ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ

መጀመሪያ አንድ ጥያቄ አብረን ለሁላችን እናንሳ:: ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድይችላልን ማለት ምን ማለት ነው? ኦሪት ዘፍጥረት እንደሚያብራራዉ ጥንታዊዉ የኢትዮጵያ መልከአምድር አሁንካለዉ የኢትዮጵያ መልከአምድር ጋር ተመሳሳይነት አለዉ:: ዘፍጥረት 2፥13 የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነውእርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል። ይግረማችሁ ብሎ ደግሞ የኢትዮጵያዊዉን መልክ ትንቢተ ኤርምያስ13፥23 እንዲህ ያብራራዋል ‘በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ።‘

መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 1፥38 ደግሞ “ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንናፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት።” ይላል :: ለምሆኑሰሎሞን ወደዬትኛው ግዮን ነበር የመጣዉ? ኢትዮጵያን ወደሚከበዉ ግዮን? ይህ ግዮን የትኞቹ አካባቢዎች ድረስየሚዘልቅ ነው?

ከሆነስ ሆነና መልኩ ሳይቀር ከነመልከአምድሩ በጥንታዊ መጽህፍ ዉስጥ የተካተተለት ኢትዮጵያዊ እስከምን ድረስየቀደመ መሰረቱን ጠብቆ ቀጥሎአል? ነው ወይስ አንዳንዶች እንደሚነግሩን ይህ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብርዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? ተብሎ የተነገረለት ህዝብ ሌላ ህዝብ ነው? ይህ የመጽሀፍ ቅዱስ አባባልለኢትዮጵያዉያን የጋራ ማንነት ፍለጋ የሚያበረክትላቸዉ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገር ይሆን ? የኢትዮጵያ ሰዉ የጋራማንነት የሌለዉ ግፋ ቢል የመቶ አመት የወረራ ታሪክ ያገናኘዉ ህዝብ ነው በማለት የብሔር የልዩነት ፖለቲካዊፍልስፍናን ሙጭጭ ያሉት ወገኖቻችንንስ ማሳመን የሚችል ነገር ከዚህ ጥንታዊ ታሪክ ዉስጥ ተፈልቅቆ ይወጣይሆን?

ለምሆኑ ዛሬ ኢትዮጵያዉያን ወደተለያዬ የጎሳ መጥሪያ ስም ከመከፋፈላቸዉ በፊት ይጠሩ የነበረዉ ኢትዮጵያዊበሚል አንድ ስም ነበር ማለት ነው? በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድይችላልን ማለት ራሱ ምን ማለት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች ያነሳሁት ለሁላችሁ ኢትዮጵያን ጥቂት የጋራ የምርምር ጭብጥ ቢፈነጥቅላችሁ ብዬ ነዉ:: ይህ እንዳለ ሆኖ እኔ ወደራሴ ሀሳብ ልግባ :: የኔ ሀሳብ ኢትዮጵያዊነት የእኔ ናርዶስ ሽቶ በሚል ጥቅል ጭብጥ የተካተተ ነዉ::

ኢትዮጵያዊነት አንዳንዶች ያቅለሸልሸናል ይላሉ ፣አንዳንዶች በሀይል የተጫነብን ማንነት ነዉ ይላሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ኢትዮጵያ ድህነቱዋ አስመርሮናልና ኢትዮጵያዊነት የሚለዉን ቃል መስማት ልባችንን ያሳምመዋል ቆዳችንንም ይኮሰኩሰዋል ይላሉ፣ አንዳንዶችም በኢትዮጵያ ምድር የተነሱ የቀደሙና ያሁኑ ዘመን ገዥዎችን ስለምንጠላ ኢትዮጵያዊነትንም እንጠላለን፣ ኢትዮጵያዊነትም አገዛዝም በቃን በማለት ኢትዮጵያዊነትን ከመሪዎችና ከገዥዎች ጋር አስተሳስረዉ ያቀርቡታል ፣ አንዳንዶች ኢትዮጵያዊነት የሚለዉን ቃሉ ስንሰማዉ ያመናል ይላሉ፣ ሌሎችም ኢትዮጵያዊነት ሁለተኛ ማንነታችን ነዉ እኛ ሌላ ማንነት አለን ይላሉ::

በፊት በፊት እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎች እኔንም ልቤ ዝቅ እስኪል የሚያሳምም ስሜት ይቀሰቅሱብኝ ነበር:: ለምን? አሁን ግን የማስበዉ እንደዚያኛዉ ዘመን አይደለም:: አሁን ከእነዚህ መሰል ሰዎች ጋር ስገናኝና በኢትዮጵያዊነት ላይ

ያላቸዉን ጥላቻ ሲገልጹልኝ አንድ ዉብ መርህ አለኝና ያን ዉብ መርህ አንዲያከብሩልኝ አካፍላቸዋለሁ:: አያይዤም እኔም የእነሱን መርህም እንደማከብር እነግራቸዋለሁ:: የእኔን መርህ አላከብር ብለዉ የእኔን ኢትዮጵያዊነት ማጣጣል ከቀጠሉ ግን ወደ ወይን ማሳዬ አትግባ: እንቁዬንም በእግርህ ለመርገጥ አትንደርደር አባቶቼ እንዳስተማሩኝ እንቁህን እሪያ እገር ስር አትጣል ተብያለሁና የሚለዉን ያባቶች አስተምሮት አስከትላለሁ::

ለምሆኑ የእኔ የኢትዮጵያዊነት መርህ ምንድን ነዉ? ከላይ እንደተባለዉ ላንዳንዶች አልጣፍጥና መአዛማ ሽታን አላመነጭ ያለዉ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ የናርዶስ ሽቶዬ ነዉ:: ለዚህም ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ የሚል መርህ አለኝ:: ይህ የናርዶስ ሽቶ ምንድን ነዉ? የከበረ ሽቶ ነው ፣ ዋጋዉም የማይተመን ነዉ ፣ የማይመለከታቸዉ ሰዎችም በ እግራቸዉ ሊረግጡት የማይገባ ነዉ፣ ከማንም ጋር የማይደራደሩበት ማንነትም ነዉ:: ብሎም አንደኛም ሁለተናም ሶስተኛም ማንነቴም ነዉ:: ሌላ ማንነት ፍለጋ ከመኩዋተን ልቤ ያረፈበት ፣ መንፈሴ የተመቻቸበት ብሎም የወደፊት ራዕዬ የሚሳለጥበት ጉዞዬ ነዉ::

ሁሉ በዚህ አገር ጥላ ሰር የተሰባሰበ ወገን እንዲህ ያስብ ወይም እንዲህ ያለ መርህ ይኑረዉ ብዬ አልሰብክም ወይም አልጮህም ወይም ደግሞ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ኢትዮጵያዊነትን የሚጠሉ ወገኖች ኢትዮጵያዊነት አንደኛ ማንነታችን ነዉ ብለዉ እንዲናገሩ በመለማመጥና በማግባባት ጊዜ አላጠፋም:: ኢትዮጵያዊነትን ፖለቲካ አይደለም ደግሞም የሚሰበክ ጉዳይ ነዉ ብዬ አላምንምና:: ኢትዮጵያዊነት ከማንኛዉም ፖለቲካዊ ይዘት በላይ ነዉና::

አንድ ነገር ግን አዉቃለሁ አምናለሁ ደግሞም ነኝምም:: ያም ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ መሆኑን:: አባቶቼ ከዚህ ዉጭ ማንነት አላስተማሩኝም ወይም ደግሞ አልነገሩኝም ወይም ከአባቶቼ የቀደም ታሪክ ዉስጥ አባቶቼ በቀደመ ዘመናቸዉ ሌላ ማንነት ፍለጋ ሲንጎዳጎዱ የሚያሳይ ሰነድ አላገኘሁም:: አባቶቼ እንዲህ ይሉ ነበር :- “ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ”:: እኔም እንዳባቶቼ አንዲህ እላለሁ-ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ:: ይህማ የትምከህት ህሳቤ ነዉ የሚለኝ ከመጣም አንድ መልስ አለኝ:: ያ መልስ ወዲህና ወዲህ ሳልል በሁሉም ቦታ የምናገረዉ ነዉ:: ታዲያ በምን ልመካ? በሆንኩትና በማንነቴ እንድመካ ለምን አትተዉኝም? አባቶቼ ያወረሱኝ ትምክህት አንድ ነዉ:: እሱም ኢትዮጵያዊነት የናርዶስ ሽቶዬ የሚል ነዉ::

ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ ነዉና :: ኢትዮጵያዊነት የሰዉ ልጅ የማንነት አብሮነት ተምሳሌት ነዉ:: ያም ሁሉ የሰዉ ልጅ ማንነት በጋራ የሚገለጥበት:: ኢትዮጵያዊነት የነብዩ መሐመድ የእምነቱ ጠለላና ከለላ አለሆነም? የዚህ ዘመን ታላቅ የአለም ህዝብ እምነት ሆኖ ይቀጥል ዘንድ የእስልምና እምነትን የታደጉ የእኔ አባቶች አይደሉም? ደግሞስ ከነበያት እስከ ሐዋርያት በአንደበታቸዉ የታቃኙለት ህዝብ የእኔ ህዝብ አይደለም?

በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? ተብሎ ማንነቱ ከነመልኩ በእግዚአብሄር ቅዱስ መንፈስ በሚመሩ ነበያት የተነገረዉ ስለ እኔ አባቶች አይደለም? እኔስ ያባቶቼ ልጅ አይደለሁም? ይህ የማይለዉጥ ኢትዮጵያዊነቴስ ሊለወጥ ይችላል? በስሜት ሳይሆን በአስተዉሎት እንዲህ እላለሁ:- እኔ ያባቶቼ ልጅ ነኝ:: ያባቶቼ ማንነት ኢትዮጵያዊ እንደነበር እኔም እንዲሁ:: እንዲህ እላለሁ- ኢትዮጵያዊ መልኩንና ማንነቱን ይለውጥ ዘንድ አይችልምና እኔም እንዲሁ:: ደግሞስ ከሙሴ በፊት የእግዚአብሄር ካህን ሆኖ እግዚአብሄር ያገለገለ : ለሙሴስ አመራርን ያስተማረ ካህኑ የቶር የእኔ አባት አይደለም? ያፌታዊ ፣ ሴማዊ ፣ ካማዊ ብሎም የአዳም ዘር በመላ በዉህድ ያስገኙት መገለጫ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት አይደለም? ኢትዮጵያዊነት የሰዉ ዘር በነጻነት ስለመኖር የተሰበከበት ማንነት አይደለም ? ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ርህራሄ መሆኑን መላዉ አለም አለመሰከረም? ይህንን እዉነትስ የአለም ታታላቅ ምሁራን የመሰከሩት እዉነት አይደለምን?

አሁን ይሄ ምን ጥቅም አለዉ ለሚለኝ ሰው ጠቀሜታዉን ለማሳዬት አልባትትም:: ወይም በእኔ እይታም እንዲማረክ አልደክምም:: እኔ ግን በዚህ ኢትዮጵያዊነት ተማርኬአለሁ ብሎም ኢትዮጵያዊ ማንነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ ስል እናገራለሁ:: በዚህ አቁዋሜ የሚከፋዉ ካለ ለሱ መከፋት ተጠያቂ አይደለሁም:: ደግሞም እኔ ይህ የናርዶስ ሽቶ የሆነ ማንነት ማንም ወገን ላይ ያለፍላጎቱ መጫን አለበት ብዬ አላምንም:: ሆኖም ማንም ሰዉ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ስላለወደድ እኔ ወይን ማሳ ዉስጥ ገብቶ የእኔ ናርዶስ ሽቶ የሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነቴን መረጋገጥ የለበትም:: ያን የሚያደር ሰዉ ካለ አባቶቼ እንዳስተማሩኝ እንቁውዬን አሪያዎች እንዳይረግጡብኝ ቆፍጠን ብዬ የማንነቴን የወይን ማሳ ዉስጥ አትግቡ ብዬ እናገራለሁ::

ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ከጊዚያዊ የገዥዎች ጭቆና ጋር ለዉድደር አይቀርብም፣ ለእኔ ዛሬ ኢትዮጵያዊዉ ህዝብ የገባበት የድህነት አረንቁዋና የስልጣኔ ሁዋላ ቀርነት ከኢትዮጵያዊ ማንነቴ ጋር ለንፅጽር መቼም አይቀርብም:: ሁሉም ወገን ግን ለምን እንዲህ አልሆነም የሚል የሞኝ ክርክር አላነሳም:: ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ ነዉና ::

ኢትዮጵያዊነት የእኔ ማንነት አይደለም ፣ ኢትዮጵያዊነት ባጣ ቆዬኝ ማንነቴ ነዉ እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት የምደራደርበት ማንነቴ ነዉና አንተም ብትሆን ጥላዉ/ጣለዉ ለሚለኝ ወገን ግን መልሴ እሪያዎች እንዳይረግጡብህ እንቁህን ጠብቅ ተብሎአልና ወደ ወይን ማሳዬ አትግባ የወይን እርሻዬንም አትርገጥ የሚል መልስ አለኝ:: እኔ ማንንም አልተጫንኩምና ወደኔ ማንነትም ማንም ዘሎ መምጣት የለበትም:: በእኔ የማንነት ምርጫም ማንም መከፋት የለበትም:: እኔ በማንም ምርጫ እንደማልከፋ ሁሉ:: እናም ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶዬ በማለት ለማንነቴ አክብሮቴን አገልጻለሁ:: ኢትዮጵያዊነት :- የእኔ ናርዶስ ሽቶዬ::

ልክ እንደ እኔ ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ ብላችሁ በማንነታችሁ ለምትመኩ ሁሉ ይህን መርህ የጋራ መርህ እንድናደርገዉ እጠይቃለሁ:: ይህ መርህ ቀላል ነዉ:: ሁሌም የሚባል ነዉ:: ሁሌም በልባችን ተቀርጾ የሚኖር ነዉ:: ኢትዮጵያዉያንን እና ኢትዮጵያዊነትን በአንድነትና በእኩልነት የምናፈቅርበት ብሎም ለሰዉ ልጅ ሁሉ ያለንን የማይናወጽ አክብሮት የምንገልጽበትም ነዉ:: እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትን የሚያንኩዋስሱና የሚያጣጥላሉ ሰዎች ሲገጥሙን የምንመልስላቸዉም መልስ ነዉ::

እኛ ኢትዮጵያዊነትን የሚጠሉ ወገኖቻችን የመረጡትን ማንነታቸዉን እንዲተዉ/እንዲለዉጡ አንጠይቃቸዉም/አንለምናቸዉምም:: በሂደት ምናልባትም ወደ እኛ ህሳቤ ከተሳቡ ደስ ይለናል:: አሁንም እንወዳቸዋለን ደግሞም ወደኛ ህሳቤ ከተሳቡ ይበልጥ እንወዳቸዋለን:: አሁን ግን የእኛን ማንነት በድፍረት የምናራምድበት መርህ ያስፈልገናል:: ይህም መርህ የሚከተለዉ ነዉ:: እሱም ኢትዮጵያዊነት- የእኔ ናርዶስ ሽቶ የሚል ነዉ:: እናም እንናገረዉ ፣ በድረገጾቻችን ላይ እንጻፈዉ ፣ በዚህ ህሳቤ ለሚሳቡም ሆነ ለማይሳቡ ሁሉ እናካፍለዉ:: ኢትዮጵያዊነት:-የእኔ ናርዶስ ሽቶ:: ይህን መርህ ማንንም ሳንሳደብ፣በማንም ላይ ሳንጮህ በስፋትና በጥልቀት እናራምደዉ:: ኢትዮጵያዊነት : የእኔ ናርዶስ ሽቶ::

ሸንቁጥ አየለ (shenkutayele@yahoo.com)

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.