የአባይ ግድብና መዘዙ

በማሙሸት አማረ 

ኢህአዴግ ከሚመፃደቅበት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ያልተካተተውና በአንድ ቀን ሌሊት ህልም ታልሞ በስራ ላይ እንዲውል የተወራለት የተዘመረለት ፤የተዘፈነለት ፤የተለመነለት ፤ቅኔ የተቀኘለት ግጥም የተገለጠመለት ፤ዜማ የተወጣለት ደራሲያን የደረሱለት፤ እስክስታ የተወረደበት፤ ድራማ የተሰራበት ተዋንያን የተወኑለት፤ እና አቶ መለስንም “አባይን የደፈረው ጀግና የተባለለት እረ ምኑ ቅጡ ሁሉም ነገር የተባለለት የአባይ ግድብ ነው:: የጉዳቱም ሆነ የጥቅሙ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይነገረው፤ ሳያውቀው ፤ሳይመከርበት፤ በእኛ እና ውቅልሀለን አባዜ የተለከፈው ወያኔ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ የሚሸርበው ደባ ህዝቡን ሳይወድ በግድ ጎትቶ ከአፍሪካዊያን ጎረቤት ወንድሞችና እህቶች ጋር ደም ሊያቃባው ላይ ታች ማለቱን ቀጥሏል፡፡

እንደነዚህ ያሉ ትላልቅ ጉዳዮች መነሻቸው የህዝብ ጥቅም መሆን ሲገባው ኢህአዴግ ግን ከህዝብና ከሀገር ጥቅም ይልቅ የስልጣንንና የፖለቲካን ጥቅም በማስቀደም በ21ኛው ክ/ዘመን ሊፈጸም በማይገባው የጦርነት አዙሪት ውስጥ ሊንቦራጨቅ ሲዳዳው ይስተዋላል፡፡ ዘመኑ የሚፈልገውንና የሚፈቅደውን የጋራ የጠንጴዛ ዙሪያ ውይይት መቅደም ሲገባው ከህዝቡ ጀርባ በሚጠነስሰው የስልጣን ማራዘሚያ ጥንስስ ባሻገር ህዝባዊ ጥቅምና ጉዳቱ ሳይመዘን የሚኬድበት የመሰሪነት ስራ ትልቅ መዘዝ ይዞ ብቅ ማለቱ አይቀሬ እየሆነ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ምሁራን፤ የህግ ባለሙያዎች፤ኢንጀነሮች ፤ገበሬዎች ፤ የሃይማኖት መሪዎች በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዚህ ውሃ ግድብ ጥቅሙ ምን ሊሆን ይችላል? የውሃው ግድብ ገበሬውን ፤ነጋዴውን ፤በአጠቃላም የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዴት ሊያረጋግጥ ይችላል? ጉዳቱን በተመለከተ ፤መቼ ፤እንዴት ፤የት ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ምንም አይነት ጥናት ሳይደረግበት ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ በሚገባ ተዘርዝሮ ሊነገረው እና ሊያውቅ ሲገባው በድንገት አባይን እንገድባለን በማለት ዱብ እዳ የሆነ መርዶ አይሉት ፤አዋጅ አይሉት ፤ ብቻ መሀንዲሱም እኛው ፤ገንዘቡንም እኛው ፤ጉልበቱም እኛው ፤ሁሉም ነገር እኛው በማለት ለፈለፉበት ፡፡

በዚህ ውሃ ግድብ ምክንያት ከግብጽ እና ሱዳንም ሆነ ከተፋሰሱ ተጠቃሚ ሀገሮች እና ከዓለም ህብረተሰብ ሊመጡ የሚችሉት ጉዳቶች በቀጥታም ይሁን በሌላ መልኩ የመጀመሪያው ተጎጂ የሚሆነው ህዝቡ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በህግ በኩልም ኢትዮጵያዊያን የህግ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን የውሃን አጠቃቀም ህግ፤ የአለም አቀፉን የውሃ ህግ ሳይመክሩበት ፤ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርገውን ጥናት ሳይደረግበት በሆያ ሆዬ የተፈጸም ስህተት አንድ ነው :: በፖለቲካው መስመርም ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በሚገባ ለማብራራት እና የሁለቱንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ጥያቄውን በሚገባ ለመመለስ የሚችሉ በዲፕሎማሲው መስክ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ሳይመረጡ በደመ ነፍስ የተፈጸመ ስህተት ሁለት ነው::

ኢህአዴግ ሁሌም እንደለመደው የኢትዮጵያን ህዝብ ውሸት እየመገበ ቢሰነብትም ከሁለት ዓመት የአባይን እገድባለሁ እንቅስቃሴ በኃላ ከውሸቱ ባሻገር እውነተኛው የግብጽ እና የአባይ ተፋሰስ ተጠቃሚ ሀገሮች ቅሬታ ቁልጭ ብሎ ኢህአዴግ ፤የግብጽ ህዝብና እና መንግሰት ተፋጠው ይገኛሉ፤፡ ኢህአዴግ ግን የግብጽ መንግስት እና ሌሎችም የተፋሰሱ ሀገሮች ግድቡን እንዲገደብ ፈቃደኛ መሆናቸውንና እርዳታም እንደሚያደርጉ ለህዝቡ የተለመደውን የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ውሸት ሲመግበው ነበር ስህተት ሶስት ማለት ይህ ነው ::

የህዝብን ምክር ያልተቀበለው እና ስልጣንን ዘላለማዊ አድርጎ በማለም የተነሳው ወያኔ ኢህአዴግ መንግስት ከትንሽ ጊዜ የውሸት መወራጨት በኃላ ሸክሙን ወደ ህዝቡ መወርወሩ አይቀሬ ነው፡፡ ባልመከረበት እና ባላወቀው ችግር ውስጥ የሚዘፈቀው ህዝብ የሚደርስበት ችግር ስህተት አራት ተብሎ ይያዝ::

ኢህአዴግ አንድ ካልተረዳው እውነት ጋር መጋጨቱን የተረዳው አይመስለኝም፤ ከጫካ እስከ አዲስ አበባ መቆጣጠር እና ያለፉት 22 ዓመታት የተጠቀመበት የውሸት ምላስ ራሱን እንደሚጎዳው እና ህዝቡም በውሸት መኖር እንደሰለቸው

አለመረዳቱ ነው፤፡ ዛሬም በደደቢት ቅኝት እየዘፈነ እስክስታ ይመታል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ በድሮ የታሪክ መነጽር በመመልከትም ህዝቡን እንደመራሁት ይከተለኛል ብሎ ያስባል፤፡ ስህተት አምስት ብለን አንዘግበዋለን::

የኢህአዴግ መነሻም ህዝቡ እርስ በራሱ ላይስማማ ይችል ይሆናል እንጂ ሀገርን የሚጎዳ ወራሪ ጠላት በመጣ ጊዜ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ሆ ብሎ በመውጣት የሀገሩን ጠላት በጋራ በመመከት አሳፍሮ የሀገሩን ዳር ድንበር እና ነፃነቱን ያስከብራል የሚል እምነት እንደሚኖረው አያጠራጥርም ስህተት ስድስት ብለን አንቆጥራል::

የአትንኩኝ ባይነት የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ይከወን የነበረው በአንዲት ኢትዮጵያ ፤ በአንዲት ሰንደቅ አላማ፤ በአንድ ህዝብ በአንድ መሪ፤ በእውነተኛ የሀገር እና የህዝብ ስሜት በተከፈለው የህይወት ዋጋ መሆኑ እና የሚገኘውም ድል የኢትዮጵያ ህዝብ ድል መሆኑ በማያወላውል መልኩ የተረጋገጠ በመሆኑ ነው፤፡

ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ በቋንቋ ከፋፍሏል፤ አንደኛውን ቋንቋ ተናጋሪ በአንደኛው ላይ በማስነሳት እንዲገዳደሉ አድርጓል፤ ደም አቃብቷል፤ ቂም አያይዟል አንደኛው ወገን የአንደኛውን ንብረት እንዲዘርፍ አድርጓል፡፡ ለአንደኛው ወገን በማድላትም አንደኛውን ጎድቷል፡፡ ብዙዎች ህይወታቸውን፤አካላቸውን የሰጡለትን ሰንደቅ አላማ ጨርቅ ነች በማለት አዋርዷል፡፡ በመሃሏ ላይም ድሪቶ ለጥፏል፡፡ ለእያንዳንዱ ቋንቋ ተናጋሪም ሰንደቅ አላማ አድሏል፤፡ ሀገሪቱንም በቋንቋ ሸንሽኗል፡፡

ኦሮሞውን የኦነግ ተከታይ /አቀንቃኝ/ ደቡቡን የሲዳማ ነፃ አውጪ አቀንቃኝ /ተከታይ/ ሱማሌውን የኡጋዴን ነፃ አውጪ ሀይል አብሊ ፤አጠጪ፤አማራውን ነፍጠኛ /የመኢአድ አባል/ ወዘተ በማለት ገድሏል ፤አስሯል ከሀገር አሰድዷል:: እንዲሁም ሀገር አስገንጥሏል ፤ወደብ አስወስዷል፤ ወጣቱን አደገኛ ቦዘኔ በማለት የወጣቱን ክብር ነክቷል፤ አዋርዷል፤ ጣት ቆርጧል፤ በጅምላ አስሯል፤ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ንፁሀንን በእሩምታ ጥይት ገድሏል፤ በኑሮ ውድነት ህዝብን አስርቧል፤ የአማራውን ህዝብ ከሚኖርበት ክልል አፈናቅሏል: ንብረት ዘርፏል፤ የጋንቤላን ህዝብ መሬት ከህዝቡ ነጥቆ ለውጭ ሀገር ነጋዴዎች ሸጧል፤ህዝቡም ተሰዷል፤ጋዜጠኞችን፤ የፖለቲካ መሪዎችን፤ የሃይማኖት መሪዎችን አስሯል፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ላይ አባሯል፡፡ በእነዚህ በተጠቀሱት ትንሽ ምክንያቶች ብቻ ኢህአዴግ የህዝብ ድጋፍ የለውም፡፡

ሀገር አስገንጥሎ ሀገር እመራለሁ የሚለውን የወያኔ ኢህአዴግ ከ1991ዓም ሻቢያ ወረረኝ በማለት ለህዝብ ባሰማው የድረሱልኝ ጥሪ መሰረት እና ህዝቡ ያለፈቃዱ በጉልበት የተገነጠለችውን ሀገሩንና ያለውዴታው የተወሰደበትን ወደቡን በአጋጣሚው አስመልሳለሁ በሚል እምነት እና የወያኔንም የውሸት እምባ በማመን ጭምር ያለ ስልጠና ፤ያለ ዝግጅት ፤ያለ እቅድ ሆ ብሎ የወጣውን ወጣት በገፍ በመማገድ የተገኘ ውጤት ባይኖርም ለጊዜውም ቢሆን የሻቢያን ወረራ ለመግታት ችሎ ነበር ፡፡

ህዝብ ያልደገፈው መንግስት የትም ሀገር ቢሆን አሸንፊ ሆኖ አያውቅም ፤ሊያሸንፍም አይችልም፡፡ ደርግ ወደ መጀመሪያዎቹ አመታት ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ተቀባይነትን አትርፎ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው ፡፡ የአገዛዝ ዘመኑ እየረዘመ በሄደ ጊዜ ግን ወጣቱን እያነቀ ፤ከወላጆቹ ፊት እያስገደደ ለብሄራዊ ውትድርና እንዲሁም ለመደበኛ ወታደርነት በሚያዘጋጅበት ጊዜ ህዝቡ ተማረረ፡፡ ወጣቱም በሀገሩ እንደሌባ እና ወንበዴ ተሳዳጅ ሆነ፡፡ ያ በግድ እየታነቀ ያለፍላጎቱ ወደ ጦር ሜዳ የዘመተው ወጣት መሳሪያውን እንደተሸከመ ፊቱን አዙሮ ወደ ቤተሰቦቹ መቀላቀልን መረጠ እንጂ ደርግ እንዲያሸንፍ አላስቻለውም:፡ ድልም ሆነ ውጤት አልተገኘም፤፡ ደርግ በመጨረሻም ህዝባዊ ጥላቻን አተረፈ እንጂ ህዝባዊነቱን ቀጥሎ የህዝብን ፍቅር አላገኘም:፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት የሚያውቀው የአባይ ግድብ ገንዘብ አዋጣ የሚለውን አስገዳጅነት እንጂ በግድቡ መሰራት እና አለመሰራት መካከል ያለውን እሰጥ አገባ ወያኔ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጀርባ ሆኖ የሚያከናውነው በመሆኑ ህዝቡ የሚያውቁበት መንገድ የለውም፡፡ ነገር ግን በዚህ ግድብ ግብፃዊያንና ሱዳናዊያን እንዲሁም ሌሎቹ ተጠቃሚ ሀገሮች ደስተኞች አይደሉም፡፡ እንዴውም በግልጽ ግደቡ ይቁም የሚል ግልጽ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፤፡ በኢህአዴግ በበኩል ደግሞ ይህንን ትልቅ ጉዳይ ከህዝቡ ደብቋል:: ለምን? የአባይ ግድብ ጉዳይ በመጀመሪያውንም ህዝባዊ ጥቅሙ ሳይሆን ስልጣንና የፖሊቲካን ጥቅም ያለመ ጅምር ስለነበር ኢህአዲጎች ስለሀገራዊ ጥቅሙ አልተጨነቁም ነበር:፡ ህዝቡም እውነት መስሎት የመጀመሪያ ዙር የገንዘብ መዋጮ ሲያደርግላቸው እነሱም የእውነት መስሏቸው እንደነበር

በግልጽ ታይቷል፡፡ የአባይ ግድብ መነሻውም ግን ጥቅም አልነበረም የመነሻውም ነጥብ የነበረው የምዕራብ አፍሪካ ህዝባዊ አመጽ እና በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ተነስቶ የነበረው የነፃነት ትግል ያስጋቸው የወያኔ መሪዎች እጣ ፈንታው የእኛም መሆኑ አይቀርም በሚል በድንጋጤ የተፈጠረ የኢትዮጵያን ህዝብ ቁጣ ለማብረድ የተጠቀሙበት የግድብ ስራ ነው ፡፡ ኢህአዴጎች ያቀዱትን የትራንስፎርሜሽንና እድገት እቅድ ስራ እርግፍ አድርገው በመተው ሁሉም ካድሪዎችና ባለስልጣናት ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ድረስ ለሁለት አመት ያህል በብር ልመና ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡

ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው የኢህአዴጉ ጠ/ሚኒስተር የሆኑት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለፓርማ ተብየው ባቀረቡት የአመቱ የበጀት ሪፖርት ላይ በግብርናውም፤ በኢንዱስትሪውም ፤በውጭ ንግዱም ፤በሀገር ውስጥ ባለው የስራ አፈፃፀም እና እድገት በዘንድሮው አመት ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን በግልጽ አቅርበዋል፡፡

ለጊዜውም ቢሆን በአባይን እንገድባለን በሚል የተጠቀሙበት የህዝብን ቁጣ ማብረጃ ዘዴ ኢህአዲጎች ባገኙት ፋታ እንደተደሰቱ እና አንዳንዶቹ ባለስልጣናትም እንደተናገሩት ሌሎች ሀገሮች የተነሳው አመጽ ኢትዮጵያን እንደማያሰጋት እንደምክንያት የሚያቀርቡትም ማስረጃ ህዝቡ በዲሞክራሲ እየተጠቀመ የፈለገውን እየመረጠ መሆኑ እና የእድገቱ ተጠቃሚም እየሆነ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡:

ለጊዜው የበረደው የህዝብ ቁጣ ግን ኢህአዴግ እንደሚለው ህዝቡ የዲሞክራሲ እና እድገት ተጠቃሚ ሳይሆን ቀፍድዶ የያዘው የኑሮ ውድነት ፤ድህነት፤ አንድ ቀን እንኳን ስራ ባቆም ልጆቼን ምን አቀምሳቸዋለሁ በሚል የነፃነት እና የዲሞክራሲ ጥያቄውን እንደተዳፈነ እሳት በልቡ ውስጥ ሸፍኖ አስቀመጠው እንጂ መፍትሄ በመገኘቱ ቁጣውን አላበረደውም :: ኢህአዴግና ህዝቡም እንደመሪ እና ተመሪ የሚያገናኛቸው አንዳችም መስመር የለም:: ምክንያቱም ህዝቡ የሚጠይቀው ሌላ ነው፡፡ ኢህአዴግም የሚሰጠው መልስ ሌላ ነው፡፡

ለምሳሌ የኑሮ ውድነቱ ህዝቡ ከሚችለው አቅሙ በላይ ሆኗል፡፡ ፍትህ ተዛብቷል፤ የህዝቡ ሰብአዊ መብት ተረግጧል፤ የህግ በላይነት ተጥሷል፤ ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው የመኖር ህገ-መንገስታዊ መብታቸውን ተነፍገዋል፤ጋዜጠኞች በነፃነት በመፃፍ በመናገር ፤ለህዝብ መረጃ የመስጠት ህገመንግስታዊውንም ሆነ በተፈጥሮ ያገኙትን ነፃነታቸውን ተነጥቀዋል፤፡ መንገስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው አንደኛው በአንደኛው ጣልቃ በመግባት ስራውን ሊያሰናክል አይችልም የሚለው የህገ መንገስት ድንጋጌ ተንዷል፡፡

በአጠቃላም እነዚህንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ያነሱ የፖለቲካ መሪዎች ፤ጋዜጠኖች፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የኢህአዴግ ነጠላ ዜማ በሆነው የሸባሪነት ክስ እየተለጠፈባቸው ወደ ወህኒ ተወርውረዋል፡፡ ታዲያ ይህ ባለበት ሀገር ህዝባዊ ቁጣው ተዳፍኖ ይሆናል እንጂ እንዴት ሊጠፋ ይችላል?

ኢህአዴግ አልገባውም እንጂ ከህዝቡ ጋር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተለያየው ሚያዝያ 30 ቀን 1997ዓም ነው፡፡ አብዩት አደባባይ የተደረገው የኢህአዴግ የድጋፍ ሰልፍ እና ለቅንጂት የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ሚያዝያ 29 እና 30 1997ዓ/ም ይህ ድጋፍ ግንቦት 7 ቀን የህዝብ አሸናፊነት በድል የተጠናቀቀበት በቃህ ብሎ ድምፁን የነፈገበት፡፡ ይህንን ተከትሎ ኢህአዴግ በእልህና በቁጭት ወታደሩን በማዝመት በከፈተው የእሩምታ ተኩስ በመላ ሀገሪቱ ትልልቅ ከተሞች እና በመላው ሀገሪቱ የቀበሌ ገበሬ ማህበራት ህዝቡ ላይ የወሰደው የግድያ እርምጃ የፀባቸው የመጨረሻ አደረገው እንጂ ህዝባዊ ፍቅርን አላስገኘለትም፡፡

ኢህአዴግ በሀገር ውስጥ ያለውን የህዝብ ችግር ሳይቀርፍ ብሄራዊ መግባባት እና እርቅ ሳይፈጽም ያሰራቸውን የህሊና እስረኖች ሳይፈታ፤ ኢርቶዶክስ ተዋህዶን እምነት ምንጭ የሆነውን የዋልድባ ገዳም መነኮሳትን ወደ ቦታቸው ሳይመልስ፤ የሙስሊም መፍትሄ ወይም እርቅ አፈላላጊ እስረኖችን ሳይፈታና ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት እጁን ሳያወጣ ፤የናቀውንና ያስራበውን ህዝብ ይቅርታ ሳይጠይቅ፤ ህዝቡን ከደረሰበት የሞራልና የህሊና ቁስል ጉዳት ሳያገግም ፤እናም በድጋሚ የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ በአሁኑ ሰዓት ከግብጽ ጋር እሰጥ አገባውን ቀጥሏል፡፡

ይህ የፈረደበት ህዝብ የሚደርስበትን ጭቆና በሰላማዊ ትግል እንዳያስወግድ ሌላ ዙር ቁጣ ማብረጃ ድግስ እየተደገሰለት መሆኑን የሚያመላክቱ ፍንጮች ብቅ ማለታቸው እየተስተዋለ ነው፡፡ ከግብጽና ሻቢያ ጋር የሚደረጉት

ንትርኮች የዚሁ ማሳያ ምልክቶች ናቸው፤፤ ኢህአዴግም ግብጽና ሌሎች ሀገሮች አባይን ገድቤ እንዳልጠቀም ጦርነት ሊያነሱብኝ ነውና ህዝቡ እንደተለመደው ትብብሩን እንዲያደርግልኝ ማለቱ አይቀርም፡፡

የዘንድሮውንም የህዝብ ቁጣ በዚህ መልኩ ለማሰለፍ የሚፈልገውም በጦርነት ላይ ስለሆንኩ በሀገር ቤት የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ህገ -ወጥ ስለሚሆኑ ህዝቡ ይህንን አውቆ ከድርጊቱ እንዲታቀብ የሚል አዋጅ መታወጁ አይቀሬ ይሆናል፡፡ በመቀጠልም ህዝቡ ወራሪወችን ለመመከት ከኢህአዴግ ጎን መሆኑን የሚያሳይ ድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በግድ ወጥቶ እንዲያሳ ይገደዳል፡፡ ለጦርነትም ዝግጁ ነው ተብሎ በተለመደው ውሸት ይደሰኮራል፤፡

ነገር ግን ከግብጽ ጋር የሚደረገው እሰጥ አገባ እና የሚከተለው ጦርነት ወያኔ ከሻቢያ ጋር እንዳደረገው የአንድ ሰሞን ጦርነት ሆኖ የሚያልቅ አይሆንም፤፡ መዘዙም የተፋሰስ ሀገራት እና ብሎም የአረቡን ሀገራት ጭምር ሊያነሳሳ የሚችል በመሆኑ መዘዙ በቀላሉ የሚፈታ አይሆንም:፡ ምክንያቱም የአባይ ውሃ ለግብፆች እና ለሌሎችም የህልውና ጉዳይ ነው:: የውሃው ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያም ይህንን ውሃ ገድባ ለህዝቡ ጥቅም ማዋሏ መብቷ ነው፡፡ እነዚህ የሁለቱም ሀገሮች የጥቅም ጉዳዮች በቀላሉ ሊታረቁ የሚችሉ አይሆኑም፡፡ ኢህአዴግ ከህዝብ ጥያቄ ለማምለጥ እመር በማለት ዘሎ የገባበት “ የነብር ሰርግ ” እና ከህዝብ ደብቆ የሰራው ደባ በመሆኑ ዞሮ ዞሮ የህዝቡን ተሳትፎ መጠየቁ ስለማይቀር በሀገር ውስጥ ካለው ህዝብ ፤ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፤በውጭ ሀገር ሆነውም ይሁን ጫካ ገብተው ፍልሚያ ከሚያደርጉት ጋር ሁሉ የጠረፔዛ ዙሪያ ውይይት በመጀመር ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ ይኖርበታል፡፡

ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኢትዮጵያ የአባይን ግድብ ሰርታ ተጠቃሚነቷን ልታረጋግጥ የምትችለው ፡፡ ያለበለዚያ ህዝቡ እንደከዚህ ቀደሙ ሆ ብሎ በመውጣት ህይወቱን፤ ንብረቱን የሚገብርበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ ከሻቢያ ጦርነት በኃላ ያገኘው ርሀብን ፤ጥማትን፤ ስራአጥነትን፤ ውርደትን፤ጥይትን በመሆኑ በመጀመሪያ የኔ የሚለው የሚያምኑበት መሪ ይፈልጋል፡፡ እንጂ የሰጠውን ድምጽ ነጥቆ እስር ቤት የወረወረውን፤ የገደለውን መሪ አምኖ ለብሄራዊ ጦርነት የሚዘጋጅበት ምክንያት አይኖረውም ፡:

በአንድ ሌሊት ታልሞ ኢትዮጵያን ህዝብ የጭቆና ይቁም ጥያቄ ለማስቆም ያለጥናት በድንገት የተጀመረው የአባይ ግድብ ስራ እነ አቶ መለስን አባይን የደፈረ ጀግና ውዳሴ ከመስጠት ውጭ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፋይዳ በሚሰጥ መልኩ እየተሄደበት አይደለም:፡ ለህዝቡም የሸረቡለት የተንኮል ገመድ ጊዜውን ጠብቁ ፍንትው ብሎ እየወጣ ነው፡፡

የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሁሉጊዜም እንደተናገሩት እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለውን ሟርታቸውንም እውን ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ህዝቡ ልብ ሊለው ይገባል፡፡ ህዝቡን በሀገር ውስጥ በቋንቋ በመከፋፈል እና ሀገሪቱን በክልል በመሸንሸን 22 ዓመት ሙሉ የሀገሪቱን አንድነት ንደዋል፡፡ ለዘመናት የተገነባውን የህዝብ ፍቅር አፍርሰዋል፡፡ አሁን ደግሞ እርሱ /ህዝቡ/ ሳያውቀውና ሳይመክርበት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ሊያላትሙት ነው፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ለመፍረስ የቀራት ነገር ምንድን ነው?

በሻቢያ ጦርነት ጊዜ የኢትዮጵያ ወጣቶች በግፍ ተማግደው ሀገራቸውን ለማስከበር የከፈሉትን ዋጋ ኢህአዴግ የሚባለው ቡድን ለግል ዝና እና ለስልጣን ማራዘሚያነት እንደተጠቀመበት እና የማያልቀውን ውሸታቸውን በመደጋገም እውነት ለማስመሰል እንደሞከሩት “በባድመ ጦር ሜዳ ያገኘነውን ድል በፍትህ አደባባይ በአለም አቀፉ ሄግ ፍ/ቤት ደገምነው” ሻቢያ ተፈረደበት ባድመ እና አካባቢው ሁሉ የኢትዮጵያ መሆኑ ተረጋገጠ በማለት አለምን ያስደመመ ውሸት እንደተናገሩት አቶ ስዩም መስፍን፡፡ አሁንም ይህ ውሸት በተደጋጋሚ በአባይ ግድብ ጅማሮ ሰሞን የግብጽን መሪዎች በቴሌቭዥን እያሳዩ ኢትዮጵያ ያደረገችውን የአባይን ውሃ ግድብ የግብጽ እና የሱዳን መሪወች ሙሉ በሙሉ ደገፉት ለግድቡም ስራ የሚውል የገንዘብ ፤የሰው ሃይል የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉልን አረጋገጡ እየተባለ እንዳልተዋሸን ሁሉ በአሁኑ ሰዓት ግን እውነተኛው የግብጽ እና የሱዳን አቋም ፍንትው ብሎ በመውጣት ኢህአዴግ ከህዝቡ በመደበቅ ብቻውን ላይ እና ታች ሲራወጥ ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ሬዲዮኖች እንዳለቆቻቸው ቢዋሹም አለም አቀፍ እውነተኛ ሚዲያዎች ግን እውነቱን ግልጽ ባለ መልኩ የግብጽ እና ሱዳንን አቋም ለአለም ህብረተሰብ እየነገሩት ይገኛሉ፡፡

የአባይ ግድብም ጋሬጣ እንደተጋረጠበት እና የኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ ችግር ውስጥ የገባ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ትልቅ የሆነ ሀገራዊ ጉዳይ ከህዝቡ በመሸሸግ አድበስብሶ ለማለፍ ቢሞክርም የግብጽ ህዝብ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ዙሪያ ተቃውሞ ሰልፍ በመውጣት የአባይ ግድብ ስራ እንዲቆም ጥያቄአቸውን አቀረቡ፡፡ የግብጽ መንግስትም ጥያቄአቸውን ተቀብሎ ተቃውሞውን እያሰማ ነው፡: የኢትዮጵያ ህዝብ ግን መብቱ የሆነውን የአባይን ውሃ ገድቦ የመጠቀም ስራው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እንኳን የሚያውቅበት መንገድ የለውም:: ይልቁንም ኢህአዴግ ሌላ የማደናበሪያ የውስጥ አጀንዳ በመክፈት የህዝቡን ትኩረት ሁሉ ወደዚያ እንዲሆን አድርጓል::ሀገሪቱን ይዟት እየሰጠመ ያለውን ስር የሰደደ የባለስልጣናት ሙሰኝነት ለማጥፋት በሚልም የሚጠየቁትን በመተው እንጭፍጫፌዎቹ ላይ በማነጣጠር ጨዋታዊ ድራማውን እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ኢህአዲግ ማወቅ የሚገባው ቁም ነገር የአባይ ግድብም ይሁን፤ ሙስናም ይሁን ፤ጦርነትም ይሁን ፤ምርጫም ይሁን ማስፈራራት ይሁን ፤እስራት እና ግድያም ይሁን በድል የሚጠናቀቁትም ይሁን ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው የህዝብ ጥያቄ ህዝቡ በሚፈልገው መልኩ ምላሽ ሲያገኝ ብቻ ነው :: ከዚህ ውጭ የሚደረጉት ማናቸውም ነገሮች ሁሉ ጊዜያዊ መብረድን እንጂ ቁጣን ፤ለነፃነት የሚደረግ ትግልን ሊያስቆሙ አይችሉም፡፡

የመንገድ ስራም ሆነ ፎቅ ግንባታ የነፃነት ጥያቄን አያስቆምም፡፡ አፈናና ጭቆናም የዲሞክራሲ ጥያቄን አያስቀርም፡፡ ወታደርና የፖሊስ ብዛትም የህዝብን ማዕበል አይገታም:፡ የቴሌቭዥንና የሬድዮ የውሸት ኢኮኖሚ እድገት የህዝብን ረሀብና እና ጥማትን አያስታግሱም፡፡ አንድ ግለሰብ ሶስት ቢሊዮን ብር  እየዘረፈ በመዋጮ የአባይ ግድብ አይሰራም፡፡ የህዝቡ የትግል መነሻውም ሆነ ማጠንጠኛው ጭቆናና አፈናን መቃወም እና በሸናፊነት መወጣት ይኖርበታል:: ማናቸውም የህዝብ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ወይም ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ጭቆና ከህዝብ ጫንቃ ላይ ሲወገድ ብቻ ነው፡፡ የአባይ መዘዝ የህዝባችንን ስቃይ እንዳያራዝመው ከወዲሁ ህዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠውን ቅድሚያ በመስጠት ሰላማዊ ትግሉን መቀጠል አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.