አማራ

አማራ

አማራ የሚባለው ጎሳ ስያሜው እንዴት እንደመጣና ትርጉሙም ምን እንደሆነ ብዙ ሊቃውንቶች ይቸገሩበታል። አንዳንዶቹ ለስሙ ትርጉም በመስጠት የልብወለድ ታሪክ ለመናገር ይሞክራሉ። አምሐራ ምህረት የጠየቀ እንደማለትም ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በጥንት ዘመን አባይ ወንዝ ዳር ይመለክበት ከነበረ የጣኦት ስም የተገኘ ቃል ነው ይላሉ። ትግሬዎች አማሮችን ወደ ደቡብ የሄዱ ትግሬዎች ናቸው እስከማለትም ደርሰዋል። ሌሎች ደግሞ ሰሐራ ውሃ የሌለበት በረሀ ሲሆን አምሐራ ደግሞ ውሃ ያለበት ለምለም ቦታ ማለት ነው ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የአገውን ታሪክ የሚመረምሩ የአማራ ጎሳ ምንጩ አገው ነው ይላሉ። በወሎ አማራ ሳይንት የሚባል የአገር ስም እንዳለ ይታወቃል። እንዲያውም ከግራኝ አህመድ ጦርነት አስቀድሞ አሁን ወሎ የሚባለው ግዛት አማራ ይባል ነበር። ሕዝቡም ሃይማኖቱ ክርስትያን ስለነበር ሃይማኖቱን ሳይለውጥ የቀረውን ሁሉ አማራ ማለት ተጀመረ። ይህ አማራ ተብሎ የሚታወቀው ጎሳ ራሱን አማራ ሲል ሌሎች አምሐራ ለምን እንደሚሉት አይታወቅም። በተጨማሪም አማራን የጎሳ ስም አይደለም የሚሉት ከሌሎች ጎሳዎች መስፈርት የአማራ በምን ተለይቶ እንደሆነ አይገልፁም። ይሁንና አማራ በሚል ስያሜ የሚታወቅ አንድ ግዙፍ ጎሳ በኢትዩጵያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ ይታወቃል። በኢትዩጵያ ክልል ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚገኝ መሆኑ ለፍፁም ኢትዩጵያዊነት ሥነ ልቡናው አስተዋፅኦ አድርጎለታል።

ይሁንና አማርኛ ቁዋንቁዋ ከዩዲት ዘመነ መንግስት ጀምሮ የህዝብ መገናኛ ቁዋንቁዋ እንደነበረ ይታወቃል። ምንም እንኩዋን ግዕዝ የስነ ፅሁፍ ቁዋንቁዋ በመሆኑ አማርኛ ተጨቁኖ ቢቆይም ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ በይፋ የፅሁፍ ቁዋንቁዋ ለመሆን በቅቶአል። በሸዋ፣ በወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃም ያለው ሕዝብ በብዛት አማራ ይባላል። ከኦሮሞ መስፋፋት በፊት ወለጋ፣ ኢልባቡር፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ሊሙ፣ ሸዋ ውስጥና ወደ ሐረርጌ በሚወስደው ደጋ አገር ላይ ያለው ሕዝብ በብዛት አማራ እንደነበረ ይነገራል። በተለይ በሸዋ ሜዳ ሜዳው ላይ ነዋሪ የነበረው አማራ ሸሽቶ በየሸንተረሩ በመደበቅ ዘሩን ማትረፉን መልከአ ምድሩን በመመልከት ለመረዳት ይቻላል። ገደላ ገደሉ አማራ ሜዳ ሜዳው የኦሮሞ አገር የኮነው ኦሮሞው በፈረስ ሆኖ በጦር እየወጋ አማራውን አባሮት ነው ተብሎም ይነገራል። ከግዜ ብዛት አማራው ኃይል ሲያገኝ ተመልሶ ከገደላ ገደሉ ወጥቶ በጦር ድል አድርጎ በመውጣቱ በአሁኑ ወቅት በጋብቻ ጭምር ተሳስሮ ከኦሮሞ ጋር የኦሮሞ አገር በተባለው ሁሉ በብዛት አብሮ በመኖር ላይ ይገኛል። የአማራ ጎሳ ለብቻ ጎሳ የመለየት ጠባይ ስለሌለው በተለይ ከኦሮሞ ጎሳ ጋር በብዛት በጋብቻ ተሳስሮአል።

የሸዋ፣ የወሎ፣ የጎንደርና የጎጃም አስተዳደር ብዙውን ግዜ በማዕከላዊው መንግስት ስር ሆኖ በየክፍለ ግዛቱ የተለያዩ ባላባቶች አሉዋቸው። ከፊታውራሪና ደጃዝማች እስከ ራስና ንጉስ ድረስ እንደ ጀብዱዋቸውና ውልደታቸው የማዕከላዊው ንጉሠ ነገሥት የተለያየ ማዕረግ ይሰጣቸዋል። በተረፈ የማዕከላዊው መንግስት ባለስልጣኖች እየሆኑ በሹመት በንጉሰ ነገሥቱ ግዛት ይዘዋወራሉ። በጎንደር ቤተ መንግስት በቁረኞችና በየጁ መካንንት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የንጉሠ ነገሥቱ መንግስት በደከመበትና እንደራሴው ስልጣኑን ካዘዘበት ግዜ ጀምሮ እንደራሴነቱን ይዘው የቆዩት ውልደታቸው ከአማራም ከኦሮሞም የነበረው የየጁ ባላባቶች ነበሩ። ከሌሎቹ ፈንጠር ብሎ ጎጃምና ዳሞት የተለዩ ጠንካራ ባላባቶች ነበራቸው። የጎንደሩ ንጉሠ ነገሥት መንግስት በእንደራሴዎች ስር በወደቀበት ወቅት በሸዋ ያለው የቀዳማዊ ምኒልክ ተወላጆች ኃይለኛ ባላባቶች ሆነው ስለነበረ የጎንደሩን መንግስት ለመተካት እቅድ ነበራቸው። በተለይ ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ዝግጅት ጀምረው በድንገት ስለሞቱ ልጃቸው ኃይለ መለኮት በሸዋ ንጉሥነት ቆዩ።

የ 20 ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዩጵያ
አንደኛ መፅሐፍ
በጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ ቤተ ገፅ 31-33

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.