስድ
እየተከላከሉ ቆይተው በመጨረሻ ምሽጉን እስከማስለቀቅ ደረሱ።

ጥር ዘጠኝ ለአስር አጥቢያ ጣልያኖች ሌሊቱን በ7፡30፣ በ8፡30፣ በ10፡15 እና በ11፡00 በተከታታይ እየወጡ በመዋጋት ምንጩን ለማስለቀቅ ሞክረው በኛዎቹ ጥብቅ ተከላካይነት ሳይሳካላቸው ስለቀረ ሁሉም ወደ ምሽጋቸው በመሸሽ ተመልሰው ገቡ። ነገር ግን በነዚህ ጊዚያት በአንደኛው ሙከራ ሁለት ጊዜ መድፍ ተተኩሶ ነበር፤ የአንደኛው መድፍ ጥይት የጣልያኖቹን መድፍ አፍ ገብቶ ሰባበረው። ይህ መድፍ በማይጠረጠር ከሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለው የተተኮሰ መሆን አለበት ተባለ። በዚሁም ምክንያት
“አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው፥
የእኛን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው”
ተብሎ እንደተገጠመላቸው በገሃድ ተነግሯል።

ተክለፃዲቅ መኩሪያ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.