አበበ ቢቂላ

ትናንት በችኮላ ለተፈጠረው ስህተት “ይቅርታ” እየጠየቅሁኝ የአበበ ቢቂላ ታሪክ ቢረዝምም እነሆ በረከት።”ይቅርታችሁ አይለየኝ”!!!!!

ተዝናናቹ አንድ አንድ ነገሮችን ማወቅ ከፈለጋቹ www.facebook.com/kefetcom LIKE በማድረግ ብዙ ነገሮችን መማር ትችላላቹ፡፡ መልካም ግዜ ይሁንላችሁ

አበበ ቢቂላ
አበበ ቢቂላ (ቁጥር 11)
ሻምበል አበበ ቢቂላ ( ነሐሴ ፴ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም –
ጥቅምት ፲፭ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም) ለ ኢትዮጵያ ና ጥቁር
አፍሪቃ የመጀመሪያውን የ ኦሊምፒክ ማራቶን ወርቅን
ከዓለም ክብረ ወሰን ጋር ያስገኘ ኢትዮጵያዊ ከመሆኑም
ሌላ በ ሮማ የኦሊምፒክ ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ
በማሸነፉ፤ በተከታዩ የ ቶክዮ ኦሊምፒክ የራሱን የዓለም ክብረ
ወሰን በማሻሻል ለሁለተኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳይ በመሸለሙ
ታሪካዊና ዝነኛ ለመሆን አብቅቶታል።
ታሪኩ
አበበ ቢቂላ ነሐሴ ፴ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም [1] በ ሸዋ ጠቅላይ
ግዛት በ ደብረ ብርሃን አውራጃ፣ ደነባ ልዩ ስሟ ጃቶ
ከምትባል ሥፍራ ላይ ከአባቱ አቶ ቢቂላ ደምሴና ከእናቱ
ከወይዘሮ ውድነሽ መንበሩ ተወለደ። ወጣቱ አበበ
እንደአካባቢው ልምድ በእረኝነትና በትምሕርት ተሰማርቶ
በአሥራ ሁለት ዓመቱ የቄስ ትምሕርቱን አጠናቀቀ። በዚህ
በጨቅላ ዕድሜው ስመ ጥሩ የገና ተጫዋች እንደነበር
ይነገርለታል። በ ፲፱፻፵፬ ዓ/ም አዲስ አበባ ሄዶ በክብር
ዘበኛ በወታደርነት ይቀጠርና በገና ጨዋታ እና በስፖርት
እየዳበረ ቆየ። ወዲያው በ፲፱፻፵፮ ዓ/ም የአራት ልጆቹን
እናት ወይዘሪት የውብዳር ወልደጊዮርጊስን አገባ።
በ ኅዳር ወር ፲፱፻፵፰ ዓ/ም በአሥራ ስድስተኛው
የ ሜልቡርንኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈውን የ ኢትዮጵያ ን ቡድን
ለመቀበል በተደረገው ሰልፍ ላይ ከጀርባቸው ላይ
የአገራቸው ስም የተጻፈበትን መለያ ልብሳቸውን ለብሰው
አገራቸውን ወክለው የተወዳደሩትን ወጣቶች ባየ ጊዜ ምን
ያህል የኩራት ስሜት እንደተሰማውና ያን ጊዜ እሱም
እንደነሱ ለመሳተፍ እንደወሰነ ይጠቀሳል። በዚሁ ዘመን አበበ
በብሔራዊ የሠራዊቱ እርስ በርስ ውድድር ላይ ተሳተፎ፣ በ፭
ሺህ ሜትር እና በ፲ ሺህ ሜትር ሩጫ የብሔራዊውን ክብረ
ወሰን የያዘው የጊዜው የስፖርት ጀግና ዋሚ ቢራቱ እና አበበ
በ ማራቶን ውድድሩ ሲገጥሙ ተመልካቹ ሕዝብ ዋሚ
ያሸንፋል ብሎ ነበር የሚጠብቀው። ከጥቂት ኪሎሜትሮች
በኋላ አበበ ቢቂላ የተባለ ያልታወቀ ወጣት ቀድሞ ሩጫውን
እየመራ እንደሆነ ሕዝቡ በራዲዮ ሰማ። አበበ በቀላሉ ይሄንን
ውድድርም አሸነፈ። የዋሚንም የአምስት ሺ እና አሥር ሺ
ሜትር ክብረ ወሰን በመስበር እየታወቀ መጣ። በዚህ ሁኔታ
ነው አበበ ለ ፲፱፻፶፪ ዓ/ም የ ሮማ ኦሊምፒክ በተወዳዳሪነት
የተመረጠውና ካራት ዓመት በፊትም ያንን የአገሩን መለያ
ልብስ በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ለብሶ ለመሳተፍ ያለመው
ሕልሙን እውን ያደረገው።
በጦር ካምፕ ውስጥ አበበ የሚያደርጋቸውን ልምምዶች እና
ውድድሮች በጥሞና ይከታተሉ የነበሩት ስዊድናዊ አሰልጣኝ
ኦኒ ኒስካነን የአበበን ችሎታ በመገንዘባቸው ከሌሎቹ
አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ እንዲሠራ ያደርጉት እና
የሮም ኦሎምፒክ እስኪቃረብ ድረስ በሚል ከሁለት ሺህ
ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ የመሮጥ
እና የሺህ አምስት መቶ ሜትር ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ
ልምምዶችን እንዲሠሩ ያደርጓቸዋል።
“ሮማን የወረረው ብቸኛው ወታደር”
ከሮማው ድል መልስ በንጉሠ ነገሥቱ ሲሸለም
አገራችውን ወክለው በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ
ከአሰልጣኙ ጋር ወደሮማ ካመሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች
መሃል ለማራቶን ሩጫ የተመረጡት አበበ ቢቂላ እና አበበ
ዋቅጅራ ነበሩ። ውድድሩ አንድ ወር ሲቀረው እዚያው ሮማ
ከተማ ውስጥ ሲሰለጥኑ የቆዩት ሁለቱ አበበዎች፣
የሩጫውን መንገድ በጥንቃቄ እንዳጠኑና ሲሮጡም በባዶ
እግርም በጫማም እንደተለማመዱ፣ አበበ በጫማ ሲሮጥ
በአምስትና በስድስት እርምጃዎች ስለሚዘገይ ሁለቱም
በባዶ እግራቸው እንዲሮጡ መወሰኑን አሰልጣኙ ኒስካነን
ከውድድሩ በኋላ (Duvbo IK’s Annual Magazine
1960:) ለተባለ መጽሔት የተናገሩት ያሳያል። ኒስካነን
ሩጫው በማታ ሰዐት ስለሚካሄድ የሞቀው የመንገድ ሬንጅ
እንደማይጎዳቸውና ከውሳኔውም በኋላ ውስጥ እግራቸው
እንዲጠነክርም ኦሊምፒክ መንደሩ ውስጥ ሁሉ በባዶ
እግራቸው እንደነበር የሚሄዱት ይነግሩናል። በዚሁ መጽሔት
ላይ ዋቢ ቢራቱ የተዘጋጀውም፣ የተመረጠውም ለ፲ ሺህ
ሜትር ሩጫ ውድድር እንደነበረና ለኦሊምፒኩ ዝግጅት
በሚያደርጉበት ጊዜ በራሱ ውሳኔ ከስልጠና ጣቢያቸው እስከ
አዲስ አበባ ድረስ በአንድ ቀን መቶ ኪሎሜትር በመሮጥ
በመታመሙ ከቡድኑ እንደወጣ ይነግሩናል፡፡ (ብዙ ስህተታዊ
ዘገባዎች (ሀ) አበበ ቡድኑ ውስጥ የተጨመረው ዋቢ ቢራቱ
በእግር ኳስ ጨዋታ ቁርጭምጭሚቱ በመሰበሩ የሱ ምትክ
ሆኖ በመጨረሻው ሰዐት ነው (ለ) ስለዚህም የተሰጠው
ጫማ ስለጠበበው/ሌላ ስላልነበረው ነው በባዶ እግሩ
የሮጠው እያሉ ዘግበዋል።)
አሰልጣኙ ኒስካነን ሁለቱን ኢትዮጵያውያን ሯጮች የጊዜውን
ምርጥ ማራቶን ተወዳዳሪዎች፦ የ ሞሮኮው ራህዲ ቤን
አብዴ ሰላም ፣ የ ኒውዚላንድ ባሪ ማጊ፣ የሶቪዬቱ
ኮንስታንቲን ቮሮብዮቭ እና በወቅቱ የማራቶን ክብረ ወስን
ባለቤት የነበረው ሰርጌይ ፖፖቭ እና የ ብሪታንያ ተወላጅ
ዴኒስ ኦጎርማን እንደሆኑ በጥብቅ አስጠንተዋቸዋል። ራህዲ
ይለብሳል የተባለው የመለያ ቁጥሩ ፳፮ መሆኑን ያጠናው
አበበ ውድድሩ ላይ ይሄንኑ ቁጥር ለመለየት ሲፈልገው
ለካስ ራህዲ በ፲ ሺህ ሜትር ውድድር ላይ ለብሶ የነበረውን
መለያ ለብሶ ኖሮ አጠገቡ ሲሮጥም አላወቀውም።
አበበ በውድድሩ ላይ ከሃያ እስከ ሠላሳ ኪሎሜትር ላይ
ባሳየው ፍጥነት አብዛኛዎቹን ባላጋራዎቹን ጥሎ ሲሄድ
የቀረው ራህዲ ብቻ ነበር። እሱም ብዙ አብሮት አልቆየም።
አበበ ድሉን ከተቀዳጀ በኋላ “ከተማው ክልል ውስጥ ስገባ
ከኋላዬ የምሰማቸው ኮቴዎች እየቀነሱ መጡ። ፍጥነትም
ስጨምር እስከነአካቴው ድምጽም አልነበረም። ለአንድ ሰዐት
ሙሉ የኮቴዎችን ካካታ ሳዳምጥ ከቆየሁ በኋላ አሁን ጸጥታ
ሲሰፍን የተከተለኝ እንዳለ ለማየት ፊቴን ማዞር አስፈላጊ
አልነበረም” ብሏል። አበበ አስተሳሰቡ ራዲ
እስከሚያጋጥመው ድረስ ጉልበቱን ለመቆጠብ ስለነበር
በዚህ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ክብረ ወሰኑን በተሻሻለ ውጤት
ይሰብር እንደነበር ኒስካኒን ጥርጣሬ እንዳልነበራቸውም
ገልጸዋል። ሆኖም አበበ ቢቂላ ውድድሩን በሁለት ሰዐት
ከአሥራ አምስት ደቂቃ ከአሥራ ስድስት ነጥብ ሁለት
ሴኮንድ (2:15:16.2 ሰዓት) በማገባደድ የዓለምን ክብረ
ወስን ሰብሮ ወርቅ አገኘ። ራህዲ ሁለተኛ እና ባሪ ማጊ
ሦስተኛ ወጡ።
የ ጣልያን ጋዜጦች በነጋታው “ኢትዮጵያን ለመውረር
የጣልይን አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር ኢትዮጵያ ግን
አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው” የሚል
ጽሁፍ ይዘው ወጥተው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ
ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ
አበበ ቢቂላ ነው። ይህም አጋጣሚ ለብዙ ጥቁር
አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ በር
ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከአለም ጫፍ እስከ ጫፍ
ተዳረሰ።
የአበበ ቢቂላ አዲሱ የዓለም ክብረ ወሰን = 2:15:16.2
የሰርጌይ ፖፖቭ አሮጌው የዓለም ክብረ ወሰን =
2:15:17.0
አበበ ከዚህ ውድድር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ በሁለት
ወሩ በክብር ዘበኛ ሠራዊት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል
መንግሥቱ ንዋይ እና በወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ
ጥንሰሳ የተካሄደው ፲፱፻፶፫ ዓ/ም የታኅሣሥ ግርግር
መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲከሽፍ፣ የሠራዊቱ አባል
የነበረው አበበም ከሌሎች ወታደሮች ጋር በመጠርጠር
ለጥቂት ጊዜ ታስሮ ነበር።
ከግርግሩ በኋላ
ከታኅሣሡ ግርግር በኋላ እስከ ጥቅምት ፲፱፻፶፬ ዓ/ም
ድረስ አበበ በ ግሪክ በ ጃፓን እና በኮሲቼ በ ቼኮስሎቫኪያ
በማራቶን ተወዳድሮ በሁሉም አንደኛ በመውጣት አሸንፏል።
በሚከተሉት ሁለት ዓመታት ግን በማናቸውም የዓለም አቀፍ
ማራቶን ውድድር ላይ ሳይሳተፍ ቆይቶ በ ሚያዝያ ፲፱፻፶፭
በ ቦስተን ከተማ በተካሄደው ማራቶን ላይ ተሳትፎ አምስተኛ
ሆኖ ነው የጨረሰው።
ሐምሌ ፫ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ/ም አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው
የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ማጣሪያ ውድድር በአበበ አሸናፊነት፤
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ማሞ ወልዴ እና ሦስተኛ የወጣው
ደምሴ ወልዴ ወደ ቶክዮ እንደሚጓዙ ሲረጋገጥ በመላው
ዓለም ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት ኃይለኛ
ተወዳዳሪዎች እንዳላት ተሰማ።
ሁለተኛው የኦሎምፒክ ወርቅ
የ ፲፱፻፶፯ ዓ/ም ፲፰ኛው የ ቶክዮ ኦሊምፒክ ሊካሄድ አርባ
ቀናት ሲቀረው አበበ ቢቂላ በማራቶን ውድድር ልምምድ ላይ
ነበር። በልምምዱ ላይ እያለም ህመም ቢሰማውምን
ህመሙን ችላ በማለት ልምምዱን ቀጠለ። ነገር ግን
በልምምድ ላይ ራሱን ስቶ ይወደቅና አንስተው ወደ
ሆስፒታል ሲወሰዱት ህመሙ ያበጠ የትርፍ አንጀት ሆኖ
ተገኘ። ወዲያው ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ለጥቂት ቀኖች
ካገገመ በኋላ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ በምሽት
ልምምዱን ቀጠለ።
አበበ ቢቂላ ከኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ጋር አብሮ ወደ
ቶኪዮ ሲጓዝ በርትቶ ይወዳደራል ብሎ ያሰበ ሰው
አልነበረም። አበበ ግን (ጫማ አድርጎ) ለዚህ ማራቶን
ውድድር ጥቅምት ፲፩ ቀን ከአርባ አንድ አገሮች ከተውጣጡ
ሰባ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ጋር ተሰለፈ።
ለአበበ ቢቂላ ምንም አዲስ ዘዴ አላስፈለገውም። አሰልጣኙ
ኦኒ ኒስካነን እንደ ሮማው ኦሎምፒክ ከፊት ከሚመሩት
ቡድኖች ጋር እስከ ሃያ ኪሎ ሜትር ድረስ አብሮ እንዲሮጥና
ከዚያ በኋላ ውድድሩን እንዲመራ መከሩት። በዚህም ዕቅድ
መሠረት ከሮጠ በኋላ ፍጥነቱን በጥንቃቄ ቀስ በቀስ
እየጨመረ ሄደ። በአሥራ አምስተኛው ኪሎ ሜትር ላይ
አብረውት የነበሩት የ አውስትራሊያ ው ሮን ክላርክ እና
የ አየርላንድ ጄምስ ሆጋን ብቻ ነበሩ። አበበ ቢቂላ በቀዶ
ጥገናውም ሆነ በሞቃታማው የአየር ሁኔታ ምንም ዓይነት
እንከን አልታየበተም። እንዲያውም ሲሮጥ ለሚመለከተው
ከመሬቱ በላይ የሚንሳፈፍ ይመስል ነበር። አሰልጣኙ ኦኒ
ኒስካነን ትንሽ ጉልበት በመጠቀም እንዴት መሮጥ
እንዳለበት ያስተማሩትን አበበ ቢቂላ በተግባር ላይ
ሲያውለው እና ሩጫው ምንም ዓይነት ጥረት
የማያስፈልገው ያስመስለው ነበር።
አበበ ቢቂላ ኦሎምፒክ ስታዲዮሙ ውስጥ የገባው ብቻውን
ነበር። በዚያም ይጠባበቅ የነበረው ፸ ሺህ ተመልካች
በከፍተኛ ሁኔታ አድናቆቱን ገልጾለታል። በዚህ ውድድር ላይ
የራሱን ክብረ ወሰን በድጋሚ በመስበር አሻሽሎታል። አዲሱ
ክብረ ወሰንም ሁለት ሰዐት ከአሥራ ሁለት ደቂቃ ከአሥራ
አንድ ነጥብ ሁለት ሴኮንድ (2፡12፡11.2) ነበር።
ውድድሩንም እንደጨረስ ምንም አይነት ድካም
አልታየበትም። እንዲያውም ገና ሊሮጥ የሚሰናዳ ነበር
የሚመስለው። ተመልካቹን በጣም ያስገረመው በውድድሩ
ምክንያት ጡንቻው እና መገጣጠሚያዎቹ እንዳይተሳሰሩ
የተለያዩ የሰውነት ማሟሟቂያ ስፖርቶች ሲሰራ
መመልከታቸው እንዲሁም እርጋታው እና ቅልጥፍናው ነበር።
አበበ ከውድድሩ በኋላ ተጠይቆ ሲመልስ ሌላ አስር ኪሎ
ሜትር ጨምሮ መሮጥ ይችል እንደነበር ተናግሯል። ደምሴ
ወልዴ በአሥረኛ ደረጃ ሲጨርስ ማሞ ወልዴ ግን አሥራ
አምስት ኪሎሜትር ላይ አቋርጦ ከውድድሩ ወጣ።
አበበ ከሮሙ ድሉ አራት ዓመት በኋላ ቶኪዮ ድሉን ሲደግም
የኦሊምፒክን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ክብረ ወሰን መስበር
ችሏል። ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም
በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ
ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድልንም ፈጸመ።
ይኸም ብቻ አይደለም ባሻናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ
በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባዝል ሔትሌይ በ2 ሰዓት
13 ደቂቃ 55 ሰኮንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን
በ1 ደቂቃ 43 ካልዒት (ሰከንድ)፣ 8 ሣልሲት (ማይክሮ
ሰከንድ) የሰበረበት ነው::
‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፤ ይቆረጣጥማል ሰዓት
እንደቆሎ፤›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ
ዋና ጸሐፊና የልዑካኑ መሪ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ
( ፲፱፻፲፬ – ፲፱፻፸፱ ) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል። [2]
ቻርሊ ሎቬት “ማራቶን በኦሎምፒክ” በሚለው መጽሐፉ
ላይ ስለቶክዮው ውድድር ሲዘግብ “ግማሽ ሩጫውን
እንዳገባደደ በአምስት ሰከንድ ልዩነት ይመራ ነበር” ይላል ።
ሎቬት “የክፍለ ዘመኑ ሩጫ ብዙ ታሪክ የተጻፈለት እና
የተወራለት ውድድር ነው” ሲል አበበ ቢቂላን ደግሞ “ወደር
የማይገኝለት እውነተኛ የማራቶን ሯጭ ምሳሌ ነው”
ይለዋል። ሪቻርድ በኔዮ ደግሞ “የማራቶን ጌቶች” በሚለው
መጽሐፉ “አበበ ቢቂላ ሩጫው ምንም አይነት ጥረት
የማያስፈልገው ያስመስለዋል” ብሎታል። “አበበ ቢቂላን
ሲያዩት ረጅም ቀጠን ያለ በቀላሉ ተሰባሪ ይመስላል፣ ነገር
ግን ከሚገባው በላይ ጠንካራ አትሌት” ነው ይልና “አበበ
ቢቂላ ማናቸውም የማራቶን ሩጫ ተወዳዳሪ ሊሆን
የሚገባው ምሳሌ ነው” ብሏል። ቀጥሎም “አበበ ቢቂላ
ተፈጥሮ ካፈራቻቸው ምርጥ የዓለማችን አትሌቶች አንዱ
ነው” ይልና “በዚህም (በቶክዮው) ድል የተነሳ ለሁለት ጊዜ
የኦሎምፒክ ማራቶንን ያሸነፈ ብቸኛ አትሌት አድርጎታል”
ይላል።
አበበ ቢቂላ ሁለተኛውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሰ
የአዲስ አበባ ሕዝብ ተገልብጦ ወጥቶ የጀግና አቀባበል
ካደረገለት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ የ ሻምበል ነት ማዕረግና
አዲስ ቮልስ ዋገን ቢትል ሸለሙት።
ሜክሲኮ ከተማ
በ ፲፱፻፷ ዓ/ም ላይ በ ሜክሲኮ ከተማ የተካሄደው ፲፱ኛው
ኦሊምፒክ ውድድር ከመጀመሩ በፊት አበበ በ ፲፱፻፶፯ ዓ/ም
እና ፲፱፻፶፰ ዓ/ም ሦስት ማራቶኖች ላይ ተሳትፎ ሦስቱንም
አሸንፏል። በ ሰኔ ወር ፲፱፻፷ ዓ/ም እግሩ ላይ በደረሰበት
ጉዳት ምክንያት ዝግጅቱን እንዲያቋርጥ ተገዶ ነበር። በድ
ግሪንስፓን “የኦሊምፒክ ተወዳጅ ታሪኮች” በሚባለው የትረካ
ፊልም ላይ “ከውድድሩ ጥቂት ቀናት በፊት አበበ ትንሽ
የእግር አጥንቱን ሰብሮ ነበር” ብሏል።
ሜክሲኮ ሲገባም በእግሩ ላይ የደረሰው ጉዳት
አልተሻለውም ነበር። ውድድሩ የሚካሄድበት ቦታ ከፍታው
አበበ ቢቂላ ከለመደው በ አንድ ሺህ ጫማ ከፍታማ
ቢሆንም እንድ አበበ ግምት ግን ከሌሎች አትሌቶች ይልቅ
ይህ ከፍታ ለኔ ይጠቅመኛል ብሎ ነበር።
የማራቶኑ ውድድር እሑድ ጥቅምት ፲ ቀን ፲፱፻፷ ዓ/ም
ሲጀመር ከአርባ አንድ አገራት የተውጣጡ ሰባ አራት ሯጮች
ተሰልፈው ነበር። ኢትዮጵያ በቶክዮው ማራቶን እንድተደረገው
በሜክሲኮም ከአበበ ጋር ሦስት ሯጮችን አሰልፋለች። ማሞ
ወልዴ እና ገብሩ መራዊ ሌሎቹ ተሳታፊዎች ነበሩ። አበበ
ውድድሩን ጀምሮ ከፊት ከሚመሩት ጋር እስከ አስራ
ሰባተኛው ኪሎሜትር ድረስ ከሮጠ በኋላ የእግሩ ሕመም
ስለጠናበት አብሮት የነበረው ማሞ ወልዴ ባልገመተውና
ባላሰበው ሰዓት በጆሮው ተምዘግዝጐ የገባውን የአበበን
ቃላት ማመን አቃተው። እንደመደንገጥ ብሎ «ምን
አልከኝ ?» በማለት ጠየቀው። አበበም የማሞን መደናገጥ
ስለተገነዘበ እንደ ማባበል ዓይነት አለና « አይዞህ
ታሸንፋለህ፤ እኔ አልቻልኩም፤ የ እግሬ ወለምታ በጣም
ተሰምቶኛል፤ ሌላም የማላውቀው ስሜት እየተሰማኝ ነው።
ስለዚህ አደራዬን ተቀበለኝ፤ የ ኢትዮጵያ ሕዝብ
ይጠብቀናል፤ እኔ ስላልቻልኩ አንተ ቀጥል፤ የ ኢትዮጵያ
አምላክ ይከተልህ» ካለው በኋላ አስፋልት ዳር ወደቀ።
እውነትም በጣም ታሟል። ወዲያውኑ አበበ ሜክሲኮ
ሆስፒታል በአስቸኳይ ተወሰደ።
የአበበ አለመጨረስ ሲሰማ ያልደነገጠ ኢትዮጵያዊም ሆነ
የአበበ አድናቂ አልነበረም። ሁናቴውን ታዋቂው ጋዜጠኛ
ሰለሞን ተሰማ እንዲህ ገልፆት ነበር፤ «የአበበን መውጣት
ስሰማ ማሞን ለማበረታታት የጮህኩት ጩኸት ድምፄን
ለሦስት ቀናት ያህል ዘግቶት ነበር።»
በዚህ ውድድር ገብሩ መራዊ ስድስተኛ ሆኖ ሲገባ ከአበበ
ቢቂላ ጋር አብሮ የተጓዘው ማሞ ወልዴ አሸንፎ ለኢትዮጵያ
ሦስተኛውን የማራቶን ወርቅ ተቀበለ። ማሞ ወልዴ
ከውድድሩ በኋላ እንድብራራው አበበ ቢቂላ በሕመም
ምክንያት ባያቋርጥ ኖሮ ያለምንም ጥርጥር ያሸንፍ ነበር
ብሏል። አበበ ቢቂላ ከዚህ በኋላ ውድድር አላደረገም።
አሳዛኝ አደጋ
ሻምበል አበበ ቢቂላ በ፲፱፻፷፩ ዓ/ም በሽልማት የተሰጠውን
ቮልስ ዋገን መኪና በአዲስ አበባ ውስጥ ሲነዳ አደጋ
ደርሶበት ከወገቡ በታች ሽባ ሆነ። ንጉሠ ነገሥቱ ለሕክምና
ወደ እንግሊዝ አገር ልከውት በታወቀው የስቶክ ማንደቪል
ሆስፒታል (Stoke Mandeville) ሲረዳ ቢቆይም
ከተሽከርካሪ ወንበር የማያላቅቀው በመሆኑ ወደሚወዳት
ሀገሩ ኢትዮጵያ በቃሬዛ ተመለስ። አዲስ አበባ ቦሌ
አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ቤተሰቡ፣ ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ
ሲቀበሉት በበዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም በየመንገዱ
ዳር ተሰልፈው እያጀቡ ተቀበሉት። ከአደጋው በኋላ እነኛ
ዓለምን ያስደነቁ እግሮች ሁለተኛ አልተራመዱም።
አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን የቀስት ኢላማ ውድድር ውስጥ
እንዲሳተፍ ሲመክሩት ነበር፣ አበበ “በተሸከርካሪ ወንበሬ ላይ
ሆኜ ማራቶንን አሸንፋለሁ” እያለ ይቀልድ ነበር። ሆኖም
ከአደጋው በኋላ በስቶክ ማንደቪል አካላቸው በጎደለ ሰዎች
ስፖርት ውስጥ በዚሁ የቀስት ኢላማ ውድድር ላይ
ከመሳተፉም በላይ “መልካም ውጤት የሚያመጡ ሰዎች
አሳዛኝ አደጋም ይገጥማቸዋል። በእግዚአብሔር ፍቃድ
የኦሎምፒክ ማራቶንን ለማሸነፍ በቃሁ እንዲሁም
በእግዚአብሔር ፍቃድ የመኪና አደጋ ደረሰብኝ። ድሉን
እንደተቀበልኩ ሁሉ እንዲሁም መከራውን መቀበል አለብኝ።
ሁለቱንም የሕይወት ሁኔታዎች ስለሆኑ በጸጋ ተቀብዬ
ሕይወቴን በደስታ መኖር ነው ያለብኝ” ብሏል።
የሁለቴው የኦሊምፒክ ማራቶን አሸናፊና የማራቶን የክብር
ወሰን ባለቤት ሻምበል አበበ ቢቂላ በ፲፱፻፷፬ ዓ/ም
በተካሄደው ፳ኛው የ ሙኒክ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ በልዩ
እንግዳነት ተጋብዞ በተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ
ውድድሩን ይመለከት ነበር። የማራቶኑን ውድድር ያሸነፈው
አሜሪካዊ ው ፍራንክ ሾርተር ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ
በቀጥታ ወደ አበበ ቢቂላ በመሄድ እና እጁን በመጨበጥ
ያለውን ፍቅር እና አክብሮት ገልጾለታል።
ጀግና ወደቀ
ሻምበል አበበ ቢቂላ ፤ “ሮማን የወረረው ብቸኛው ወታደር”፤
በተወለደ በ ፵፩ ዓመቱ፤ የሜክሲኮውን ሩጫ አቋርጦ
መንገድ ዳር በወደቀ በስድስት ዓመቱ ጥቅምት ፲፭ ቀን
፲፱፻፷፮ ዓ/ም የሕይወት ትግሉን ጨርሶ ከዚህ ዓለም
በሞት ተለየ። ከተወዳደረባቸው አስራ አምስት የማራቶን
ውድድሮች አስራ ሁለቱን በአንደኛነት የጨረሰው
ኢትዮጵያዊው ጀግና ጉዞውን አከተመ።
አበበ አዲስ አበባ በ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ሲቀበር
ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት ዘመዶቹ ወዳጆቹ እና
አድናቂዎቹ ጋር ከ፸፭ ሺህ በላይ የሚሆን ሕዝብ ተሰብስቦ
እየተላቀሰ የመጨረሻ ስንብት አድርጎለታል። ዕለቱም በመላ
ኢትዮጵያ የሐዘን ቀን ሆኖ እንዲውል ተደርጓል።
ጥቅስ
“እኔ ዓለም ሁሉ እንዲያውቀው የምፈልገው አገሬ
ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ የምታሸንፈው በቆራጥነት እና በጀግንነት
ነው” ሮማ ካሸነፈ በኋላ
“መልካም ውጤት የሚያመጡ ሰዎች አሳዛኝ አደጋም
ይገጥማቸዋል። በእግዚአብሔር ፈቃድ የኦሎምፒክ
ማራቶንን ለማሸነፍ በቃሁ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፈቃድ
የመኪና አደጋ ደረሰብኝ። ድሉን እንደተቀበልኩ ሁሉ
እንዲሁም መከራውን መቀበል አለብኝ። ሁለቱም የሕይወት
ሁኔታዎች ስለሆኑ በጸጋ ተቀብዬ ሕይወቴን በደስታ መኖር
ነው ያለብኝ።” የተሽከርካሪ ወንበር ተጠቃሚ ከሆነ በኋላ
“እኔ የዓለም አንደኛ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ሯጭ ነኝ”
ለዋሚ ቢራቱ ያለውን ፍቅር ክብር እና አድናቆት ሲገልጽ።
“ለምወዳት አገሬ ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ የሺህ ዓመት
መኩሪያ እና መከበሪያ ታሪክ በእግዚአብሔር ፈቃድ
ስለሠራሁ ከእንግዲህ በኋላ የምመኘው ነገር የለም።”
እኛስ ኢትዮጵያውያን ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ምን
አደረግንላት?(ተርጓሚው)
የአበበ ቢቂላ የክብር መታወሻዎች
አዲስ አበባ ውስጥ አባ ኮራን ሰፈር የሚገኘው
የቀድሞው የአሜሪካ ሕብረተሰብ ት/ቤት ስታዲየሙን
በአበበ ስም ሰይሞታል
አምስተርዳም – የአበበ ቢቂላ መንገድ አላት
ሮማ አበበን የዘከረችው በሩጫ ብቻ ሳይሆን ከከተማዋ
፳፭ ኪሎ ማትር ርቀት ላይ በምትገኘዋ ላዲስፖሊ ከተማ
የሚገኘውን አዲስ የእግር ድልድይና መንገድ በአበበ ቢቂላ
ስም (ፖንቴ አበበ ቢቂላ) በመሰየም ነው፡፡
የ ሴኔጋል መዲና ዳካር በ፲፱፻፸፩ ዓ.ም. የመጀመሪያውን
የአፍሪቃ አትሌቲክስ ውድድር አጋጣሚ በማድረግ ወደ
“ዴምባ ዲዮፕ” ስታዲየም የሚያስገባውን መንገድ የአበበ
ቢቂላ መንገድ ብላዋለች።
የአበበ ቢቂላ የቶክዮ ድል “ቶክዮ ኦሊምፒያድ” በተባለ
የትረካ ፊልም ላይ ተጨምሯል። ከዚሁ ፊልም የተወሰደ
ጉራጅም በ ፲፱፻፷፰ ዓ/ም በተሠራው “ማራቶን ማን”
በተባለው ፊልም ላይ ይገኛል።
“ቪብራም” የተባለ የ አሜሪካ የጫማ ድርጅት በ ፳፻፪ ዓ/
ም “ፋይቭፊንገርስ ቢቂላ” (FiveFingersBikila) የተባለ
ጫማ ገበያ ላይ አዋለ።
ሮቢን ዊሊያምስ የተባለው አሜሪካዊ ቀልደኛ ‘የራስ
ማጥፊያ መሳሪያዎች’ በተባለው ዝግጅቱ ላይ የአበበን
በባዶ እግር መሮጥ ይጠቅሰዋል።
ዕሮብ፣ ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፭ ቀን ለሕዝብ እይታ የቀረበው
የ’ጉግል’ (Google) ሰሌዳ የአበበን ፹ኛ ልደት በመዘከር
በሮማው ውድድር ላይ በባዶ እግሩ የመጨረሻውን መስመር
በጥሶ ሊያልፍ ሲል የነበረውን ገጽታ የሚያሳይ ምስል
አቅርቧል።
-መልካም ንባብ ለሁላችን።
-ስህተት ካለ በማስረጃ ለመታረም ዝግጁ ነን።
-ለሁሉም አስተያየቶቻችሁ በቅድሚያ ምስጋናየን አቀርባለሁ።
– በማንኛውም ሰዕት “BOLE HOMES” የሚለውን ፔጅ LIKE በማድረግ የተለያዩ ታሪኮችን መከታተል ይችላሉ።

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.