አባትና ልጅ
የሰማንያ ሰባት አመት የእድሜ ባለፀጋ ሽማግሌ፤ ከአርባ አምስት አመት ዶ/ር ልጃቸው ጋር ተቀምጠው እያወጉ ሳለ፤ በድንገት ቁራ መስኮቱን በመንቆር ሲቆሮቁር ተመልክተው፡-
አባት፡- ‹‹ልጄ፤ ይሄ ነገር ምንድን ነው?››
ልጅ፡- ‹‹ቁራ ነው…››
ከትንሽ ቆይታዎች በኋላ አባት መልሰው ልጃቸውን በድጋሚ ይጠይቃሉ፤ ‹‹ይሄ ነገር ምንድን ነው?››
ልጅ፡- ‹‹አባዬ፤ አሁን እኮ ነገርኩህ ቁራ ነው››
አሁንም ከትንሽ ጊዜያቶች በኋላ አባት ለሶስተኛ ጊዜ ልጃቸውን ይጠይቃሉ፤
‹‹ይሄ ነገር ምንድን ነው?››
ልጅ፡- በአባቱ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ ጥያቄ በመበሳጨት ቆጣ ብሎ ‹‹ነገርኩህ አይደል እንዴ፤ ቁ…ራ…ነው፡፡››
አባት፡- ለአራተኛ ጊዜ ወደ ልጃቸው በመዞር ‹‹ይሄ መስኮቱ ላይ ያለው ነገር ምንድን ነው?›› ብለው ሲጠይቁ፤
ልጅ፡- በጣም በመበሳጨትና በጩኸት፤ ‹‹ለምንድን ነው አንድ ጥያቄ አስር ጊዜ እየደጋገምክ የምትጠይቀኝ፤ ስንት ጊዜ ልንገርህ፣ ቁራ ነው አልኩህ እኮ፤ ለምን ታደርቀኛለህ፤ እንዴት ይሄን መረዳት ይከብድሃል፡፡››
አባትየውም በዚህ ጊዜ ከመቀመጫቸው በመነሳት ወደ መኝታ ቤታቸው በመሄድ፤ ልጃቸው ከተወለደ እለት ጀምሮ ሲፅፉበት የነበረውን የተቦጫጨቀና በእድሜ ብዛት ያረጀ የየቀን ማስታወሻ መፃፊያ ደብተር (ዲያሪ) ይዘው በመምጣታት፤ ልጃቸውን እንዲያነብ ይሰጡታል፡፡ በማስታወሻ ደብተሩም ላይ የተፃፈው እንዲህ ይነበብ ነበር፡-
‹‹…ዛሬ ልጄ ሶስት አመት ሞላው፤ በሶፋው ላይ ተቀምጠን እየተጫወትን ሳለን በድንገት አንድ ቁራ መስኮቱ ላይ ተቀመጣ ያያል፤ ልጄም በመጓጓት ምን እንደሆነ ሃያ ሶስት ጊዜ ጠየቀኝ፤ እኔም ሃያ ሶስት ጊዜ ቁራ እንደሆነ መለስኩለት፤ ሃያ ሶስት ጊዜ እየተፍለቀለቀ ደጋግሞ ሲጠይቀኝ አቅፌው ጉናጮቹን በመሳም እና በልጄ ኮልታፋ አንደበት በመደሰት ሃያ ሶስቱንም ጊዜ ሳልሰለች መለስኩለት፤ በእርግጥም ልጄ ከዚያም በላይ ቢጠይቀኝ ኖሮ ለመመለስ ዝግጁ ነበርኩ…›› በማለት ካቀረቀሩበት ቀና ብለው ልጃቸውን አዩት፤ የልጃቸውም አይን በእንባ ተሞላ፡:
*ትምሀርት*፡- ወላጆችችሁ በሚያረጁበት እና በሚደክሙበት ወቅት፤ እነርሱን በመሸሽ፣ በማንቋሸሽ፣ እንደ ሸክም በመቁጠር ፊት አትንሷቸው፡፡ ይልቁንም ከጎናቸው በመሆን በመልካም አንደበት፣ በፍቅር ቋንቋ፣ በትህትና ቃላት፤ በፈገግታ መልክ ልታናግሯቸው እና በቅንነት ልትመልሱላቸው ይገባል፡፡ ፈጣሪ እድሜና ጤና ለወላጆቻችን ይስጥልን!