የአርቲስት እጅግአየሁ ሽባባዉ (ጅጅ) ግጥሞች
ሸጋው ያገሬ ልጅ
ሸጋው ያ’ገሬ ልጅ ሚዛኑ ሚዛኑ፣
እስኪ ሰዎች ሁሉ ባንተ ይመዘኑ።
ከበሮውን ምቱት በገናም ይደርደር፣
ምንም አይለየኝም ከአገሬ ልጅ ፍቅር፤
አንተ የአገሬ ሰው እኔ እወድሀለሁ፣
ከልቤ ገብተሀል እምልልሀለሁ።
ደማምዬ፣ ደማምዬ፣
ደማምዬ፣ ና ሸግዬ!
ልቤ ፈሶልሀል እንደ ወንዝ ጅረት፣
ብትሻኝ ና ጠጣ፣ ከፍቅሬ ወተት፣
ሸጋው ያገሬ ሰው ሰውነት የእኔ ዓለም፣
ሰው ባንተ ይለካ፣ ካንተ በላይ የለም።
ሸጋው ያ’ገሬ ልጅ ሚዛኑ ሚዛኑ፣
እስኪ ሰዎች ሁሉ ባንተ ይመዘኑ።
ተው አንተ ሰው
አሞራ ወድጄ፣ አሞራ ሆኛለሁ
ነብርንም ወድጄ፣ ነብር ሆኜ አውቃለሁ
ድብ አንበሳ ነበርኩ ከጥንትም ተዋድጄ፣
ዛሬ ግን አቃተኝ እርሜን ሰው ወድጄ፣
ሰው መሆን አልቻልኩም ብርቄን ሰው ወድጄ
ተው አንተ ሰው ልቤን አደከምከው፣
ተው አንተ ሰው ልቤን አደከምከው።
ዘንድሮ ይህ መውደድ የጣለብኝ እዳ
ሰው እንዴት ይወዳል ሰውን ሳይረዳ?
ፍቅር አጠናገረኝ እንደ ገደል ምች…
መድሀኒት ፈልጉ መጣሁኝ ሰዎች
ተው አንተ ሰው….
አሞራ ወድጄ፣ አሞራ ሆኛለሁ
ነብርንም ወድጄ፣ ነብር ሆኜ አውቃለሁ,
ድብ አንበሳ ነበርኩ ከጥንትም ተዋድጄ፣
ዛሬ ግን አቃተኝ እርሜን ሰው ወድጄ፣
ሰው መሆን አልቻልኩም ብርቄን ሰው ወድጄ
ተው አንተ ሰው ልቤን አደከምከው፣
ተው አንተ ሰው ልቤን አደከምከው።
እኔን ግራ ገብቶኝ፣ ግራ አጋባው ሰውን
ፍታኝ ከዚማ ስር፣ ፍታኝ አንተ ሰው
እንዲህ ከሆነማ የፍቅር ነገር፣
ከሀውልት ከድንጋይ ከእንጨት ልፈጠር።
ተው አንተ ሰው ተው አንተ ሰው…
ንገረኝ አንተ ልጅ ዝም አትበለኝ ምነው?
ጉንፋን እኮ አይደለም የያዘኝ ፍቅር ነው፣
ቀልቤ ተበታትኖ ማሰብ ተስኖኛል __
ሰው አርገኝ አንተ ሰው ሰው መሆን አቅቶኛል….
ተው አንተ ሰው… ተው፣ ተው፣ ተው….አንተ ሰው…
አድዋ
የሰው ልጅ ክቡር ሰው መሆን ክቡር፣
ሰው ሙቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር፣
በደግነት በፍቅር በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ፣
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ካጥንት፣
ስንት ወገን ወደቀ በነጻነት ምድር፣
ትናገር አድዋ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር አድዋ ትናገር ሀገሬ፣
እንዴት እንቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፣
በኩራት በክብር በደስታ በፍቅር፣
በድል እኖራለው ይኸው በቀን በቀን፣
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን፣
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት፣
መቸ ተነሱና የወዳደቁት፣
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነጻነት ላበቁኝ ወገኖች፣
የትቁር ድል አምባ አድዋ አፍሪካ እምየ ኢትዮጵያ፣
ተናገሪ ተናገሪ የድል ታሪክሽን አውሪ::
ዓባይ
ከዓባይ ወዲህ ማዶ ያለችው አገር፣
ፍልቅልቅ ፍልቅልቅ አንቺ ውብ ከተማ፣
ዓባይ ባልሽ ነው ወይ ሰማሁኝ ሲታማ፣
ዓባይን የሚያህል ንጉስ አግብተሽ፣
ምነው መጠማትሽ ምነው መራብሽ?
(ያልታተመ ስራዋ)
**********
“ጎጃም ያረሰውን ፣ ለጎንደር ካልሸጠ
ጎንደር ያረሰውን ለጎጃም ካልሸጠ
የሸዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ
የሐረር ነጋዴ ወላጋ ካልሸጠ
ፍቅር ወዴት ወዴት ፣ ወዴት ዘመም ዘመም
ሀገርም አለችኝ ሀገር የኔ ህመም
ስሩ እንዳይበጠስ መቋጠሪያው ደሙ
አረንጏዴ ቢጫ ቀይ ነው ቀለሙ!
****************
ሸማ ነጠላውን ለብሰው
አይበርዳቸው አይሞቃቸው
ሐገሩ ወይናደጋ ነው
አቤት ደም ግባት -ቁንጅና
አፈጣጠር ውብ እናት
ሐገሬ እምዬ ኢትዮጵያ
ቀጭን ፈታይ እመቤት
የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና።
ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከነገት
ግርማ ሞገስ
የአገር ፀጋ የአገር ልብስ
ግርማ ሞገስ።
ዓባይ…
የበረሐው ሲሳይ…
************
ካህን
በቃላት ድርድር
በሙዚቃ ቃና
ስሜት ስታብራራ
ነብሴን ስታጣራ
አየሁኝ ጥበብ
ሰማሁኝ እውቀት
ልናገር ልመስክር የዚህን ሰው ቅንነት
ቀልጦ አንደሚበራ ሻማ
መብራት በሌለው ከተማ
እየቀለጠ በራልኝ
አየሞተ አኖረኝ
እሱስ ባለዕዳው ነኝ
ህይወት እንዳይሰለቸኝ
ሲጨነቅ ሲጠበብልኝ
አይተኛም ቀን ከሌት
ለደስታዬ ሲዋትት
ካህኔ የነብሴ አገልጋይ
እንቅልፍ አትተኛም ወይ
የነብሴ አገልጋይ
እንቅልፍ አትተኛም ወይ
ካህኔ የነብሴ አገልጋይ
እንቅልፍ አትተኛም ወይ..
Leave a Reply
You must be logged in to post a comment.