ፕሮፌሰር መሥፍን ንስሓ ይገቡ ይሆን?
ፕሮፌሰር መሥፍን ንስሓ ይገቡ ይሆን?
ኢሳት ሰሞኑን እያቀረበው ያለውን ከፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም ጋር የተደረገውን ረዘም ያለ ውይይት እያዳመጥኩ ነው። ውይይይቱ ደስ ይላል፣ ፕሮፌሰር ከሚያነሱዋቸው ታሪኮችም በመነሳት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ዓይነት ደስ የሚል ማህበረሰብ እንደነበር እና በዚህ ዘመን ያለነው ኢትዮጵያውያን ደግሞ መከራችንን እያየን ያለነው ምን ስላጣን እንደሆነ በከፊልም ቢሆን ፍንጭ የሚሰጥ ነው።
ከዚያ በተረፈ ግን ውይይቱ ውስጥ ብዙ የሚያስከፋ ነገር አግኝቼበታለሁ፤ እንዲያውም ፕሮፌሰር መሥፍንን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ እየታዘብኩ ነገር ግን በውስጤ ይዤ የቆየሁትን ቅሬታ ጠንክሮ እንዲወጣ እና ምክንያቱንም ለመጠየቅ ያስገደደ ውይይት ነው። አስቀድሜ ግን ለአንባቢዎቼ አንድ ነገር ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፣ እኔ ፕሮፌሰር መሥፍን ላይ በፍፁም ጥላቻ የለኝም፣ አከብራቸዋለሁ፤ እንዲያውም በደርግ የመጨረሻዎቹ የቀውስ ዓመታት ወደ ወደ ጉርምሥና መጥተን፣ ከተማሪነት ወደ ጎልማሳነት የተሸጋገርንበትን ዕድሜ ደግሞ በሃያ ዓምስቱ የወያኔ የዝሙት እና የውርደት ዓመታት ውስጥ ለባከንን ዜጎች፡ ፕሮፌሰር መሥፍን ታላቅ መድህን የሆኑ ሰው ናቸው። እንደ ፕሮፌሰር መሥፍን ያሉ ጥቂት ጠንካራ ዜጎች በመኖራቸው ነው የወያኔ ታሪክን የመበረዝ ሴራ እንደጭስ በንኖ የጠፋው እና የኢትዮጵያውያን የሃገርነት ተስፋ ሕያው ሆኖ ሊቆይ የቻለው። ከዚያ በተረፈ
የፕሮፌሰር መሥፍን ነገር ለማመን በጣም ይከብዳል፣ ያስደነግጣልም፤ የሚናገሩት ነገር ሁሉ በተቃርኖ የተሞላ ነው። አንድ ቡድን እና ቤተሰብ ላይ ያነጣጠረ እና ለረጅም ጊዜ ውስጣቸው የተቀበረ ጥላቻ እንዳለ ይሰማኛል። ፕሮፌሰር መሥፍን ራሳቸው በግልፅ እንዳስቀመጡት፤ እርሳቸው ያደጉበት ዘመን ተራው ሕዝብ “…ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ፡ የገደለሽ በላ…” ወዘተ እያለ፡ እያንዳንዱን ችግር “…ሃይለሥላሴ አርበኞችን አግልለው ባንዳዎችን ስለሾሙ ነው…” በሚል ስንኩል መነጽር በኩል ይመለከት የነበረ ነው ።
በርግጥም ኃይለሥላሴ ባንዳዎችን እና ስድተኞችን ቢሾሙም፡ ዓላማቸው ግን እውነተኛ አርበኞችን ለማግለል አልነበረም፤ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ “…ኢጣሊያ እና ሌሎቹ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃይሎች ስለ ኢትዮጵያ ምን ጻፉ፣ ከኢትዮጵያ ጀርባስ ምን ተዋዋሉ?” የሚለው ጥያቄ ነበር፤ ስለዚህም ፈረንሳይኛ፡ ጣልያንኛ፡ አረብኛ እና እንግሊዝኛ የሚናገሩ ሰዎች በጣም ይፈለጉ ነበር፤ በወቅቱም እነዚህን ቋንቋዎች ይናገሩ የነበሩት ጥቂት የተማሩ ኢትዮጵያውያን የነበሩ ቢሆንም፣ ብዙዎቹ ግን ለጣልያን ያደሩ ትግሬዎች፡ ኦሮሞዎች፡ አደሬዎች፤ ሱማሌዎች እና ኤርትራውያን ነበሩ።
እነዝያ ባንዳዎች ደግሞ ዝም ብሎ ተራ ግለሰቦች አልነበሩም፣ ጣልያን ኢትዮጵያን በዘር እና በሃይማኖት ለመከፋፈል እና ለመበታተን ባቀነባበረው ሴራ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ነበሩ። በመሆኑም ሹመቱ የማባበል እና ግለሰቦቹ ኢትዮጵያዊነት እንዲሰማቸው የማድረግ ዓላማም ነበረው። እኔን የሚገርመኝ ግን እነዚያ ባንዳዎች ለሃገሪቱ ከባድ አደጋ እንደነበሩ ኃይለሥላሴ ከማንም በላይ አጥብቀው የተረዱትን ያህል እርሳቸው ላይ አቃቂር የሚያወጡት ተምረናል ባዮች አንዳችም ያልተገለጸላቸው መሆኑ ነው።
ዞሮ ዞሮ ኃይለሥላሴ የፈሩት አልቀረም፡ ትግሬዎቹ እና ኦሮሞዎቹ የዘር ፖለቲካ ማጠንጠን ጀመሩ፤ ንጉሡ ጭሰኝነትን እና ፈውዳላዊ የመሬት ባለቤትነትን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ የጀመሩትን ፕሮግራም መና ያስቀሩትም እነዚሁ ጎሰኛ ባንዶች ነበሩ። አንድ እንግሊዛዊ የታሪክ ፀሓፊ በግልፅ እንዳስቀመጠው “…ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊውዳላዊ የመሬት ሥርዓትን ለማስቀረት እና፣ ግለሰቦች መሬትን ተጠቅመው ለመንግሥት ብቻ ግብር የሚከፍሉበትን እንዲሁም፡ እያንዳንዱ ጠቅላይ ግዛት በሚሰበስበው ግብር፡ መሠረተ ልማቶችን የሚያስፋፋበትን እቅድ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረ ነበር፡ ነገር ግን ብዙ መሬት የያዙ እና በጎሳ ትሥስር የተመሰረቱ ባላባቶች ከፍተኛ ተቃዋሚ ሆኑ፣ በተለይም በባሌ እና በኦጋዴን ነገሩ መልኩን ቀይሮ ወደ ከፍተኛ ዓመጽ ተቀጣጠለ፣ ቀስ እያለም ወደ ጎሳ እና ሃይማኖታዊ ፍጥጫ ተቀየረ፡ በዚህም የተነሳ ኃይለሥላሴ በጉዳዩ ሊገፉበት አልቻሉም…”
ይህ ታሪክ በከፊል በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ላይ በግልፅ የሠፈረ ነገር ነው፣ የሚያሳዝነው ግን አሁን በቅርቡ በወጣው አዲሱ እትም ላይ ግን፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ወያኔ እና ኦነግ ከደረሱት ተረት ጋር እንዲመሳል ተደርጎ “ተሻሽሏል”። የባሌና የአርሲ ዓማጽያን እንዲያውም በዋቆ ጉቱ እየተመሩ ከሶማልያ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ወግተዋል፤ ይህንን ታሪክም በደርግ ጊዜ ደግመውታል፤ የሚያስቀው ነገር ግን ሱማሌዎቹ ተመልሰው “…ጋላ…ጋል…” እያሉ መጫወቻ ሲያደርጓቸው እንደገና ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ተመልሰው፡ ከዚያ በፊት ሲሰድቡት እና ሲወጉት የነበረው ክርስቲያኑ ሕዝብ በክብር ተቀብሎ እና መኖሪያ ቤት ሰርቶ ከመሃሉ በሠላም እንዲኖሩ አደረጋቸው። የነዚህን ከሃዲዎች ታሪክ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።
እንግዲህ እነዚያን ሁሉ እንቅፋቶች ችለው ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና እንድትራመድ መሠረት የጣሉትን ንጉሥ ነው እንግዲህ ፕሮፌሰር መሥፍን አንዲትም እንኳ የምሥጋና ቃል የነፈጓቸው። እስቲ ይታያችሁ፣ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለፈጠሩት ግርግር ትኩረት ሰጥተው እትምህርት ቤቱ ድረስ እንደመጡ ከነገሩን በኋላ ፡”…ሃይለሥላሴ ስለራሳቸው ክብር እንጂ ስለሕዝብ እና ስለሃገር ክብር ደንታ አልነበራቸውም…” ይሉናል። ትንሽ ወረድ ብለው ደግሞ “…ንጉዊው ቤተሰብ ሕዝቡ እንዲማር ይፈልግ ነበር፣ ያንንም ለማሳካት ባገሪቱ ጥሩ ጥሩ ትምህርት ቤቶችን ከመክፈት ጀምሮ፡ብዙ ገንዘብ እያወጡ ወጣቶችን ወደ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች እየላኩ እንዲማሩ አድርገዋል፣” ካሉ በኋላ “…ነገር ግን እነርሱ መማር እና መለወጥ አይፈልጉም ነበር…” በማለት የካቡትን መልሰው ይንዱታል።
እኔ የምለው፡ መማር እና መለወጥ የማይፈልግ ነው እንዴ “…ተማሩ!” እያለ ዜጎቹን ሌት ተቀን የሚመክረው እና የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ የያዘን አንድ ተራ ዜጋ ቤተመንግሥት ድረስ በክብር እየጠራ የሚሾመው እና የሚሸልመው? ትምህርት እና ለውጥ የማይፈልግ ንጉሥ ነው እንዴ በየኮሌጁ እየዞረ ተማሪዎችን በግል የሚያነጋግረው እና የማበረታቻ ሥጦታ የሚያበረክተው?
ከሁሉም በላይ ፕሮፌሰር መሥፍን በአማራ ላይ እና በንጉሳውያኑ ቤተሰብ ላይ ያላቸውን አመለካከት አስፈሪ ያደረገብኝ፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይካሄድ ስለነበረው የተማሪዎች ዓመፅ እና ስለመሪዎቹ ማንነት የተናገሩት ነው፤ ፕሮፌሰር በግልፅ እንዳስቀመጡት የወቅቱ አፍራሽ ዕንቅስቃሴ ቀንደኛ መሪዎች ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች እና ኤርትራውያን ሲሆኑ፡ ለጥይት እና ለዕሥራት የሚማገደው ግን አማራው ነበር ።
ፕሮፌሰር ቅን እና ገለልተኛ ቢሆኑ ኖሮ ይህችን ጉዳይ እንደዋዛ ነካ ብቻ አድርገው አያልፏትም ነበር። ይህን ጥርጣሬዬን ይበልጥ የሚያጎላው ደግሞ፡ ራሳቸው ፕሮፌሰር መሥፍን ይመሩት በነበረው መርማሪ ኮሚሽን ውስጥ አባል የነበሩ ኦሮሞዎች፡ ትግሬዎች እና ኤርትራውያን ከደርግ ጎን ተሠልፈው እነዚያን የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች ለማስገደል ከፍተኛ ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸው ማረጋገጣቸው ነው። ነገሩ እንዲህ ግልፅ ሆኖ ሳለ እንኳ፣ ፕሮፌስር መሥፍን የነባሮ ቱምሳ እና የነበረከት ኃብተሥላሴን ዓማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በግልጽ ቃላት ለመናገር አልፈለጉም፡ ወይም አልደፈሩም።
ሌላው ፕሮፌሰር መሥፍን ላይ ያለኝን ጥርጣሬ ያጠናከረው ጉዳይ ደግሞ ፡ ራሳቸው በግልፅ ያስቀመጡት የግል ባህሪያቸው ነው፤ እንደነገሩን ከሆነ ፕሮፌሰር መሥፍን ሃይማኖተኛ ይሁኑ እንጂ፣ ገና ከልጅነታቸው ሕግን ተጻራሪ እና ለበላዮቻቸውን ያለመታዘዝ እና የመናቅ እንዲሁም ቂመኛ ባሕሪ ነበራቸው። እስቲ አስቡት፣ በዚያ በየዋህ ዘመን በሴንጢ የሰው ሆድ፡ ያውም የዕድሜ እኩያውን የሚወጋ ልጅ ነበረ ሲባል ትንሽ አያስፈራም? ያም አልበቃ ብሎ፡ በዕድሜ የእናትን ዕኩያ የሚሆኑ(ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ላይ ያፌዙትን አስታውሱ) ያውም በሃገር የተከበሩ እመቤት ላይ ማሾፍ እና በአሽሙር መዝለፍ የሚያደፋፍር ባሕሪ፡ እንኳን በዚያ በደጉ ዘመን በዚህ “ሥነምግባር የማያውቅ” በሚባለው ትውልድ ውስጥ እንኳ ያን ያህል የጎላ አይደለም።
እኔ በበኩሌ፡እነዚህ ባሕርያት ፕሮፌሰር መሥፍንን ያመሰግንናቸውን ያህል(እንዲያውም በበለጠ) እንድንከፋባቸው የሚያደርጉ ከባባድ ጥፋቶችን አስከትለዋል እያስከተሉም ነው ብዬ አምናለሁ፤ ይባስ ብሎም እንደነ ሌንጮ ለታ ያሉ ኢትዮጵያን ያተራመሱ ጎሰኞች ጥፋታቸውን ለማመን ዳር ዳር በሚሉበት ወቅት፡ እንደገና ወደ ኋላ ተመልሰው “ልክ ነበርን!” እንዲሉ የሚያበረታታ ነው።
እነዚህ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ፡ ባለችኝ መጠነኛ ዕውቀት የፕሮፌሰር መሥፍን የልጅነት እና የወጣትነት ዘመን ባህሪ ከትክክለኛ የልጅ ባህሪ እንደማይመደብ እና በዚያም የተነሳ ስለ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና ስለ አማራ ሕዝብ ያላቸው አመለካከት በጥርጣሬ መታየት እንዳለበት ለማስረዳት እሞክራለሁ።
እኔ እንደተረዳሁት፡ የፕሮፌሰር መሥፍን ልጅነት በሕግ እና ሥርዓት ተጻራሪ ባሕርያት እና ዓመለ ብልሹነት (Oppositional Defiant Disorder and Conduct Disorder)የተሞላ ነበር። እንደ አሜሪካ ሳይኪያስትሪስቶች ማህበር የኣዕምሮ ሕመሞች እና የባህሪ ችግሮች ዝርዝር (DSM-IV Diagnostic and Statistical Manual)መሠረት፣ የዚያ ዐይነት ባህሪ ያላቸው ልጆች
በቀላሉ ይናደዳሉ፣ ከአዋቂዎች ጋር ይጨቃጨቃሉ፣ በአዋቂዎች/ትላልቅ ሰዎች የተሰጡ መመሪያዎችን ይጥሳሉ፣ ሆን ብለው ሰውን ያናድዳሉ፣ ለሁሉም ነገር ሌሎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፣ የጦር መሳርያ ወይም ሥለት ባለው ነገር ሰው ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ፣ይሳደባሉ፣ ብሶተኛ ናቸው፣ ብስጩ እና በጥላቻ የተሞሉ እንዲሁም ቂመኛ ናቸው፤ እነዚህ ባህርያትም በትምህርት፡ በሥራ እና በማህበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ እንቅፋት ይሆናሉ።
.loses temper, argues with adults, defies adult rules, deliberately annoys, blames others,
touchy/easily annoyed, angry and resentful, spiteful or vindictive
• behaviour causes significant impairment in social, academic or occupational functioning
• aggression to people and animals (bullying, physical fights, use of weapons,
• disturbance causes clinically significant impairment in social, academic or occupational functioning
እንደ እኔ ምኞት ቢሆን፡ ፕሮፌሰር መሥፍን ይህን ችግራቸውን ተረድተው ንስሕ ይገባሉ፣ ልክ እንደርሳቸው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን መንግሥት ያለጥፋቱ ሲወነጅሉ እና አመፅ ሲያነሳሱ የነበሩ፣ ነገር ግን ሁኔታዎችን ረጋ ብለው ከተመለከቱ በኋላ ከባድ ሥህተት እንደፈፀሙ አምነው ይቅርታ እንደጠየቁ ጓደኞቻቸው ይህችን ጉድፍ ከራሳቸው ላይ ያነሳሉ።