የሙስሊሞች ወደ ሃበሻ (ኢትዮጵያ) መሰደድና ተቀባይነት ማግኘት

የመጀመሪያዉ የስሙሊሞች ወደ ሃበሻ ሀገር  ስደት  (ከኢትዮጵያን ሙስሊምስ ድረገጽ የተገኘ)

 

ወርሃ ሸዕባን- ሀበሻ እንግዳ አስተናጋጅነቷን ያረጋገጠችበት ከመካ ቀጥሎ የመጀመሪያው የዳእዋ ማረፊያና ከለላ መሆኗን ያስመሰከረችብት ወር ነው። ታሪኩን እነሆ…

…የአላህ መልእክት ከሠማይ ዘለቀ፤ ብርሀኑም ፈነጠቀ፤ መልእክተኛው ጥሪውን አንግበው ከተፍ አሉ።

ጥሪው የአንዳንዶችን ቤት ይነቀንቃል። በበደል የተገነባ ህይወታቸውን ያፈርሳል። ከተደበቁበት የክብር ምሽግ አውጥቶ ወደ ሰብአዊ እኩልነት ሜዳ ያጋልጣቸዋል። ስለዚህ መልእክቱን ያነገበና ወደዚያ ብርሀን የተጣራ ምንም ያህል ንጹህና እውነተኛ ሰው ቢሆን የእነዚህ ሰዎች ጠላት ነው። የተባበረ ኃይላቸው ይነባበርበታል። ይህ መከራ በተከተሉትና ወደርሱ በቀረቡት ላይም አይቀርም።

ጊዜው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነብይነት ከታወጀ አምስት አመት ሆኖ ነበር። ልክ የዛሬ አንድ ሺህ አራት መቶ አርባ አንድ አመት አካባቢ፤ እ.አ.አ. ልክ በ615 እንበለው።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ አላህ በመጣራታቸው፣ የጣኦት አምልኮን በመቃወማቸው፣ የማህበራዊ ሚዛኖችን ለማስተካከል እና ፍትህን ለማንገስ በመታገላቸው መከራን ይጋቱ ነበር። እርሳቸው ላይ ከሚደርሰው እንግልት ተጨማሪ ተከታዮቻቸው ለታላቅ አደጋዎች ይጋለጡ ነበር። ከሀዲያን ያስሯቸዋል። ይቀጧቸዋል። ይደበድቧቸዋል። በረሀብና ጥም ይፈትኗቸዋል።

በበረሀው ንዳድ የቀለጡ ድንጋዮች፣ እሳት፣ ጅራፍ፣ ሰይፍና የማረሻ ስለት ሳይቀር የቅጣት መሳሪያዎች ነበሩ። እነዚህ ምስኪን የንፁሁ መልእክተኛ ተማሪዎች የሚቀጡበት።

ይህ ሁሉ መከራ ኃይማኖታቸውን እንዲተዉ ለማድረግ ነው። ነብዩ ሀይል አልነበራቸውም። ተከታዮቻቸውን ከእነዚህ አረመኔዎች አደጋ መታደግ አይችሉም። የባልደረቦቻቸውን ጭንቅ ሲመለከቱና እዝነት የተሞላው ልባቸው መከራን መመልከት ሲሳነው “አላህ መፍትሄ እሰኪያመጣ ድረስ ወደ ሐበሻ ምድር ብትሄዱ መልካም ነው። በእርሷ ማንም የማይበደልበት ንጉስ አለ። የእውነት ሀገር ናት።” አሉ።

ይህም ይህንን የአላህ ንግግር ያጠነክራል፡-

يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّ أَرْضِي وَاسِعَةٌ فَإِيَّايَ فَاعْبُدُونِ ﴿٥٦﴾ كُلُّ نَفْسٍ ذَائِقَةُ الْمَوْتِ ثُمَّ إِلَيْنَا تُرْجَعُونَ ﴿٥٧﴾ وَالَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ لَنُبَوِّئَنَّهُم مِّنَ الْجَنَّةِ غُرَفًا تَجْرِي مِن تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا نِعْمَ أَجْرُ الْعَامِلِينَ ﴿٥٨﴾ الَّذِينَ صَبَرُوا وَعَلَىٰ رَبِّهِمْ يَتَوَكَّلُونَ ﴿٥٩﴾ وَكَأَيِّن مِّن دَابَّةٍ لَّا تَحْمِلُ رِزْقَهَا اللَّهُ يَرْزُقُهَا وَإِيَّاكُمْ وَهُوَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ ﴿٦٠﴾

“እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሠፊ ናት፤ (ብትቸገሩ ተሰደዱ)። እኔንም ብቻ ተገዙኝ። ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት። ከዚያም ወደኛ ትመለሳላችሁ።እነዚያም ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ከገነት በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ሰገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲሆኑ በእርግጥ እናሰፍራቸዋለን። የሠራተኞች ምንዳ ምንኛ አማረ! (እነርሱ) እነዚያ የታገሱ በጌታቸውም የሚመሩ ናቸው። ከተንቀሳቃሽም ምግቧን ለመሸከም የማትችለው ብዙ ናት። አላህ ይመግባታል። እርሱ ሠሚው አዋቂው ነውና።” (አል-ዐንከቡት 29፤ 56-60)

በዚህ በያዝነው የሻዕባን ወር ተሰቃይተው የነበሩት ሙስሊሞች ወደ ሐበሻ ምድር ተሰደዱ። በኃይማኖታቸው ላይ የመጣ ፈተናን ፈርተው…

ሽሽታቸው ወደ አላህ ነው። ይህም የመጀመሪያው ስደት ሆነ።

የሐበሻው ስደት ሰበቦች

ተመራማሪዎች ሙስሊሞች ወደ ሐበሻ ያደረጉትን ሒጅራ (ስደት) ሰበብ ምን እንደሆነ የተለያዩ ነጥቦችን ይጠቅሳሉ። ከነዚህ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

1. ኢማን ይፋ መሆኑ፡-

ወደ ኢስላም የሚገቡ ሰዎች መብዛታቸው፣ ኢማን ይፋ መሆኑ፣ የመካ ሠዎች ዋና የወሬ አጀንዳ እስልምና መሆኑ ሙስሊሞች ላይ ቅጣት እንዲበዛ አድርጓል። አል-ዙህሪይ ከዑርዋህ ይዘው በዘገቡት የሐበሻው ሒጅራ ወሬያቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡- “ሙስሊሞች ሲበዙ፣ ኢማን የወቅቱ ርእሰ-ዜና ሲሆን… የመካ ከሃዲያን የሆኑት ሙሽሪኮች በአላህ ባመኑት የጎሳ አባላቶቻቸው ላይ ቅጣት ማዝነብ ጀመሩ። ያስሯቸዋል። ይቀጧቸዋል። በኃይማኖታቸው ሰበብ ይፈትኗቸዋል። ይህ ሁኔታ አስከፊ ደረጃ ላይ ሲደርስ መልእክተኛው ላመኑባቸው ሠዎች ‘በምድር ላይ ተበተኑ’ አሏቸው። እነርሱም ‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ ወዴት እንሂድ?’ ብለው ጠየቁ። ‘ወደዚህ!’ ብለው ነብዩ ወደ ሐበሻ አመለከቱ።”

2. ከኃይማኖት ፈተና መሸሽ፡-

ሰዎቹ ሀገራቸውን ትተው የሚሸሹት በኃይማኖታቸው ሰበብ ከሚገጥማቸው አደጋ ለመሸሽ ነው። ይህ ምክንያት ትልቁ የስደታቸው ሰበብ ነው። ኢብኑ ኢስሐቅ እንዲህ ይላሉ፡- “የመልእክተኛው ባልደረባ የሆኑት ሙስሊሞች ወደ ሐበሻ ተሰደዱ። የተሰደዱትም በዲናቸው የሚገጥማቸውን ፈተና ለመሸሽ ነው።…”

3. ዳዕዋውን ከመካ ውጪ ለማሰራጨት፡-

ኡስታዝ ሰይድ ቁጥብ እንዲህ ይላሉ፡- “…ከዚህ በኋላ መልእክተኛው መልእክታቸውን የሚያሰራጩበት ከመካ ውጪ የሆነ ማእከል ፈለጉ። እምነት የሚጠበቅበትና ነጻነቱን የሚያገኝበት ማዕከል፤ መካ ውስጥ ከገጠመው በደልና ፈተና ርቆ የሚቆይበት መሬት፤ መልእክቱ በነጻነት የሚሰበክበት፤ አማኞች የሚጠበቁበት ማእከል! ይህ ነው እንደኔ ቀዳሚው የመጀመሪያው የሐበሻው ሂጅራ ሰበብ። ስደቱን ያከናወኑት ነፍሳቸውን ለማዳን ብቻ ነው የሚል እምነት ካለ መረጃን የተደገፈ አይመስለኝም። እንዲያ ቢሆን ኖሮ ከቤተሰቦቻቸው ጥበቃ ማግኘት የሚችሉ የታላላቅ ቤተሰቦች ልጆች ተሰደው ጥበቃን የሚሹና ትልልቅ የቅጣት አጋጣሚዎችን ያስተናገዱት ድሆችና ባሮች ሳይሰደዱ አይቀሩም ነበር። ተቃራኒው ነበር የሆነው። ደካማዎቹ ተቀምጠው ኃያሎቹ ተሰደዱ። ብርቱ ቅጣት የገጠማቸው የሚሳደዱና መከራና ፈተና የሚገጥማቸው ባሮችና ድሆች ተቀምጠዋል። የታላላቅ ጎሳዎች አባላት የነበሩ ሙስሊሞች ግን ተሰደዋል። እነዚህን ከስደት የሚያብቃቃ ከፈተናና ከችግር የሚጠብቅ ቤተሰብ ነበር። ከተሰደዱት መሀል አብዝሀኞቹ የዚህ አይነት ከለላ ማግኘት የሚችሉ የቁረይሽ ጎሳ አባላት ነበሩ።…”

ፕሮፌሰር ሙኒር አልገድባንም ይህን ሀሳብ ይጋራሉ። እንዲህ ይላሉ፡- “ይህ የኡስታዝ ሰይድ ግንዛቤ ብዙ የነብዩና የባልደረቦቻቸው ገድሎች የሚያግዙት ታላቅ ግንዛቤ ነው። እንደኔ አመለካከት የሐበሻ ሙሐጂሮች የደረሱበት የኋላ ውጤት እራሱ ይህንን ያጠናክረዋል። የየስሪብ (የኋላዋ መዲና) ስደት እስኪሳካ ድረስ መልእክተኛው ሙሐጂሮቹ ከሐበሻ እንዲመለሱ አልፈለጉም። እንደውም የበድር፣ የኡሑድና የኸንደቅ ዘመቻዎችን ከዚያም የሑደይቢያ ስምምነትን አድርገው እስኪያበቁ ድረስ የሐበሻ ስደተኞች እንዲመለሱ አልፈለጉም። እስከዚህ ድረስ በነበሩት አምስት አመታት ውስጥ መዲና የተረጋጋች ሀገር አልነበረችም። በየጊዜው ለቁረይሾች ጥቃት የምትጋለጥ ከተማ ነበረች። የመጨረሻው ሠፊ ጥቃት የኸንደቁ ጥቃት ነበር። ከዚያም መልእክተኛው መዲና ውስጥ ልባቸው ረጋ። መዲና ፀጥ ያለችና ሰላማዊ የሙስሊሞች ዋና ማእከል መሆኗን አረጋገጡ። ከሙሽሪኮች የሚቃጡ ጥቃቶችም ቆሙ። ይህን ጊዜ ነው መልእክተኛው ሙሀጂሮች ከሐበሻ እንዲመለሱ ያዘዙት። አሁን መዲና በአደጋ የተከበበች እና በድንገት የመካ ሠዎች እጅ ትወድቃለች የሚሉበት ስጋት የላቸውም። ስለዚህ ሐበሻን የጥንቃቄ ጊዜ ተለዋጭ የዳዕዋ ማእከል አድርጎ መያዙ አያስፈልግምና ትተዋት እንዲሄዱ አደረጉ።”

ፕሮፌሰር ዲሩዛህም ተለዋጭ የዳዕዋ ስርጭት ማዕከል ማበጀት የሐበሻው ስደት አላማ እንነደበር ያምናሉ። እንዲህ ይላሉ፡- “… ልብን የሚያረጋጋ ምርጥ ሐሳብ አለኝ። ሐበሻ በዘመኑ የክርስቲያን መንግስት ያላት ሐገር ስለነበረች እርሷ ውስጥ ሠፊ የዳዕዋ መድረክ ይገኛል። ስለዚህ የሐበሻ ሒጅራ አላማ አዲስና ተለዋጭ የዳዕዋ ማዕከል መፍጠር ነበር። ጃዕፈር የሙሐጂሮቹ መሪ ተደርጎ መላኩ የዚሁ ሐሳብ ጠቋሚ መረጃ ነው።…”

“የሐበሻው ስደት ለአዲሱ ነብያዊ አስተመህሮና ተሀድሶ (ዳዕዋ) አማራጭ ማዕከል ለመፍጠር የተደረገ ለመሆኑ የነጃሺና የአንዳንድ ሐበሻዎች መስለም ጥሩ ማሳያ ነው። ሌላ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ነጥብ አለ። ወደ ሐበሻ የተደረገው ስደት በነብዩ ምክርና መመሪያ እንደሆነ ሁሉ ከሐበሻ የመመለሱም ትእዛዝ የመጣው ከርሳቸው ነው። ቡኻሪ ላይ አሽዓሪያዎች የተሰኙት የየመን ጎሳዎችን ሐበሻ ላይ ሲያገኟቸው -ጃዕፈር- እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል። ‘የአላህ መልእክተኛ ወደዚህ እንድንመጣ አዘውናል። እዚሁም እንድንቆይ ይፈልጋሉ። እናንተም ከእኛ ጋር እዚሁ ቆዩ’።” እያሉ ዶክተር ሱለይማን ቢን ሐምድ አልዐውዳህም ይህኑ ሐሳብ ይደግፋሉ።

ይህም ማለት ሰዎቹ ወደ ሐበሻ የመጡት ውስን ተልእኮ ኖሯቸው ነበር። ወደ አላህ ዲን ከመጣራት የበለጠ ምርጥ ተልእኮም አይኖርም። የነርሱም ተልእኮ እርሱው ነበር።

4. ሙስሊሞች አማን የሚሆኑበትን ቦታ መፈለግ

ይህ የመልእክተኛው የደህንነት እቅድ የንጹህ ምእመናንን ህይወት ለመጠበቅ የታለመ ነው። ለዚህ እቅድ ደግሞ ሁነኛ ቦታ ሐበሻ ነበረች። ይህን ሚናዋንም ሐበሻ ኢስላም ይፋ እስከሆነበት እና የክህደት ማእበል የሚያጠፋውን አጥፍቶ ረጭ እስኪል ድረስ ተወጥታዋለች። ይህ ሐበሻ ሁሉ ሊኮራበት የሚገባው ታላቅ ገድል ነው። ሐበሾችንም በኢስላም ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም ያስጻፈ ታሪክ ነው።

ሶሀቦቹ ሐበሻ ውስጥ ሠላም አግኝተዋል። ልባቸውም ረግቷል። ይህን ኡሙ ሰለማም እንዲህ ሲሉ ይመሠክራሉ:- “የሐበሻን ምድር ከረገጥን አንስቶ ምርጥ ጠባቂያችን ከሆነው ነጃሺ ጋር ጥሩ ጉርብትና አግኝተናል። በኃይማኖታችን ሰበብ የሚቃጣብን መከራን ተጠበቅን። አላህን ያለከልካይ አመለክነው።…”

ለምን ሐበሻ ተመረጠች?

ነብዩ ሐበሻን የመረጡበትን ምክንያት ማወቅ ለሚፈልግ ሠው የሚረዱ ጥቂት ነጥቦች አሉ።

  1. የነጃሺ ፍትሀዊነት፡- ይህን ከመልእክተኛው ንግግር ማግኘት እንችላለን። ባልደረቦቻቸውን ወዲህ ሲልኩ እንዲህ ነበር ያሉት፡- “ወደ ሐበሻ ምድር ብትሄዱ መልካም ነው። እርሷ ውስጥ እርሱ ዘንድ ማንም የማይበደል የሆነ ንጉስ አለ።”
  2. የነጃሺ ደግነት፡- የአላህ መልእክተኛ የሐበሻውን ንጉስ ለማወደስ ከተናገሯቸው ቃላት መሀል የሚከተለውን እናገኛለን። “ሐበሻ ውስጥ ነጃሺ የሚባል ደግ ንጉስ አለ። እርሱ ዘንድ ማንም አይበደልም።” ይህን ደግነትም ለሙስሊሞች ባደረገው እንክብካቤ አሳይቷል። የልቡን ንፅህናም ቁርአንን ባዳመጠ ጊዜ ባወረደው እምባ አረጋግጧል። በመሲህ ዒሳ ላይ የነበረው እምነት ትክክለኛ ነበር።
  3. ሐበሻ የቁረይሾች የንግድ ሥፍራ ናት፡- የቁረይሾች የኢኮኖሚ ዋልታ ንግድ ነበር። በአረቢያ ደሴት ውስጥ ደግሞ ሐበሻ እንደ ዋና የንግድ ማዕከል ትታሰብ ነበር። አንዳንድ ሙስሊሞች ለንግድ በመጡበት ተመልክተዋት ይሆናል። ወይም ወደርሷ ከመጣ ሠው ስለሷ የሰሙት ነገር ይኖራቸው ይሆናል። አል-ጠበሪይ ወደ ሐበሻ ስደት የተደረገበትን ምክንያት ባቀረቡበት ፅሁፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡- “ሐበሻ የቁረይሾች የንግድ ስፍራ ነበረች። እርሷ ላይ ይነግዱ ነበር። ከርሷም ጥሩ ጥቅም፣ ሰላምና ሲሳይ ያገኙ ነበር።”
  4. ሐበሻ ሠላም የሠፈነባት ሀገር መሆኗ፡- በጊዜው ከዐረቢያ ደሴት ውጪ ሰላምና ደህንነት የነበረበት እንደ ሀበሻ ያለ ሀገር አልነበረም። እንደሚታወቀው ደግሞ ሐበሻ ከቁረይሾች ተፅእኖ ነጻ የሆነች የነርሱን መመሪያ የማትከተል ሀገር ናት። ይህ ከዐረብ ጎሳዎች የተለየ ግምት ይሰጣታል። ኢብኑ ኢስሐቅ ሐበሻ ለስደት ማእከልነት የተመረጠችበትን ምክንያት ባስረዱበት ጊዜ ያነሱት ሐዲስ ላይ እንዲህ የሚል እናገኛለን:- “እርሷ የእውነት ሐገር ናት። እርሱ ዘንድ ማንም የማይበደል ንጉስ በርሷ ውስጥ አለ።” እርሷ የእውነት ሐገር ናት። ንጉሷም ፍትሀዊ ነው። ይህ ደግሞ የሠላማዊ ሀገር መገለጫዎች ናቸው።
  5. መልእክተኛው ሐበሻን መውደዳቸውና ስለርሷ ማወቃቸው፡- እዚህ ላይ የምንጠቅሰው የኢማም አዝ-ዙህሪይን ሐዲስ ነው። እንዲህ ይላል:- “ሐበሻ መልእክተኛው ሊሰደዱባት ከሚሹባቸው ሀገራት መሀል ተወዳጇ ነበረች።”

ምናልባት ይህ ፍቅርና ውዴታ ሰበብ ይኖረው ይሆናል፤

  • የነጃሺ ፈጣንና ፍትሀዊ ዳኝነት
  • የወቅቱ ሐበሻዎች ክርስቲያኖች መሆናቸውና ክርስትና ከጣኦተኞች በተሻለ ለኢስላም የቀረበ መሆኑ።
  • መልእክተኛው ስለሐበሻ የሚያውቁት ብዙ ነገር መኖሩ። በተለይም ኡሙ አይመን የተባለችው አሳዳጊያቸው ሐበሻ እንደመሆኗ ከርሷ የቃረሟቸው የሐበሻ ገድሎችን ያውቁ ነበር። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች መልእክተኛው ሐበሻን እንዲወዱ እንዳደረጋቸው ይጠረጠራል።

የስደተኞቹ አወጣጥ

የአላህ መልእክተኛ ባልደረቦች መካን የለቀቁት ልክ ከነብይነት በኋላ በአምስተኛው አመት ላይ በረጀብ ወር ውስጥ ነበር። ምናልባት እዚህ ሐበሻ የደረሱት ወርሀ-ሻዕባን መጀመሪያ አካባቢ ነው። አስር ወንዶችና አራት ሴቶች ነበሩ። ሴቶቹ አምስት ናቸው የሚልም ዘገባ እንዳለ ይታወቅ። ቁረይሾች ከመንገድ ወደ መካ ሊመልሷቸው ሞክረው ነበር። ዱካቸውን ተከትለው የባህር ዳርቻው ድረስ ደርሰው ነበር። ነገር ግን ሙስሊሞች ቀድመው ባህሩን ተሳፍረው ነበርና ሊደርሱባቸው አልቻሉም።

አወጣጣቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎችን ስንመለከት በሚስጥር እንደወጡ የሚጠቁሙ ዘገባዎችን እናገኛለን። ለምሳሌ አል-ዋቂዲይ እንደዘገቡት “በድብቅና በቀስታ ወጡ።” ይላል። አል-ጠበሪይም እንዲሁ አይነት ዘገባ አስፍረዋል። ኢብኑ ሰይዲን-ናስ፣ ኢብኑ-ልቀዪምና አዝ-ዙርቃኒይ ያሰፈሯቸው ዘገባዎች ይህንኑ ይመሰክራሉ። ሙስሊሞቹ ሐበሻ እንደደረሱ ነጃሺይ የአክብሮት እንክብካቤ አደረገላቸው። ቤተሰቦቻቸውና ሀገራቸው ላይ ያላገኙትን ደህንነትና ሰላምም ሠጣቸው።

የስደተኞቹን ስም በጥሞና ያጤነ ሰው ችግር ይደርስባቸው የነበሩ ቢላልን፣ ኸብ-ባብንና ዐም-ማርን የመሠሉ ድሆችና ባሮችን ስም አያገኝም። በተጻራሪው የባለሀብትና የአለቆች ቤተሠብ አባላትን በብዛት ያገኛል። ቁረይሽ ውስጥ ታላቅ ስፍራ ያላቸው የጎሳ አባላት ቤተሰቦችን ያገኛል። በእርግጥ የማእረግ ባለቤት ከሆኑ ቤተሠቦች የወጡት ሙስሊሞች መከራ አልደረሠባቸውም አይባልም። ነገር ግን መከራው የጎሳ ጥበቃ በማያገኙት ባሮች ላይ ይበረታል። በተለይም በቁረይሽ ማህበረሰብ ውስጥ ለጎሳ ክብር ታላቅ ግምት ይሰጣልና ፈተናው ለድሆቹ ይከብዳል። የሒጅራ ግቡ ከጭንቅ መሸሽ ብቻ ቢሆን ኖሮ ከማንም በላይ መሰደድ የሚገባቸው እነዚህ ድሆችና ባሮች ናቸው። ምክንያቱም እነርሱ ዘብ የሚቆምላቸው እና መከራቸውን የሚካፈል ጎሳ አያገኙም። ኢብኑ ኢስሐቅና ሌሎች ዐሊሞች የደካማዎቹን ስቃይ ጠቅሰው መሰደዳቸውን አለማስፈራቸው ንግግራችንን ይበልጥ ያጠናክርልናል።

ስለዚህ የሒጅራን ሰበብ የሚያጠና ሰው አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ምክንያቶች ላይ ይደርሳል። ሶሀቦችን ወደ ሐበሻ ያስሰደደው ስቃይና መከራ ብቻ ሳይሆን የትልልቅ ቤተሰብ አባላትን የሚያስመርጥ ሌላ ተልእኮ አለ። በአንድ ጎን ቁረይሾች ሐበሻዎችን አሳምነው ስደተኞቹን ወደ መካ ለመመለስ ይችሉ ይሆናል። በሌላ ጎን የልጆቻቸው ስደት የሚያነቃንቃቸው ብዙ ቁረይሾች አሉ። መካ ለተወላጆቿ ጠባለች ብለው የሚነሱ ወገኖች ቁረይሽ ውስጥ ይፈጠራል። በሦስተኛ ጎን ደግሞ እነዚህ ስደተኞች ለኃይማኖታቸው ሲሉ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ እምነታቸውን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ያደርሳሉ። ምናልባት ለጥሪያቸው ምቹ የሆነች ስፍራን ያገኙና የጎሳዎቻቸው አእምሮና ልቦና ለተዘጋበት ጥሪያቸው ክፍት የሆነ አእምሮና ልቦና ያገኙ ይሆናል።

ሙስሊሞች ስደቱ ከተጀመረ ሦስት ወር ያህል ኖሩ። መካ ውስጥ ደግሞ በሙስሊሞች ህይወት ውስጥ ታላቅ ለውጥ የሚፈጥር አዲስ ክስተት ተከስቷል። ከዚህ በፊት ያልነበረ አዲስ ነገር ሆኗል። ይህ ክስተት ሙስሊሞች በኃይማኖታቸው ላይ ተስፋ እንዲጥሉ ያደረገ ክስተት ነበር። ዳዕዋቸው መካ ውስጥ ሳይቀር እያበበ እንደሚሄድ ምኞት የጣለ ክስተት ነው። በእነዚህ ጥቂት ወራት ውስጥ የነብዩ አጎት -ሐምዛ ኢብኑ አቢጣሊብ- እና ዑመር ኢብኑል-ኸጣብ ሰለሙ። የነብዩ አጎት መጀመሪያ ዘረኝነቱ ገፋፍቶት ሰለመ። ከዚያም አላህ ልቡን ከፈተለትና እምነቱ ረጋ። ኒያውም ተስተካከለ። ሐምዛ ከቁረይሽ ወጣቶች መሀል ኃይለኛ የሚባል አይነት ነበር። ጉልበተኛ ነበር። እርሱ ወደ እስልምና ሲገባ የአላህ መልእክተኛ ኃይላቸው እያየለ እንደሆነ ቁረይሾች ተረዱ። አጎታቸው እንደሚጠብቃቸውና ከሚቃጡባቸው አደጋዎችም እንደሚከላከልላቸው ተገነዘቡ። ስለዚህ አንዳንድ ይፈጽሟቸው የነበሩትን በደሎች ተዉ።

ሐምዛ ከሠለመ በኋላ ዑመር ኢብኑል-ኸጣብ ተደገሙ። ዑመርም ማንም የማይዳፈራቸው ኃይለኛ ሠው ነበሩ። እርሳቸው ሲሰልሙ ሶሃቦች እርሳቸውንና ሐምዛን መከላከያ አድርገው መያዝ ጀመሩ። ከዚያም ለቁረይሾች የማይበገሩ ሆኑ።

እነዚህ ታሪክ የማይዘነጋቸው ሁለት ሶሀባዎች ናቸው። የሰለሙት ሙስሊሞች ወደ ሐበሻ ከተሰደዱ በኋላ ነው። የነርሱ መስለም ለሙስሊሞች ልቅናን ጨምሯል። የሙሽሪኮችን አንገትም ሠብሯል። የመልእክተኛው ባልደረቦች ከድብቅ ዳዕዋ ወደ ይፋ ጥሪ ተሸጋግረዋል። እምነታቸውንም በግልፅ እንዲናገሩ አድርጓቸዋል።

ዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ እንዲህ ብለዋል፡- “የዑመር መስለም ታላቅ ገድ ነበር። ወደ መዲና መሰደዳቸው ደግሞ ታላቅ ድል ነበር። የመሪነት ዘመናቸው ደግሞ እዝነት ነበር። እኛ ከዕባህ አጠገብ መስገድ አንችልም ነበር። ዑመር ሲሰልሙ ግን ቁረይሾችን ታገሏቸውና ካዕባ አጠገብ ሰገዱ። እኛም ተከትለናቸው ሰገድን።”

ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር እንዲህ ይላሉ፡- “የሰለሙ ቀን -ዑመር- ‘ማን ይሆን ከቁረይሾች መሀል መስለሜን የሚነግር ጥሩ ወረኛ?’ ብለው አሰቡ። ከዚያም ጀሚል ቢን ሙዐመር አል-ጁመሒይ ፈጣን ወሬ አድራሽ እንደሆነ ሲነገራቸው በጠዋት ወደርሱ ጋር ለመሄድ ተነሱ። እኔም ምን ሊያደርጉ ይሆን ብዬ ተከተልኳቸው። ከዚያም ልክ ሲያገኙት ‘ጀሚል ሆይ! እኔ መስለሜንና ወደ ሙሐመድ ኃይማኖት መግባቴን አላወክም እንዴ?!’ አሉት። በአላህ እምላለሁ ገና ዑመር ለተናገሩት ንግግር ምላሽ ሳይተነፍስ መጎናፀፊያውን እየጎተተ ሄደ። ዑመርም ተከተሉት። እኔም አባቴን ተከተልኩኝ። ሰውየው ልክ የተከበረው መስጊድ ደጃፍ ላይ ሲደርስ ‘እናንተ የቁረይሽ ህዝቦች ሆይ!’ -እነርሱ ከከዕባ ዙሪያ ተሰብስበው ነበር።- ‘የኸጣብ ልጅ ከሀዲ ሆነ!’ ብሎ ጮኸ። ከኋላው እየተከተሉ ‘ውሸቱን ነው! እኔ ሠለምኩኝ እንጂ አልካድኩም! በአላህ ጌትነትና በመልእክተኛው ሙሐመድ ነብይነት አምኛለሁ!’ እያሉ ይጮኻሉ። ከዚያም ቁረይሾቹ ዘለሉ። ተጋደሉት እርሱም ታገላቸው። ፀሀይ መሀል አናታቸው ላይ እስኪሆን ድረስ ታገሉ። ከዚያም ደከማቸውና -ዑመር- ተቀመጡ። ቁረይሾቹ አናታቸው ላይ ቆመው ሳሉ እርሳቸው ግን ‘የሻችሁን ሥሩ። በአላህ እምላለሁ ሦስት መቶ ብቻ እንኳን ብንሆን ሀገሩን ወይ ትተዉልናላችሁ ወይ እንተውላችኋለን እንጂ አላርፍም!’ ይሉ ነበር።…”

ስለዚህ ሙስሊሞች ከሐበሻው ሒጅራ በፊት ከነበሩበት ሁኔታ የተሻለ ተጨባጭ ላይ ደርሰዋል። በሐምዛና በዑመር ትከሻ ሥር መደበቅ ችለዋል። የማይታሰበውን ከዕባህ አቅራቢያ መስገድም ቻሉ። በይቱል አርቀም ኢብኑ አቢል-አርቀም ቤት መደበቃቸውም ቀረ። በይፋ እምነታቸውን መግለጥ ቻሉ። የቁረይሾች አረመኔያዊ ቅጣትም ጋብ አለ። ይህ ለሙስሊሞች አዎንታዊ ለውጥ ነው። ከሐበሻው ሒጅራ በፊት ይኖሩበት የነበረው ሁኔታቸው ተለውጧል። ይህን መደበቅ ይቻላል? እነዚህ ለውጦች ወደ ሐበሻ ምድር በመድረስ እዚያ ያሉት ስደተኞች እንዳይሰሙ ማድረግ ይቻላል? በተለይም በጂዳ በኩል የሚተላለፉት የባህር ተጓዦች ወሬውን አያደርሱትም ተብሎ ይጠበቃል? በፍፁም…

ወሬው በጊዜ ነው የሚደርሳቸው። በዚህ ዜናም እንግዶቹ እጅግ እንደሚደሰቱ አያጠራጥርም። ከዚያም ሐገራቸውን እንደሚናፍቁ ግልፅ ነው። ይህ ተፈጥሮአዊ ስሜት ነው። የከተማዎች አውራ ወደሆነችው ቀያቸው ለመመለስ ቋመጡ። ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ ተነሱ። ልባቸውን በሚያደፋፍረው ዜና በመመራት ገሰገሱ። ወደ ጥንታዊቷ ምርጧ የአላህ ሀገር፣ ወደ እድሜ ጠገቡ ቤቱ -መካ-…

የሀበሻ ሙሐጂሮች ሐምዛና ዑመር መስለማቸውን ሲሰሙ ወደ ሐገራቸው ተመለሱ። ምክንያቱም የነዚህ ሠዎች መስለም የሙስሊሞችን ኃይል ያጠናክራል ብለው ያምናሉና።

ነገር ግን ይህ ምኞታቸው አልተሳካም። ቁረይሾች የእነዚህን ሁለት ሰዎች መስለም በአዲስ አካሄድ ተቃወሙት። በአንድ በኩል እኩይ ተንኮላቸውን በሌላ በኩል ደግሞ ጭካኔያቸውን የሚያሳዩ አዳዲስ እርምጃዎችን ወሰዱ። የቅጣት መሳሪያዎችን ጨመሩ። አዳዲስ የማስፈራሪያ መንገዶችን ቀየሱ። አዲስ ያመጡት መሳሪያ ክፉ ነበር። መልእክተኛውንና ተከታዮቻቸውን ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ማግለል ነበር አዲሱ መሳሪያ። ማዕቀብ። ክስተቱ ሰፊ ትንታኔ ስለሚያሻው እዚህ ላይ ዝርዝሩን ማውራት አያስፈልገኝም። ዋናው ነገር- የተሻለ ነገር ይገጥመናል ብለው ከሐበሻ የመጡት ስደተኞች ድጋሚ የሚያስከፋቸው ነገር ገጠማቸው። አሁንም ስደቱ ወደ ሐበሻ ነበር። ከመጀመሪያው የበዛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በድጋሚ ወደ ሐበሻ አመሩ።

http://www.ethiomuslims.net/

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.