ቅርጫ በገጣሚ ለማ
ወያኔ ጋጠ ወጥ አጋድሞ ፍሪዳ ፣
የማይታረድን አርዶ መሀል ሜዳ፣
ቆራርጦ በላልቶ ሲቀረው ሹልዳ፣
ጎረቤት ጠራርቶ ዙሪያ በመደዳ፣
ማከፋፈሉ ነው ለዘመድ ለባዳ ፣
ለወንበር ላበቁት እየከፈለ እዳ፣
ማብላት ማጠጣቱ ለባእድ ለእንግዳ፣
ሰንጋ ተጣለለት ሊወስድ ወደ ጓዳ፣
ገና ጉድ አለብን ወያኔ ካልጸዳ ፡፡(2)
ቀለጣፋው ወያኔ ያዘጋጀው ቅርጫ፣
ከአያሌ ዘመናት እጅግ አለው ብልጫ፣
በነጻ ነው አሉ ተሰጥቶአል መግለጫ፣
ገንዘብ ልክፈል የሚል አለበት መቀጫ፣
አልወስድም እንኳን ቢል ያለበት ግልምጫ፣
ከዚያም ከተመቸው ያርፍበታል ጡጫ፣
ድርጅቱን ቢቃወም ሕዝባችን ቢነጫጫ፣
ተወቃቅጦ ያልቃል በጠባብ ሙቀጫ፣
እንዳው ዝም ሆኖአል ሥለሌለው ምርጫ፣
እምየ ኢትዮጵያ እጣሽ ሆኖአል ቅርጫ፣
የዘረፋ ወንበር የጠባብ መፈንጫ ፡፡
እንደዚህ ነው አሉኝ ስሰማ ሲወራ፣
መተክል አሶሳ መተማ ሁመራ፣
ጭብጨባ ይዘዋል ሱዳን ሣትጠራ፣
ባድሜና ቡሬ ሰግደዋል ኤርትራ፣
በከፊል አፋርም ተሰልፏል ጎራ፣
ለጅቡቲ ሊሰጥ የታጨው ሙሽራ፣
ከፊሉ ነው አሉ የሱማሌ ተራ፣
እምዬ ኢትዮጵያ ያየሽው መከራ፣
ከመቸውም ከፋ ቅርጫ በስንዘራ፡፡
ሠፋ ያለ ቦታ ኡጋዴን ጨምሮ፣
ሶማሌ ደርሶታል ሊያደርገው ነው ጓሮ፣
የወያኔ ለቅሶ ተሰምቷል እሮሮ ፣
እመዬ ኢትዮጵያ ምን ይሻል ዘንድሮ ?
መሬትሽ አለቀ ዙሪያው ተሸርሽሮ ፣
ቅርጫ እኮ አደረገሽ ወያኔ ተማክሮ ፡፡
ቦረና ሞያሌ የአካባቢው መንደር ፣
ወያኔ ወስኗል ለኬንያ ድንበር ፣
ልግስና እንድህ ነው መቸም የለው ወደር ፣
ቆራርጦ የሚሰጥ እያናጨ ሀገር ፣
ቅርጫ ሆነ እድልሽ የኢትዮጵያ ነገር ፣
ለማን አቤት ልበል ለማንስ ልናገር ?
እነግደህ ይኸው ነው ወያኔ እልል አለ ፣
ጉዞው ካለተገታ ካልተከለከለ ፣
ቅርጫው ይቀጥላል አናቱ ለይ ካለ ፣
ኢትዮጵያን አስቧት ወሠን ተከለለ ፣
የጼ ምኒልኩ ችካል ተነቀለ ፣
ወያኔ አፈረሳት ሳይጠየቅ ማለ ፣
ይኸን ውሰዱልኝ አልፈልግም አለ ፣
ሕዝባችንም ጨንቆት ከጥላት ሥር ዋለ ፣
ቅርጫው ሀገር ጥሎ ኢትዮጵያነ ገደለ ፣
ምን ትመክራላችሁ ከቶ ምን ተሻለ ፣
ሌላም ጉድ ይመጣል ካልተመነገለ !
በአጭር ከአልተቀጨ ካልተፈነገለ !
ሸገርም ያአንዱ ነው እጣ ከተጣለ ፡:
Leave a Reply
You must be logged in to post a comment.