በጀዋር አመለካከትና ፍልስፍና ዉስጥ

በጀዋር አመለካከትና ፍልስፍና ዉስጥ ምን የተለዬ ነገር ተገኘበትና እና ነዉ አሁን በጀዋር ላይ ጅራፍ ማጮህ የበዛዉ?

ሸንቁጥ አየለ

ጀዋር መሃመድ ጥንቱንም የሚለዉ ኦሮሞነት ቀዳሚዉ ማንነቴ ነዉ ነዉ:: ይሄን ማንነቴ ሳይረጋግጥ ኢትዮጵያዊነትን አልቀበልም ይላል:: ይሄ አባባል ሁሉም ብሄረተኛ ፖለቲከኞች የሚዘምሩት መዝሙራቸዉ ነዉ:: የትግራይ የብሄረ ፖለቲካ ህሳቤ አራማጆች የኢትዮጵያ ህዝብ ጆሮ እስኪደነቁር የዘመሩት ይሄን ነዉ::ሁሉም የኦሮሞ ብሄረተኞች የሚዘምሩት ይሄንን ነዉ:: ቅኝ ተገዛን ሞትን ተቀነጠስን ብለዉ ከኢትዮጵያ የተነጠሉት ኤርትራዉያን ፖለቲከኞችም የዘመሩት ይሄንኑ ነዉ::

እያንዳንዱን የብሄር ፖለቲካ መርህ ዉስጥ የገባ ሰዉ ከዚህች መርህ ዉጭ የሚናገራት አንዳችም ነገር የለችዉም:: ሌላዉ ቀርቶ በጣም ጥቂት የህዝብ ቁጥር ያላቸዉ የሀረሪ ብሄረሰብ ፖለቲከኞች እንኳን ይሄንኑ አባባል ነዉ የሚራቀቁበት:: ሀረሪነቴ መጀመሪያ ማንንነቴ ሲሆን ኢትዮጵያዊነት ግን ሁለተኛ ማንነቴ ነዉ ሲሉ ይቀናጣሉ:: አንድ ቀበሌ የማይሞላ ሰፈር ይዘዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን ከክልላቸዉ አስተዳደር አግልለዉ ሀረሪ የተባለችዉን ትንሽ ክልል ለራሳቸዉ ጎሳ ብቻ እንድትመች አድርገዉ በግል ይዞታነት መያዝ ዋናዉና ተቀዳሚ መርሃቸዉ ነዉና ሀረሪነቴ ቀዳሚ ማንነቴ ሲሉ ይዉረገረጋሉ::

እንግዲህ ወያኔን በመታገል ሂደት ዉስጥ እየተሳተፉ ያሉ እንደ ጀዋር ያሉ ፖለቲከኞች ከወያኔ መርህ የተለዬ ፖለቲካ አይከተሉም:: የወያኔም ሆነ የጀዋር መርህ አንድ ነዉ:: የብሄር ፖለቲካ ነዉ::የብሄር ፖለቲካ መርሁ ደግሞ የኔ ማንነት በቀዳሚነት ብሄሬ ሲሆን ኢትዮጵያዊነት ሲያሰኘኝ የምለብሰዉ ሲያስጠላኝ አዉልቄ የምጥለዉ ማንነት ነዉ ብለዉ ያምናሉ::ለዚህም ሀሳባቸዉ ማደላደያነት የወያኔን ህገመንግስት አንቀጽ 39 ኝን ሁሉም በጋራ ይቀበላሉ::

በአክራሪ ኢትዮጵያዊነት ሲወቀሱና ሲከሰሱ የነበሩት የአንድነት ሀይሎች ደግሞ ያለኝ አንድ ማንነት ነዉ እሱዉም ኢትዮጵያዊነት ነዉ ሲሉ ነበር:: በለዘብተኛ ኢትዮጵያዊነት ሲፈረጁ የነበሩ የአንድነት ሀይሎች ጽንፍ ብሄረተኝነት ላይ የረገጡትን እና ጽንፍ አንድነት ጎራ ላይ የረገጡትን ሀይሎች ለማሳሳብ ሲማስኑ ነበር:: እንዲህ አይነት የማንነት ፖለቲካ ላይ ቀድመን ከተንጠለጠልን የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን ዉስብስብ ያደርገዋል ሲሉም ነበር:: እናም ብሄረተኞችም : የአንድነት ሀይሎችም አብረዉ መስራት እንደሚችሉ ለማረጋገጥ የማደራደር ስራ ሲሰሩ ነበር:: ዋናዉ ለዲሞክራሲ መገንባት መደላድል ሊፈጥር የሚችለዉን ወያኔን መጣል ወይም አስገድዶ ወደ ድርድር ማምጣት የሚለዉን ሀሳብ ሲያራምዱ ነበር::

ከጥቂት ወራት በፊት የኦሮሞ ህዝብ በወያኔ ላይ ተቃዉሞዉን መግለጽ ሲጀምር የተስተዋለዉ በጋራ ወያኔን የመጣል መንፈስ ታላቅና ተስፋ ሰጭ ከመሆኑ የተነሳ የማንነት ጥያቄዎች ወደጎን ተገፍተዉ ለዲሞክራሲ መደላድል የሚሆነዉን ወያኔን በጋራ የመጣል የቤት ስራ ለመስራት መልካም ጅምር ህዝቡ ራሱ በማህበራዊ ሚዲያ ጀምሮ ነበር::ሀሳቡን ማንም ፖለቲከኛ ሳያነሳዉ ህዝቡ እራሱ በጋራ ወያኔን መታገል የሚለዉ ህሳቤ በደንብ አስኪዶት ነበር::

ይሄን የህዝብ ስሜት ተከትሎ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር የሆነዉ አቶ ነዓምን ከጀዋር ጋር ያደረገዉ ድርድር ብዙ አዎንታዊ የስሜት መስተጋብርን የፈጠረ ጉዳይ ሆኖ ነበር:: ታላቅ መነቃነቅን የፈጠረዉ የኦሮሞ ተማሪዎች እና የኦሮሞ ህዝብ አመጽም ወያኔን ብርክ ሲያሲዛት የኢትዮጵያ ህዝብም አብሮ መዘመር ጀምሮ ነበር::በዚያ ሰሞን የተሰተዋለዉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በጣም ድንቅ ነበር::

በመሀሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዋሽንግተን ላይ ዱብ እዳ ይዘዉ መጡ:: ጀዋርን እንደ አራስ ነብር ያስቆጣ የአንድነት ጽንሰ ሀሳብን ዱብ አደረጉ:: “የብሄር ፖለቲካ/የማንነት ፖለቲካ/ ለዲሞክራሲ ግንባታ እንቅፋት ነዉ:: እኔ በግሌ መሆን አለበት ብዬ የማምነዉ የዜግነት ፖለቲካ ነዉ:: የዜግነት ፖለቲካ ለዲሞክራሲያዊነት ብቸኛዉ አማራጭ ነዉ::” አሉ::

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ቆፍጠን ብለዉም ኢትዮጵያን በሀገርነት የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ድርድር አይደለም የያዝነዉ:: ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ የማድረግና ያለማድረግ እንጅ” ፍርጥ አድርገዉ ተናገሩት:: እንግዲህ እንዲህ አይነት የጸና የኢትዮጵያዊነት ንግግር ሲሰሙ ሁሉም ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ይደነግጣሉ:: ጀዋርም ከመደንገጥም አልፎ “አዎቆም እነዚህ የማይታመኑ ሰዎች ጋር አብረን ለመስራት መሞከራችን… ” ሲል ብዙ ነገር የተናገረዉ ከቀደመዉም አሁን ካለዉም መሰረታዊ እምነቱ ተነስቶ ነዉ:: በርካታ የአንድነት ሀሎችን በደስታ ያስጨበጨበዉ የፕሮፌሰር ብርሃኑ ንግግር ለጀዋር እሬት እና ኮሶ ሆኖ ነዉ የቀረበዉ:: :

እናም እንግዲህ ወደ መሰረታዊ ጥያቄአችን እናምራ:-በጀዋር አመለካከትና ፍልስፍና ዉስጥ ምን የተለዬ ነገር ተገኘበትና እና ነዉ አሁን በጀዋር ላይ ጅራፍ ማጮህ የበዛዉ? የሚለዉን ጥያቄ እናንሳ:: መልሱ ምንም የተለዬ ፍልስፍና: አመለካከት እና መርህ አልተገኘበትም:: ትናት ከጀዋር ጋር አብሮ ለመስራት ድርድር ዉስጥ የተገባዉ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ኦሮሞ : አማራ ሳይል ወያኔ ላይ እንዲሰፍርባት የሚያበረታታ መንፈስ የተፈጠረዉ ጀዋር ከነአስተሳሰቡ የአንድነት ጎራዉም ከነ አስተሳሰቡ በጋራ ለመሰለፍ በመነሳቱ ነዉ::

ጀዋር ነገም ያዉ ነዉ:: አስተሳሰቡ አይለወጥም:: ይሄ ማለት ግን ወደፊት ድርድር ዉስጥ ገብቶ አስተሳሰቡን የሚያስገብርለት ሁኔታ አይኖርም ማለት አይደለም:: የጀዋርን አስተሳሰብ ማስገበር የሚቻለዉ ደግሞ ጀዋርን ቀጥታ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ፊት ለፊት እንዲፋጠጥ በማድረግ ነዉ:: ያ ሁኔታ የሚፈጠረዉ ደግሞ ወያኔ መድረኩን ስትለቀዉ ነዉ:: ጀዋር የሚያነሳቸዉ በርካታ ሀሳቦች የኦሮሞ ወጣቶችን የማነሳሳት አቅም እንዳላቸዉ ሁሉ ከጥቂት ቆይታ ብኋላ በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ጀዋርን በብዙ ጥያቄ ቀስፈዉ መያዛቸዉ አይቀርም:: ለምሳሌ ጀዋር ኦሮሞን ወደ እስልምና ማንነት አስጠግቶ የማሰብ ግንዛቤዉ በፍጥነት በብዙ ሚሊዮን ኦሮሞ ክርስቲያኖች ጥያቄ ዉስጥ መግባቱ አይቀርም:: የዲሞክራሲ ግንባታም የሚጀምረዉ እንዲህ ነዉ::ጀዋርም ሁለት ምርጫ ይኖረዋል:: ወይ ሚዛናዊ ሆኖ ወደ ህዝቡ ህሳቤ መዉረድ አለዚያም በህዝቡ መተፋት::

ጀዋር ሚዛናዊ ሆኖ ወደ ህዝቡ ሲወርድ ታዲያ የኦሮሞ ህዝብ በዋናነት የሚያነሳዉ ጥያቄ የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ይሆናል:: ይሄ ለበጣ አይደለም::ኢትዮጵያን በደንብ ከማጥናትና ከማወቅ የመጣ እመነት ነዉ:: የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ቢነጠል ምን አይነት ጉዳት እንደሚደርስበት እያንዳንዱን ሰዉ መጠዬቅ ቀላል ነዉ:: ኦሮሞዉ ከሰሜን እስከ ደቡብ በስፋት የተንጣለለዉ ኢትዮጵያ ሰማይ ስር ይገኛ:: ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ የኦሮሞ መኖሪያ ነች:: እናም ኢትዮጵያ ወደ ልዩ ልዩ ክልል መቆራረስ ስትጀምር ምን እንደሚከተል የኦሮሞ ህዝብ ጥንቅቅ አድርጎ ያዉቃል::

ኢትዮጵያ ብዙ ቦታ መከፋፈል ስትጀምር አማራ ኦሮሚያ የተባለዉን ሰፊ ቦታ ጠቅልሎ ለኦሮሞ እንደማያስረክብ የኦሮሞ ህዝብ ያዉቃል:: ኢትዮጵያ ስትከፋፈል የሲዳማ ጦረኞች እጃቸዉን አጣጥፈዉ ዛሬ ወያኔ የሰጣቸዉን መሬት ብቻ ይዘዉ እንደማይቀመጡ ሁሉም ያዉቃል:: ኢትዮጵያ ብትንትን ስትል ሶማሌዉ እስከ መሃል ሸዋ ከባሌም እስከ አርሲ ድንበር ድረስ ኢትዮጵያን ጠቅልሎ ሊወስዳት እንደሚነሳ ሁሉም ያዉቃል::

ደርሶ መወሻሸት ካልሆነ በቀር የኢትዮጵያ ሰዉ እኩል ጦረኛ ነዉ:: ኢትዮጵያ የብዙሃን ነገድ ሀገር በሚለዉ መጽሀፋቸዉ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪ እንዲህ ብለዋል “ኦሮሞዎችም አማሮችም የባህል ልዩነት ያላቸዉ ይመስላል እንጅ የሁለቱም ባህል አንድ ነዉ:: የሁለቱም ባህል እኩል ጦረኛ ነዉ::” የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን በደንብ ጠንቅቆ ያዉቃል:: እናም የኢትዮጵያ ሰዉ የሚፈልገዉ እና የሚያዋጣዉ ታላቂቱ ኢትዮጵያ ሳትበታተን በአንድነት ዲሞክራሲያዊ መብቱ የሚጠበቅበት ሁኔታ ቢፈጠርለት ነዉ:: እናም የኦሮሞም ህዝብ እምነቱ ይሄዉ ነዉ::

እንግዴህ የጀዋር መሃመድ ወደ ተጠይቅ በህዝብ ግፊት ተስቦ መምጣት የሚጀምረዉ እዚህ ላይ ነዉ:: እናም ትናንትም ዛሬም ጀዋር አስተሳሰቡ አንድ ነዉ:: ነገም አስተሳሰቡ ያዉ ነዉ::ግን የኦሮሞ ህዝብ ጀዋርን አስገድዶ ወደ ተጠይቅ እንደሚያመጣዉ ምንም ጥያቄ የለዉም::

ስለሆነም ተቃዋሚ ድርጅቶች አሁን ጀዋር ላይ ወንጭፍ ማስወንጨፍ : ድንጋይ መወርወር ትተዉ የኦሮሞ ህዝብ እና ተማሪ የጀመረዉን ትግል ወደ ሀገራዊ ደረጃ ለማሳደግ ብሎም ለዲሞክራሲያዊ ድርድር የሚሆነዉ መድረክ እንዲፈጠር ወያኔ ከመንበሯ እንድትለቅ ወይም ወደ ድርድር እንድትመጣ በጋራ መስራቱ ላይ ማተኮሩ ወሳኝ ነዉ::

የብሄረተኝነት ፖለቲካ ኢትዮጵያ ዉስጥ እዉነት ሆኖ ሀገሪቷን አስጨንቋት ያለ ነገር እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱን ብሄረተኛ ሀይል ሳያገሉ የኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሀሳብን ግን አስፍቶና አጥልቆ እየሰበኩ ወያኔን ወደ ድርድር ለማምጣት ወይም ለማዉረድ የሚደረገዉ ትግል ላይ ግን በጋራ መስራት አማራጭ የለዉም::

ይሄ ሀሳብ ወደ ጽንፍ ለሚገሰግሱ ወገኖች የማይዋጥ ቢሆንም ሌላ ምርጫ የለም:: ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መፈጠር የድርድር መድረክ እስኪፈጠር ድረስ በጋራ መቆም አማራጭ የሌለዉ ምርጫ ነዉ:: ይሄን አባባል የሚያስረግጥልን አራት ምክንያት ነዉ :- አንደኛ ወያኔ የህዝቡን አንድነት ተመልክታ ወደ ድርድር ለመምጣት የስነልቦና ዝግጅት እንድታረግ ስለሚያግዝ:: ሁለተኛም የተቃዉሞዉ ጎራ ጉልበት እንዲጎለብትና አይዞህ አይዞህ የሚለዉን ስሜት ለመቀስቀስ ብሎም ህዝቡ ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆን ስለሚያደርግ:: ሶስተኛም በጋራ መስራት ሂደቱ ዉስጥ የሚፈጠረዉ መስተጋብር ወሳኝ

ሀገራዊ የመግባቢያ ቀዳዳ ስለሚፈጥር ብሎም አገር በጋራ ለማቆም ስለሚያግዝ:: አራተኛም ነገ የሚመጣዉ ለዉጥ የጋራ እንደሆነ ሁሉም አምኖ እንዲቀበለዉና በቀጣይነት የሚፈጠሩ የተቃዉሞ ትግሎች እንዳይኖሩ ስለሚያደርግ ነዉ::

በመሆኑም በጀዋር አመለካከትና ፍልስፍና ዉስጥ ምን የተለዬ ነገር ተገኘበትና እና ነዉ አሁን በጀዋር ላይ ጅራፍ ማጮህ የበዛዉ? የሚለዉን ጥያቄ ምንም አዲስ ነገር የለም ብለን ከመለስን የሚቀጥለዉ ጥያቄ ለምን የተጀመረዉ ትብብር እንዲህ እንደጉም እንዲበን ተደረገ? የሚል ይሆናል:: የሚሰጠዉ መልስ ሁሉ ምንም አሳማኝ አይደለም:: ጀዋር እንዲህ አለ እንዲያ አለ የሚለዉ አባባል በቂ መልስ አይደለም:: ጀዋር የተናገረዉ ያንኑ የቀደመ እምነቱን ነዉ::ሌላ የተናገረዉ ነገር የለም::

ስለሆነም አሁንም ሁሉም የተቃዋሚ ሀይልን ለማስተባበር እና በጋራ ለመስራት የሚደረገዉ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚለዉ ምክር የዚህ ጽሁፍ መቋጫ ነዉ:: ይሄ ጉዳይ እከሌን የመዉደድ ወይም የመጥላት ጉዳይ አይደለም:: የፖለቲካዉን እዉነት መቀበል ብሎም ለቀጣይ የዲሞክራሲ ቀመር ሀገራዊ መደላድልን ለመፍጠር የሚደረግ የስሜት: የሀሳብ እንዲሁም የብዙ ነገሮች መስዋዕትነት ነዉ:: አሁን ጀዋር ላይ ድንጋይ በመወርወር በሚገባ ሁኔታ የተቀጣጠለዉን የኦሮም ህዝብ የትግል መንፈስ ላለመጉዳት መቆጠብ ተገቢ ነዉ::

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.