በአንድ ልብ የቆመ ህዝብና በግማሽ ልብ የሚይያነክስ ህዝብ ፍጥጫ ?
በሸንቁጥ አየለ (shenkutayele@yahoo.com)
ዘመናዊ አገር ግንባታን ዉጤታማ: የማይናጋ እንዲሁም ቀጣይነት ያለዉ እንዲሆን የሚያደርጉ በርካታ መሰረታዊ ጉዳዮች ቢኖሩም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸዉ:
1. አገሩ የቆመበት መሰረት ስፋት : ጥልቀትና ሁሉን ዜጋ ባይሆን እንኩዋን ብዙሃኑን የሚያስማማ መሆኑ
2. አንዱ ወገን ሲገነባ ሌላዉ ወገን ለማፍረስ እቅድ ነድፎና ተደራጅቶ የማይንቀሳቀስ እስከሆነ ድረስ
3. በተለያዩ ሀይላት መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መተማመን እና የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ካለ
4. ከሀገራዊ እድገትና ምጥቀት ሁሉም ወገን ተጠቃሚ ነኝ ብሎ ካመነ/ቢያንስ ተስፋ የሚያደርግ ከሆነ
ይህን የሀገር ግንባታ ጉዳይ ያነሳሁት የሀገራት ጥንካሬ መሰረት : የአንድ ህዝብ የጋራ የአንድነት መሰረትና የዉጭ ጠላትን በአብሮነት የመመከት ሂደት የሚመሰረተዉ በዚሁ የሀገር ግንባታ ሂደታዊ ጥንካሬ ላይ ስለሆነ ነዉ:: የአንድ ሀገር ህዝብ በአንድ ልብ ቆሞ የጋራ ጥቅሞቹን የማስጠበቅም ሆነ የጋራ ጠላትን የመመከት ሚስጥር የሚጠነሰሰዉም ሆነ የሚቁዋጨዉ በዚሁ ከላይ በተነሳዉ ጽንሰ ሀሳብ ላይ ተመርኩዞ ነዉ ::
እናም ሰሞኑን በሁለት ሀገራት መካከል የተነሳዉ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጉዳይ ጭቅጭቅን ከላይ በተነሳዉ ነጥብ ማዕቀፍ ዉስጥ ሆኖ መቃኘት በርካታ ጉዳዮችን እንድንታዘብ ያስችለናል:: ከወዲያ በአንድ ልብና በአንድ አላማ የቆሙ የግብጽ ህዝብን የሚወክሉ ታላላቆች: ታናናሾች : ሀገር የሚመራዉ ፓርቲ : ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም በሀገራችን ላይ ያገባናል የሚሉ ሀይሎች ሁሉ በጋራ ኢትዮጵያ ላይ ጣታቸዉን እየቀሰሩ ዋ ዉሃዉን ትነኪና : ዋ የእኛን ጥቅም ትጋፊና እያሉ ከፍተኛ ስሜት ዉስጥ ገብተዉ የግብጽ ጥቅም በጦርነትም ቢሆን ይጠበቃል ሲሉ ይደመጣሉ::
በግብጾች መካከል አንድኛዉም ወገን እንኩዋን የተለየ አቁዋም ሲያራምድ አይደመጥም:: እንዲያዉም ደፋሮቹ ግብጾች ኢትዮጵያዉያንን እንደለመድነው በእርስ በእርስ ፍጭትና ግጭት እንዲዳከሙና እንዲጠፋፉ እናደርጋቸዋለን ሲሉ ይደመጣሉ::ለዚህም የጎሳ ልዩነታቸዉን: የፖለቲካ ልዩነታቸዉን እና የሀይማኖት ልዩነታቸዉን ሁሉ እንጠቀማለን ብሎም በአባይ ላይ የጀመሩት ጥረት እንዲቆም ብሎም ወደፊት ሙከራ እንዳያደርጉ እናሽመደምዳቸዋለን ሲሉ ይደመጣሉ::
በወዲህ ከኢትዮጵያ ከተለያዩ ጽፎች የሚደመጡት አቁዋሞችና ድምጾችም ኢትዮጵያዉያን የጋራ የቤት ስራቸዉን በጋራ ሆነዉ ገና እንዳልሰሩ ያሳብቃሉ:: በተቃዉሞዉ ጎራ ያሉት ኢትዮጵያዉያን የሚሰጡት ትንታኔ ከመንግስት ትንታኔ ጋራ የሚቃረን እና ጉዳዩን በተቃራኒ አቅጣጫ የሚመለከት ነዉ:: እንዲያዉም ከግድቡ ጀርባ ተንኮልና ደባ አለ ሲሉ የራሳቸዉን ሀሳብ በመሰንዘር የግድብ ስራዉን ሊደግፉት ቀርቶ አምርረዉ ሲቃወሙ ይደመጣሉ:: ሆኖም መንግስት በዉጭም ሆነ በዉስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች የያዙትን አስተሳሰብ በማስለወጥ ወደ ራሱ ለመሳብ የሚያደርገዉ እንቅስቃሴ
በአሉታና በጥላቻ የተሞላ ነዉ:: ቆም ብሎ ሊያደምጣቸዉም የፈለገም አይመስልም:: እንዲያዉም የእነዚህ ወገኖች ሚና ኢምንትና እዚህ ግባ የማይባል ነዉ ሲል ያጣጥላቸዋል:: አገር አፍራሽ : የሀገር ልማት የማይመኙ ሲልም በፕሮፖጋንዳ አለንጋ ይዠልጣቸዋል:: እነሱም ባላቸዉ አቅምና ጉልበት ሁሉ የመንግስትን ጥረት ማጣጣልና ማጠለም ቀጥለዋል::
የቀድሞዉ የሀገር መሪ መንግስቱ ሀይለማሪያም የሚቃወሙዋቸዉን ወገኖች አግባብተዉ በጋራ ሀገራዊ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ከማድረግ ይልቅ በስድብና በንቀት “ሰባት ወንበዴ: እፍኝ የማይሞሉ ገንጣይና አስገንጣይ” በማለትና እና መሰል አዋራጅ አባባሎችን በመለጠፍ ግዜአቸዉን አባክነዉ ብሎም ጉልበታቸዉን ጨርሰዉ መንበረ ስልጣናቸዉን መነጠቃቸዉ እዉን ሆነ:: እናም እሳቸዉ የደከሙበት የፓዌ መስኖ ልማት ድካምም አብሮ አከተመለት::
በተመሳሳይ በአሁኑ ጊዜም ሀገሪቱን የሚመሩት ወይም የሚገዙት ወገኖች አገሪቱ የቆመችበት መሰረት ስፋት : ጥልቀትና ሁሉን ዜጋ ባይሆን እንኩዋ ብዙሃኑን የሚያስማማ መሆኑን : አንዱ ወገን ሲገነባ ሌላዉ ወገን ለማፍረስ እቅድ ነድፎና ተደራጅቶ የማይንቀሳቀስ መሆኑን : በተለያዩ ሀይላት መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መተማመን እና የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ወሳኝ መሆኑን ብሎም ከሀገራዊ እድገትና ምጥቀት ሁሉም ወገን ተጠቃሚ ነኝ ብሎ እንዲያምን ወይም እንዲያስብ/ ቢያንስ ተስፋ እንዲያደርግ ከመስራት ይልቅ እኛ የምንለዉ ብቻ : እኛ ብቻ ለሀገር አሳቢ የሚለዉን ዘይቤ ሙጭጭ ብለዉ ቀጥለዋል:: ኢትዮጵያ የበለጠ የኛ ሀገር ነች የሚለዉ የቀደመዉ ዘመን ዘይቤ መሆኑ ነዉ::
እንግዲህ የሚሰማም ቢኖርም ባይኖርም የዚህች ሀገር እጣ ፋንታ በአንድ ክር ላይ ተንጠልጥሎአል:: ያች ክርም የሀገር ግንባታ ሂደቱ የተንጠለጠለባት ክር ነች:: ጥያቄዉ ይህች ክር ምን ያህል ትልቅ መሰረት ላይ ቆማለች: ምን ያህል ወፍራ ተገምዳለች: ምን ያህል ሁሉም ክሩዋ እንዳትበጠስ ይጠብቃታል: የእኔ ናትስ ብሎ ስንቱ ያስባታል : ስንቱስ ክሩዋን እየገመድ ወፍራምና የማይበጥስ ገመድ ከዚያም ሰፊ መሰረት ላይ የቆመ የማይናወጥ የጋራ ቤት የደም ስር እንድትሆን እያደረገ ነዉ የሚለዉ ህሳቤን በሚመለከታቸዉ አእምሮ ዉሰጥ እየተንሰላሰለ ነወይ የሚለዉ ጉዳይ ነዉ::
አሁን ለጊዜዉ ያለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁኔታ ሲዳሰስ ግን በግማሽ ልብ የሚይያነክስ ህዝብ ይመስላል:: ተቃዋሚዉ በዚያ በኩል ገዥዉ በዚህ በኩል ሀሳቡን በተለያየ ቦይ ዉስጥ የሚያፈስበት ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብም ነገሩን በዝምታ የሚመለከትበት የሰፈነ ይመስላል:: እናም ሁሉ ወገን ቢያንስ ብዙሃኑ ህዝብ ኢትዮጵያዊ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቱዋን ብሎም በአባይ ወንዝ ብትጠቀም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አትራፊነቱን ከዚያም በዘለለ ከሚደረገዉ ጥረት ጀርባ ቅንነት እንጂ ደባ አለመኖሩን ተቀራርቦ በልበሰፊነት: በአርቆ አሳቢነት መወያየት ብሎም ቢያንስ በትልቁ አገራዊ አጀንዳ ላይ አንድ ልብ መሆን ወሳኝ ነዉ::
እንዲህ አይነት ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ለጠለቀ ሀገር ግንባታ መሰረት ሊጥሉ የሚችሉት በቅንነት : በመተማመን እና በረዥም ራዕይ ጉዳዩን ማስላት ከተቻለ ብቻ ነዉ:: አሁን ያለዉን ሁኔታ በአንክሮ እያስተዋለ በልቡ ለሚተነትን ሰዉ ግን በኢትዮጵያዉያን እና በግብጻዉያን መካከል ያለዉ ፍጥጫ የሚከተለዉን ተጠይቃዊ አግራሞት ያጭርበታል – በአንድ ልብ የቆመ ህዝብና በግማሽ ልብ የሚይያነክስ ህዝብ ፍጥጫ ? !
Leave a Reply
You must be logged in to post a comment.