ስለ ኢ/ር ሀይሉ ሻዉልና ጀግንነትን የሚያስገብር ቀጣይነት ያለዉ ዲሞክራሲያዊ ተቁዋምን ስለ መገንባት
ስለ ኢንጅነር ሀይሉ ሻዉል ጉዳይ በዬ መሃሉ እየተነሳ በዉጭ ያለዉን የመኢአድ አባላት በጋራ ከመቆም ይልቅ የማፈራቀቂያ ነጥብ እንደሆነ ይገኛል:: ይሄን ጉዳይ ከስሜትና ከቡድናዊነት ወጥቶ በቀናነት ማዬት ነዉ የሚበጀዉ:: ስለሆነም ነገሩን ሰፋ አድርጌ ልዳስሠዉ ፈለግሁ::
እንደሚታወቀዉ ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል እና ማሙሸት አማረም በዋና ልዩነትና እርስ በእርስ መነቃቀፍ እና መለያዬት ብሎም የከረረ ጸብ ዉስጥ ነበሩ::
እነዚህን ሁለት ወገኖች እንዲሁም ሌሎችንም ሶስት ወገኖች በጥቅሉም 5 ወገኖች ለማስታረቅ በተደረገዉ ሂደት ዉስጥ ተሳትፌአለሁ:: ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል የት ጋ ለምን እንደተሳሳቱ ጠንቅቄ ገብቶኝም ነበር:: የሰሩትን ሀገራዊ አስተዋጾም እንደ ግንቦት ዳመና የምበታትን ወይም እንደ ደራሽ ዉሃ ጠራርጌ ገደል የምከት ሰዉም አልነበርኩም::
ሀይሉ ሻዉል ላይ ሚዛናዊ አቋም መያዝ አለበት በሚለዉ አቋሜ እነ ማሙሸት አማረ ይከፉ እንደነበረ አስታዉሳለሁ:: የእነሱም መከፋት አያስጨንቀኝም ነበር:: ምክንያቱም እነሱ በኢ/ር ሀይሉ ሻዉል የደረሰባቸዉ በደል ከፍተኛ ነበርና በጣም ይበሳጩ ነበር:: በተለይም ለድርጅቱ በጣም የደሙ ሰዎች ስለነበሩ የመኢአድ መፍረስ እንደ እግር እሳት ይፈጃቸዉ ነበር::
ከሁሉም በላይ አንድን ሰዉ ሀላፊ አድርገህ እንዲመራህ ስታስቀምጠዉ በተለይም የሚያስገብረዉ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሳትፈጥርለት ስህትት ለመስራት : አምባገነን ለመሆን ብሎም የህዝብ ስሜት ትቶ የራሱን ስሜት የመከተል እድሉ ሰፊ ነዉ:: በዚህ ላይ አንተም እኔም ብንሆን ተመሳሳይ ወጥመድ ዉስጥ መግባታችን አይቀርም:: ሰዎችን ከስህተተ የሚጠብቃቸዉ ሰዎች የሚገብሩለት ተቋም ከሌለ እንደ ኢትዮጵያ ሰዉ ሁሉ ተራራ ለተራራ እረ ጎራዉ ባይ ነዉ:: ሰዉ ነዋ:: ህሳቤ አለዉ:: የራሱ እይታ አለዉ:: የራሱ ስሜት አለዉ:: የራሱ ህመምና ድክመትም አለዉ:: ስለዚህ ሰዎች ስህተተ ላይ ማተኮሩ ቁም ነገር አይደለም:: በ እርቅ
ሂደቱ ላይ ዋና የተከተልኩት መርህ ይሄ ነበር:: እሰዎች ስህተት ላይ ማተኮር ሳይሆን ሰዉዬዉ ስህተቱን በስራ ሂደት ውስጥ ሰራዉ ወይስ ከሌ አላማ ሰራዉ የሚለዉ ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ ነዉ::
እኔ አንድ ደጋግሜ እናገር የነበረዉ ነገር ሀይሉ ሻዉል ተሳስተዉ ነበር:: በመሳሳታቸዉ መኢአድ እየፈረሰ ነዉ:: ግን የተሳሳቱት ወያኔ ስለሆኑ ወይም ሌላ የኢትዮጵያን ሰዉ የሚጎዳ ተልዕኮ ተሸክመዉ አይደለም እል ነበር:: ብዙዎች ቡድኖች በዚህ ሀሳቤ ይበሳጩ ነበር:: በተለይ የማሙሸት ቡድን በዚህ ሀሳቤ እንዴት ይበሳጭ እንደነበረ ሳይ ፈገግ ያደርገኝ ነበር::
የሆነ ሆኖ እኔ የማስበዉ ነገር ትክክል እንደነበረ ያረጋገጥሁበት አንድ ወሳኝ ነገር አለ:: ይሄዉም ከሁለት አመታት በላይ የፈጀዉ የእርቅ ሂደት ተሳክቶ የመኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 28-30/2007 ዓም የተጠራ ቀን ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል ስለ ማሙሸት አማረ እና ስለ አቶ አበባዉ መሃሪ ለ483 ተሰብሳቢዎች በድፍረትና በእዉነት ብሎም በሀቅ የተናገሩት ንግግር ሰዉዬዉ ተሳስተዉ እንጅ ሌላ የወያኔ አላማ ኖሯቸዉ እንዳልሆነ የሚያስመሰክር ነዉ:: በክፍፍሉ ወቅት ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል ማሙሸት አማረን ድርጅቱን ሊያፈርስ ነዉ ማስረጃ አለኝ እያሉ ብዙ ጊዜ ሲወነጅሉት ነበር::
ሆኖም ጥቅምት 28-30/2007 ዓም በተደረገዉ ስብሰባ ላይ ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል በግርማ ሞገስ እተሰብሳቢዉ ፊት ቆመዉ እንዲህ አሉ::”ይሄን ማሙሸት አማረ የተባለን ልጅ አትንኩት::
አንዳንዶቻችሁ አሁንም ይሄ ሰዉ ካልጠፋልን እያላችሁ ነዉ:: እኔም እንደ እናንተዉ ተሳስቼ ብዙ ነገር በድየዋለሁ:: እሱን ብቻ ሳይሆን መኢአድንም አዳክሜዉ ነበር:: ማሙሸት አማረ ቀጥ ያለ ታጋይ ነዉ:: ወደ ቀኝም ወደ ግራም አያዉቅም:: እዉነትን እዉነት ሀሰትን ሀሰት ብሎ የሚናገር ሰዉ ነዉ:: ጀግና ታጋይ ነዉ:: ስለሆነም መኢአድ እንዲጠነክር የምትፈልጉ ሰዎች ካላችሁ በሀሰት ወሬ አትወናበዱ:: እኔ ብዙ የተሳሳትሁበትን ነገር መርምሬ እና አጥንቼ የደረስኩበትን ዉሳኔ ነዉ የምነግራችሁ::”
የተበታተኑት አምስት ቡድኖች እንዳይግባቡ ; መኢአድ እንዳይሰባሰብ ከወያኔ ተልዕኮ ተሰጥቶት የነበረዉ አበባዉ ስብሰባዉ እንዲበተን ብዙ ተንኮል ሲሰራ ቢያስተዉሉ እና ቢያስቸግራቸዉ ደግሞ እንዲህ አሉ “አንተን ሰምቼ ብዙ ተሳስቻለሁ:: አንተ አላማህ ሌላ ነዉ”
እንግዴህ ይሄ የኢ/ር ሀይሉ ሻዉል ንግግር ዉስጥ ምን አለ:: መኢአድ ወደ አንድ መጥቶ የተከፋፈለዉ ቡድን በአንድ ቆሞ በክብር የሚቀጥለዉ ትዉልድ ትግሉን እንዲቀጥል የመፈለግ ጥብቅ ፍላጎት እንዳላቸዉ ያብራራል:: ይሄን ነገር ሰፋ አድርጌ የስብሰባ ሂደቱን በገለጽኩበት ጽሁፍ ለሚዲያ በትኘዉ ነበር:: እዚህ አሜሪካ ያለዉ ሚዲያ ግን ጭራዉን በሀይሉ ሻዉል ላይ አንዴ ቆልፏል እና የኔን ጽሁፍ ማዉጣት የፈለገ ወገን የለም:: ዘሀበሻ የሚባለዉ ዌብሳይት ግን ጽሁፉን አዉጥቶታል:: ከእዉነት ይልቅ ስማ በለዉ የሚወደዉ ወገን ግን አሁን ድረስ ሀይሉ ሻዉል ወያኔ ነዉ ሲል ይደመጣል::
ኢ/ር ሀይሉ ስህተታቸዉ ግዙ ቢሆንም ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ያፈሰሱት ላብና ያወጡት ጉልበትም እንዲዚያዉ እጅግ ግዙፍ ነበር:: ዛሬ አንዳንድ የትጥቅ ትግል ጀመርን የሚሉ ሰዎች ይሄን ሁሉ አለም አቀፍ እዉቅና የገነቡት በኢ/ር ሀይሉ መሰረት ላይ ቆመዉ ነዉ:: እርግጥ አሁን ሁሉም የታሪክ ሽሚያ ዉስጥ ነዉና ይሄ ነገረ ቢነሳ ቡራ ከረዩ ባዩ ይበዛል:: አበሻ ሲሸፍጥም ሸፍጠኛ ነዉ:: ሲጀግንም እንደዚያዉ ጀግና ነዉ::
ሰዉዬዉ ስንት አይነት ፕሮፖጋንዳ ይሰራጭባቸዋል:: ወያኔ ሁለት ሰይፍ ያለዉ ፕሮፖጋንዳ ትነፋለች:: በአንድ ወገን ኢ/ር ሀይሉ የመርሃቤቴ የሸዋ አማራ መሰረት ያለዉ ሰዉ ስለሆነ ይሄዉ ኦሮሞን ሊገዛና ሊያስገብር እንዲት ኢትዮጵያ እያለ መጣ እያለች ብዙ የቤት ስራ ሰራችባቸዉ:: ቅንጅት ሲፈርስ አሁን ትጥቅ ትግል ዉስጥ ገባን ያሉ ወገኖች ሁሉ ሳይቀር ይሄንኑ የወያኔን ፕሮፖጋንዳ ተጠቅመዉበታል:: እንዴዉም የነ ብርሃኑ ነጋ ወገኖች ቅንጅትን ያፈረሰዉ 95 % የሚሆነዉ በሰሜን አሜሪካ ያለዉ የቅንጅት ደጋፊ ሀይል አማራ ስለሆነ ነዉ እያሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የማይገባ ስም ይሰጡ ነበር::
ይሄም የአማራ ሀይል የሀይሉ ደጋፊ ነዉ እያሉ ከካናዳ እስከ ሀገር ቤት ፕሮፖጋንዳ ይነፉ ነበር:: በተለይም በወቅቱ ገናና የጋዜጣ ስርጭት የነበረዉ አዲስ ነገር የሚባለዉ ጋዜጣ በዲያስፖራ ያሉ አማሮች ናቸዉ ቅንጅትን ያፈረሱት እያለ ተገቢ ያልሆነ ስም ይለጥፍ ነበር:: ይሄ ሁሉ ቅስቀሳ ሀይሉ ሻዉልን በቂጡ ቁጭ ለማድረግ: የሀይሉ ሻዉልን ስህተተ ሰማዬ ሰማዬት ለማድረስ ብሎም እንደወያኔ ስትራቴጅ በራሱ ስነልቦና የሚቆም ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ዥዋዥዌ የሚጫወት ወገን እንዲፈጠር ለማድረግ ነበር::
እዉነቱን ለመናገር ግን የኢትዮጵያ ሰዉ ከማንም ጋር ሲሰለፍ ዘር እየቆጠረ አልነበረም:: ይሄንንም ሀሰት የሆነ ወሬ እኔ እራሴ በወቅቱ በጋዜጣ ላይ ተቃዉሜ መልስ ሰጥቼበታለሁ::
በሌላ ወገን ደግሞ ወያኔ ሌላ ወሬ ትረጫለች:: ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል በእናቱ ኦሮሞ ስለሆነ ጸረ አማራ ስነልቦና ስላለዉ ነዉ መአህድን ወደ መኢአድ የለወጠዉ:: ሰዉዬዉ የበታችነት ስሜት ስላለበት አማራ ይጠላል እያለች ወሬ ታስነፋበታለች:: በወዲህ በኩል ደግሞ ይሄ ሰዉ ከወያኔ ጋር ተሞዳሙዶ ኢንቨስትመንት ዉስጥ ገብቶ እየተባለ ብዙ ሀጢያት ይወራበታል:: ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል በዚህና በመሳሰለዉ ዉስብስብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ስንት አመት ታገሉ?ምን ያህል ዋጋ ከፈሉ? ቅንጅት እስኪፈጠር ያለዉን አስፈሪ እና ግርማ ሞገሳም ፓርቲ እስኪፈጥሩ ድረስ ምን ያህል ጊዜ ፈጀባቸዉ? ምን ያህል ገንዘብ አፈሰሱ?
ከቤተሰባቸዉ ጋር ስንት ጊዜ ተጋጩ? ወያኔ ስንቴ አስፈራራቻቸዉ? ስንቴ ልትገላቸዉ ፈለገች? ይሄን ሁሉ ማን ይቁጠርላቸዉ? ማንም::
ደብቡ ኢትዮጵያ ላይ መኢአድ 300 ህሽ አባላትን ማፍራት የቻለዉ በሀይሉ ትጋት ነበር:: ኢትዮጵያዊነት የአማራ ጉዳይ ነዉ ሲባል በመላ ሀገሪቱ 1.2 ሚሊዮን አባላት አደራጅቶ እንደ ሰደድ የ97 ዓም ምርጫ ምድር አንቀጥቅጥ እንዲሆን ያደረገዉ ሀይሉ የጣለዉ መሰረት ነበር:: በዚህ ጥብቅ መሰረት ላይ እንደ ብርሃኑ ነጋ ዓይነት ተናግሮ አሳማኝ ጎበዝ ተናጋሪ ብሎም ብዙ ያነበበ ሰዉ : እንደ ልደቱ ለግላጋ ደፋር ወጣት ካባና ሱሪ ለብሰዉ ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ሲቀርቡ የነበራቸዉ ሞገስ ልብ ያሸፍት ነበር:: የሀይሉ ግትርነት: የብርሃኑ ብልጠት: የልደቱ ወኔ : የፕሮፌሰር መስፍን ምሁራዊነት ይሄ ሁሉ ታሪካዊ ቅንጅት
ነበር::
እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸዉ በራሳቸዉ ጀግና ነበሩ:: ብርሃኑን የማይወዱ ሰዎች ብርሃኑን ጀግና ለምን ትላለህ ሊሉኝ ይችላሉ:: ሀይሉን የማይወዱኝ ሰዎች ሀይሉን እንዴት ጀግና ትላለህ ሊሉኝ ይችላሉ:: እዉነታዉ ግን እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸዉ በራሳቸዉ መንገድ ጀግና ነበሩ:: እናም መሰረታዊ ስህተትም የተፈጠረዉ ጀግናን ጀግና ሊያስገብረዉ ሲሞክር እኔ እገን እኔ እገን ሲመጣ ነዉ:: ይሄን ነገር ማንኛቸዉም እዉነቱን መናገር አይፈልጉም:: ወይም ደግሞ ነገሩ በጥልቀት ላይገለጽላቸዉ ይቻላል:: ዲሞክራሲያዊ ተቋም እነዚህን ጀግና ግለሰቦች አላስገበራቸዉም ነበርና እነሱም ለዲሞክራሲያዊ ተቋም አልገበሩም
ነበርና ሰዎቹ ብትንትን ሲሉ ሁሉም ነገር ተበታተነ:: ከዚያስ ምን አለ? ምንም! ማን ተወቃሽ አለ? ማንም! ሀይሉ ሻዉል ለስንት ጀግና ስህተተ ብቻዉን ተጠያቂ ይሆን ዘንድ የብልጠት ፕሮፖጋንዳ ተቀምሮ እጀርባዉ ላይ ተለጠፈለት::
በኢትዮጵያዊ ስነልቦና ከማዝንባቸዉ ነገሮች ዉስጥ ይሄን ሁሉ የሀይሉን ዉለታ አፈር አብልተዉ እነብርሃኑ ነጋ ከእስር ተፈትተዉ ወደ አሜሪካ ሲመጡ ሀይሉን የሚያህል ገናና ጀግና “ይሄ ብስብስ ! እርሱ ብስብስ ነዉ:: እኔን ለመናገር የስነ ልቦና ብቃት የለዉም ” ሲል ብርሃኑ ነጋ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ስራ የሰራበትን ሁኔታ ነዉ:: ወይም ደሞ አሁን ያንን ቂም ይዘዉ አሁን ብርሃኑ ነጋ የሚሰራዉን ስራ ሁሉ በካልቾ ጠልፈዉ ለመጣል የሚሄዱ ሰዎችን ሳስተዉል ነዉ:: ሀገር በሚዛናዊነት ብቻ ይድናል:: ሚዛናዊነት የሚጠብቀዉ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ተቋም ሲፈጠር ብቻ ነዉ::
አንዳንድ ሰዎች ብር ተበላ እነ ሀይሉ ሻዉል አጠፉት ይላሉ:: ግን ብሩን ማን በላዉ ? ማን መጥቶ በቅንጅት ስም ወሰደዉ ? ሁሉንም ገንዘብ ሰብስቦ የወሰደዉ ሀይሉ ሻዉል ነዉ? ይሄ እዳ የሀይሉ ሻዉል እዳ ብቻ ነዉ? ብርቱካን ሚደቅሳስ ስንት ሚሊዮን ብር ሰብስባ ወደ ሀገር ቤት ተመለሰች? ብርሃኑ ነጋስ ከተሰበሰበዉ ዉስጥ ምን ያህሉን ወሰደ? ሌሎች የቅጅት አመራሮችስ? ይሄ ሁሉ ነገር ምስቅልቅል የወጣ መልስ ከተመሰቃቀለ አቅጣጫ እንደሚመጣለት በደንብ አዉቃለሁ::
አንዳንዱም ሊዘፍንብኝ ይነሳ ይሆናል:: ሀይሉን ለመከላከል ነዉ : ምናምን ሊለኝ ይችል ይሆናል:: ሀይሉን የመከላከል ቅንጣት ፍላጎት የለኝም:: ለህዝቤ የሚያስተምረዉን እዉነት ብቻ የመተንተን የህሊና እዳ አለብኝ::
ጀግና ኢትዮጵዊ አባቶቻችን የሰሩት ሀገር እንዴት ዲንቢጥ እንደገነባዉ የወፍ ቤት ፍርስርሱ በወያኔ ተንኮል ሊወጣ ቻለ? መልሱ ቀላል ነዉ:: አባቶቻችን ጀግና ነበሩ:: ግን የሚያስገብራቸዉ ጀግና ተቋምን ሳይመሰርቱ በማለፋቸዉ ነዉ:: ዛሬ እኛ እንደ ዲቃላ ሜዳ ላይ ቆመን እንደ በራሪ ወፍ ጭዉ ጭዉ እንላለን:: አባቶቻችን የከፈሉት የጀግንነት መስዋዕትነት ግን አሜሪካዊ አባቶች ወይም እንግሊዛዊ አባቶች ከከፈሉት መስዋዕትነት ይበልጥ ቢሆን እንጅ ያነሰ አልነበረም:: እንግሊዞች ከማግና ካርታ (11ኛዉ ክፍለ ዘመን) ጀምሮ ጀግኖቻቸዉን የሚያስገብር : ጀግኖቹም የሚገብሩለት ዲሞክራሲያዊ ተቋም እየገነቡ ሲመጡ
የኛ አባቶች ያን ተቋም መገንባት ሳይችሉ ስለቀሩ ይሄዉ እኛ እንደ ጨረባ ድንቢጥ ስለ ዲሞክራሲ ጭዉ ጭዉ እንላለን:: ማንም አይሰማንም:: ማንም አያደምጠንም:: ማንም ከሰዉ አይቆጥረንም:: የከሰሩ ህዝቦች : ብሎም ፈራሽ ሀገር (failed state) ያላቸዉ ሰዎች ተብለናል::
እኛም ዛሬ ዲሞክራሲአዊ ተቋም መገንባት ባለመቻላችን ስለ ግለሰብ ጀግኖች እናወራለን:: ግማሻችን ሀይሉን እንወቅሳለን:: ግማሻችን ብርሃኑን እንነቅፋለን:: ግማሻችን ሀይሉን እናሞግሳለን:: ብርሃኑን እናወድሳለን:: ግን ይሄ ሁሉ አካሄድ ለሀገሪቱ ድህነትን ይዞ ከቶም አይመጣም:: መሰራት ያለበትን ስራ አልሰራንም:: ሀይሉን ከመዉቀሳችን ወይም ብርሃኑን ከማሳነስችን በፊት መሰረታዊ ጥያቄ እንመልስ:: እኛ የችግሩን ቁልፍ የሚፈታ ስራ ላይ ምን አበረከትን? አሁን ነገ ኤርትራ የሚባለዉ ሀገር ኤርትራ በመሸጉ ጀግኖቻችን ላይ ሸፍጥ ቢሰራባቸዉ ምን ሊፈጠር ይችላል? አሁን ይሄን ጥይያቄ የሚያንሰላስል
ዲሞክራሲያዊ ተቋም የግድ ያስፈልጋል:: እና ይሄን ማን ይፍጠረዉ?
እናም ዋናዉ ነጥብ ምንድ ነዉ? ቅንጅት ኢንተርናሽናል የሚል ተቋም ተቋቁሞ የሚባለዉ ተቋም ተቋቁም እንዳልነበረ ያሳያል:: ሁሉንም ጀግኖች ማስገበር አልቻለም ነበርና:: አሁን ከቅንጅት ኢንተርናሽናል ምን እንማራለን ከተባለ ከላይ የግለሰቦችን ጀግንነት የሚያስገብር ቀጣይነት ያለዉ ዲሞክራሲያዊ ተቋም በሚለዉ ጽሁፍ ዉስጥ መልሱ አለ::
እናም አሁን ሀይሉ ሻዉልን ለመዉቀስ ጊዜዉ አይደልም ወዳጄ:: የማመስገኛም ጊዜዉ አይደልም:: ከተሰራዉ ያልተሰራዉ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብዙ ነዉና:: ትናንት ታሪክ ነዉ:: ከታሪኩ ዉስጥ ተፈልፍሎ የሚወጣዉን አስተማሪ ነገር ፈልፍሎ ማዉጣት ነዉ ቁም ነገሩ:: ያቁም ነገር አንድ ነዉ:: እሱም የግለሰቦችን ጀግንነት የሚያስገብር ቀጣይነት ያለዉ ዲሞክራሲያዊ ተቋም መመስረት አልተቻለም ነበር::
ሸንቁት አየለ