ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳም
ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳም በጎጃም ክፍለ ሀገር ከሚገኙት ቅዱሳት አያሌ ገደማት መካከል አንዷ የታላቋ እና የጥንታዊቷ ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳም ናት ፡፡ ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳም የምትገኘው በጎጃም ክፍለ ሀገር በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ርእሰ ከተማ መርጡለ ማርያም ሲሆን ከአዲስ አበባ ሰሜናዊ አቅጣጫ ከባሕር ጠለል በላይ በ2,405 ሜትር ከፍታ ትገኛለች ፡፡
መርጡለ ማርያም ትርጉሙ ፦ የማርያም አዳራሽ ማለት ነው ፡፡ ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳም አሁን የያዘችውን የስም መጠሪያ ከመያዟ በፊት በተለያዩ ዘመናት አራት ጊዜ የስም መለዋወጦች አጋጥሟታል ፡፡ መጀመሪያ ሀገረ ሰላም ተብላለች ቀጥሎ ሀገረ እግዚአብሔር ተብላለች ከዚያም ጽርሐ አርያም ተብላ ተጠርታለች በመጨረሻም አሁን የምትጠራበትን መርጡለ ማርያም የሚለውን ስያሜ አግኝታለች ፡፡
የገዳሟ አስተዳዳሪ ርእሰ ርኡሳን የሚል ስያሜ አለው ፡፡ ይች ታላቅ እና ጥንታዊት ገዳም የተመሰረተችው ከእስራኤሉ ንጉሥ ሰሎሞን እና ከኢትዮጵያዊት ንግሥት ሳባ (ማክዳ) የተወለደው ቀዳማዊ ምኒሊክ በአራት ሺ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም ነው ፡፡ የኦሪት ካህናት መሥዋተ ኦሪትን አምልኮት ሲፈጽሙ ኖረዋል ፡፡ በ፫፻፴፫ ዓ.ም ህሩያን ነገሥታት አብርሃ ወ አጽብሃ ከከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ ጋር በመሆን በዚች ቦታ መጥተው ሕገ ወንጌልን አስተምረዋል ሕዝቡን አጥምቀው ካህናትን ሹመዋል ፡፡
አምስቱ ተራሮች
ገድለ አብርሃ ወ አጽብሃ እና ገድለ አባ ሰላማ ከሳቴብርሃን እንደሚያስረዱት ሕሩያን ነገሥታት አብርሃ ወ አጽብሃ ከጳጳሱ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ጋር በመሆን በ፫፻፴፫ ዓ.ም አባይን ተሻግረው ጎጃም ምድር መርጡለ ማርያም ደረሱ ፡፡ “ ወአደው ፈለገ ግዮን አብርሃ ወ አጽብሃ ዘምስለ ሰላማከሳቴ ብርሃን ወበጽሑ ምድረ ጎጃም ” በዚህ ቦታ ሕዝበ ክርስቲያኑን ወንጌል አስተምረው መክረው ከኦሪት ወደ ሐዲስ ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተእግዚአብሔር መልሰው ካጠመቁበኋላሕዝበ ክርስቲያኑ አምልኮቱን የሚፈፅምበት ቤተ ክርስቲያንን ለመስራት አሰቡ ፡፡ ቦታው ላይ በጣም የሚያምር ቤተ ምኲራብ ስለ ነበር ይህንን ለታሪክ ትተን ሌላ ቦታ ላይ እንስራ በማለት በስተ ምሥራቅ አሻጋሪ ካለው ተራራ አሁን ግንብ ወሬ እየተባለ ከሚጠራው ኮረብታ ለይ ቁፋሮ ጀመሩ ፡፡ ነገር ግን መሬቱ የእሳት ትንታግ እየተፋ አልቆፈር አለ ፡፡ በመሆኑም በዚህ ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንሰራ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደም ፈቃደ እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ ለ፫ ተከታታይ ቀናት ሱባኤ እንግባ በማለት በ፭ በአካባቢው ባሉ የተለያዩ ኮረብታዎች ሱባኤ ገቡ ፡፡
ሱባኤየገቡባቸው ከረብታዎች የሚከተሉት ናቸው
የኦሪቱ ሊቀ ካህንአብኒ ከተባለው ኮረብታ
የሐዲሱ ሹም ሐዲስጌ ከተባለው ኮረብታ
ጳጳሱ አቡነ ሰላማ ሰላምጌ ከተባለው ኮረብታ
ንጉሥ አብርሃ አብርሂ ከተባለው ኮረብታ
ንጉሥ አጽብሃ ዜነዎ ከተባለው ኮረብታ
ንጉሥ አጽብሃም ከሁሉም አስቀድሞ ወደ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንበመሄድ ያየውን ራዕይ ተናገረ ፡፡ ሌሎችም መጥተው ያዩትን ሁሉ ተናገሩ አባ ሰላማም ይህንን ራዕይ ያዩ መሆናቸውን ነገሯቸው ፡፡ሁሉም በአንዲት ሌሊት አንድ ዓይነት ራዕይ አዩ ፡፡ ያዩት ራዕይም ፦ “ ዐሥራሁለት በሮች ያላትአንድ አምደ ብርሃንየቤተ መቅደሱ መሰረትከተጀመረበት ኮረብታ ተነስታእያበራች የጥንቱ ቤተምኲራብ ከሚገኝበትጽርሐ አርያም አምባላይ ስታርፍ ” ነበር ፡፡ጧት ወደ ቦታውሲሄዱ የጥንቱ አስደናቂውቤተ ምኲራብ መሬትውስጥ ተቀብሮ ለጥያለ አረንጓዴ ሜዳሆኖ አገኙት ፡፡“ ወእም ድህረዝ ፈቀዱ አብርሃ ወ አጽብሃከመ ይህንጽ መቅደስ በህየ ወሐነጹ ማህደረ ሰናይተ ወገብሩ አረፋቲሃ ዘወርቅ ወዘብሩር ወሴሙ ካህናተ ወዲያቆናተ ወአስተሳነዩ ኲሎሥርዓተ ወሴሙ በውስቴታ ርእሰ ርኡሳን ዘውእቱ ሊቀ ካህናት ወሰመይዋ ለይእቲ መቅደስ መርጡለ ማርያም ” ነገሥታቱ አብርሃ ወ አጽብሃበቦታው ቤተ መቅደስን ይሰሩ ዘንድ ወደዱ በወርቅ እና በእንቍ አምዶችን እና አረፍቶችን ልዩ አድርገው በማስጌጥ የማርያምን ቤተመቅደስ ሰሩ ፡፡ ሥርዓትንም በመደንገግ ካህናትን ዲያቆናትን እንዲሁም ሁሉንም ሊያስተዳድር የሚችል ሊቀ ካህናት ርእሰ ርኡሳን ብለውሾሙ ፡፡ መቅደሷንም መርጡለ ማርያም ብለው ሰየሟት ፡፡ ንጉሥ አብርሃወ አጽብሃም እግዚአብሔርበመራቸው መሰረት በጳጳሱበአባ ሰላማ አስባርከውበጽርሐ አርያም አምባላይ አስደናቂውንባለ ፲፪ ቤተመቅደስ ባለ ፩ ፎቅቤተ መቅደስ ሰርተውበወርቅ በእንቊ በከበሩማዕድናት አስጊጠው ጥር፳፩ ቀን የእመቤታችንንጽላት አስገብተውቅዳሴ ቤቱን አከበሩ፡፡ ንጉሥ አብርሃ ወ አጽብሃ ቤተ መቅደስ ለመስራት መጀመሪያ ቁፋሮየጀመሩበት ተራራ አሁንም ግንበ ወሬ እየተባለ ይጠራል በወሬ የቀረ ግንብ ማለት ነው ፡፡ በዚህ የተነሳ ንጉሥ አጽብሃ በመጀመሪያመጥቶ ራዕዩን ስለ ተናገረ ሱባኤ የገባበት ኮረብታ ዜነዎ ሲባል ሌሎች አባቶች ሱባኤ የያዙባቸው ኮረብታዎች አሁንም በየስሞቻቸውእየተጠሩ ሕያው የታሪክ ምስክሮች ሆነው ይገኛሉ ፡:
አብርሃ ወ አጽብሃ በዚች ቦታ ላይ በ፫፻፴፫ ዓ.ም ባለ ፲፪ ቤተ መቅደስ እና ባለ ፩ ፎቅ ቤተ ክርስቲያን አንጸው የእመቤታችንን ጽላት ጥር ፳፩ ቀን በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስገበተዋል ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን እጅግ የተለየ በልዩ ልዩ ቅርፅ ያጌጠ በወርቅ እና በእንቁ የተለበጠ አስደናቂ የጥበብ አሻራ ያረፈበት ነበር ፡፡ ይህ ቤተ መቅደስ በዮዲት ጉዲት ዘመን በ፰፻፵፪ ዓ.ም ተቃጥሏል ፡፡ ከቃጠሎው የተረፈው ፍርስራሽ አሁንም አለ ፡፡ በ፰፻፹፪ ዓ.ም የነገሰው አንበሳ ውድም በዮዲት የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን እንደገና አሰርቶታል ፡፡ ነገር ግን አብርሃ ወ አጽብሃ ያሰሩት ባለ ፲፪ ቤተ መቅደስ እና ባለ ፩ ፎቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መልሶ ለመስራት በጣም አስቸጋሪ ሰፊ ታላላቅ ሙያተኞችን የሚጠይቅ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ውስብስብ እና ጥልቅ ጥበብ የሚጠይቅ በመሆኑ መልሶ ለመስራት አልቻለም ፡፡ በመሆኑም ከተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ሌላ የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን አሰርቷል ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን አሁንም በአገልግሎት ላይ አለ ፡፡ ይህንን ቤተ ክርስቲያንን ከነሐሴ ፳፮ ፲፬፻፷ ዓ.ም – ኅዳር ፲ ፲፬፻፸ ዓ.ም የነገሠው ንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም በ፲፬፻፷ ዓ.ም አሳድሶታል ፡፡ ባለቤቱ ንግሥት እሌኒ ደግሞ የአንባውን ዙሪያ አሰርታለች አሁንም የገዳሟ ዙሪያ የእሌኒ ውድሞ ይባላል ፡፡ ንጉሠ ነገሠት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በ፲፱፻፴፯ ዓ.ም ሌላ ቤተ ክርስቲያን በዚች ገዳም ውስጥ አሰርተዋል ፡፡ የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ገብርኤል ጽላት ይገኝበታል ፡፡ እንደገናም በ፲፱፻፸፫ ዓ.ም በወቅቱ የገዳሟ አስተዳዳሪ የነበሩት ርእሰ ርኡሳን አባ ለእከ ማርያም ከሳር ክዳን አሁን ወዳለበት ቆርቆሮ ክዳን አሳደሰውታል ፡፡ በዚች ገዳም ውስጥ ፫ ቤተ ክርስቲያን አሉ ፡፡ ፩. አብርሃ ወ አጽብሃ ያሰሩት የእመቤታችን ቤተ መቅደስ ፪. ነጉሥ አንበሳ ውድም ያሰራው የእመቤታችን ቤተ መቅደስ ፫. ንጉሥ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያሰሩት የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ገብርኤል ቤተ መቅደስ ናቸው ፡፡
Leave a Reply
You must be logged in to post a comment.