ከተግባራዊ የፖለቲካ እንቅስቅሴ በፊት የነጠረ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ወሳኝነት

 

ይድረስ ለኢንጂነር ይልቃል (የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት)

ከሸንቁጥ አየለ(shenkutayele@yahoo.com)

በላይፍ መጽሄት ላይ የሰጠህዉን (ይቅርታ ወጣት ስለሆንህ አንተ እያልኩ ልጥራህ) ቃለ መጠይቅ ካነበብኩ ብሁዋላ ሁለት የተለያዩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ  ስለፈለግሁ ይሄን ጽሁፍ ላንተ ለማድረስ አዘጋጀሁ:: አንደኛዉ መልዕክቴ አድናቆት ሲሆን የዚህ የአድናቆቴም ምንጭ አንተ በወጣት እድሜህ በሀገሬ ፖለቲካ እና በህዝቤ መጻኢ ዕድል ላይ ያገባኛል ብለህ መነሳትህና ያቅምህን ልታበረክት ደፋ ቀና ማለትህ በራሱ የሚያስመሰግንህ መሆኑን መግለጽ ነዉ:: ብዙዉ ትዉልድ ከህሊናዉ ይልቅ ሆዱ ሲያሸንፈዉና በማያምንበት ነገር ዳክሮ ዳክሮ ሲታክተዉ በየስርቻዉ ተቀምጦ እንዲሁም ዘወር ብሎ አስገዳጆቹ እንደሌሉ ሲያቅ እዚህ የማይረባ የፖለቲካ ፓርቲ ዉስጥ የገባሁት እኮ የሆድ ነገር/የስራ ጉዳይ/ ሆኖብኝ ነዉ ማለት የዕለት ከዕለት ትዕይንት በሆነበት አገር ዉስጥ ያመንኩበት የፖለቲካ እይታ ይሄ ነዉ ብለህ በራስህ መንገድ መሄድህና የዲሞክራሲን ጥሪ ለብዙሃን ወጣቶችማሰማትሕ በጣሙን የሚያስመሰግንህ ጉዳይ ነዉ::

ሁለተኛዉ የመልዕክቴ ጭብጥ ግን እከሌ የሚባል ጎሳ(ብሄር) ስለመኖሩ የሚያሳይ ማስረጃ የለም እነከሌ የሚባሉ ጎሳዎች/ብሄሮች ስለመኖራቸዉ ግን ማስረጃ አለ በማለት ያነሳህዉና ተያያዥነት ያላቸዉ ጉዳዮች ላይ የሰነዘርካቸዉ አስተያዬቶች ላይ ለወደፊቱ በማስተዋል ሊታረሙ የሚገባቸዉ ጉዳዮች እንዳሉ የሚያብራራ ነዉ:: እናም መልካም ንባብ::

በቃለ መጠይቁም ሆነ ወደፊት መመለስ ያለበት መሰረታዊዉ ጥያቄ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሄረሰብ ከጎሳ የፖለቲካ አደረጃጀት አጠር ዉስጥ ወጥቶ አገሪቱን ከመፍረስ እንዴት ሊታደጋት ይችላል? ኢትዮጵያዉያን ብሄሮች ማለትም ኦሮሞዎች: ጉራጌዎች : አማሮች: ትግሬዎች : ደቡቦች: አፋሮች: እንዲሁም ሌሎችም የልዩነት ታሪካዊ መሰረታቸዉን ሳይሆን የጋራ የታሪክ ጭብጣቸዉን እንዲያስተዉሉና በጋራነት ወደ በለጠ አብሮነት ዉህደት እንዲሄዱ ለማስቻል ምን የፖለቲካ ፍልስፍና ለዚህች ሀገር ይበጃል ብሎ ማንሰላሰል ቁልፍ የሆነዉ የዚህ ዘመን ምሁራን : ፖለቲከኛ እና ዜጋ ያልተመለሰና ያልተፈታ የቤት ስራ ነው:: በምን መልክ ወደፊት የጠለቀና የጸና ዉህደትን ለማምጣት እንችላለን ብሎ ማሰላሰል አገራዊ የፖለቲካ ፍልስፍና እናራምድ የሚል ሀይል ጥያቄ ነዉና በአንተ በኢንጅነር ይልቃልም ቢሆን መመለስ ያለበት ነጥብ ይሄዉ ነዉ:: የኢትዮጵያን አንድነት ጉዳይ ከአንድ ብሄር ጋር በማገናኘት ይሄ ብሄር በጎሳ ከተደራጀ አገር ይፈርሳል ብሎ መናገር ግን ታላቅ የፖለቲካ ዕጸጸ ነዉና ለወደፊቱ ይታረማል ብዬ የጠነከረ ተስፋ አለኝ::

በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ብቅ ጥልቅ የሚሉ ፖለቲከኞች የሌሉትን ብሄር መርጠህ ደርሰህ አክራሪ አማራዎች ብለህ ለመፈርጅ ተጣደፍህና መልሰህ ስጋት ገባህ መሰለኝ “ከአክራሪዎቹ አማራዎች እንዳታጣላን እንጅ” አልክ:: ሲጀምር አክራሪዎቹ አማራዎችን መፍራት እና እዉነትን መዉደድ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸዉ:: እዉነቱ አማራ የሚባል ብሄር የለም የሚል ከሆነ እሱን አጥብቆና አንጠርጥሮ መተንተን ይገባል:: አንዱን እዉነት ቆርጦ ጥሎ አንዱን እዉነት ደግሞ ደምስሶ በቆረጣ በማስወገድ አንድ እዉነት የምትመስል ጽንሰ ሀሳብን ብቻ አንስቶ ጉዳዩን አለባብሶ ማለፍ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነዉ:: የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን እርስ በእርስ አጫርሶ በመጨረሻም አገሪቱን አፈር አብልቶ ተከታታይ ትዉልድንም በአዉሎ ንፋስ እንደተመታ ደረቅ ሰንበሌጥ ስሩን ነቃቅሎት የሄደዉ በሶሻሊስትና በሶሻሊስት መካከል ምን ልዩነት ኖሮ ነዉ እርስ በእርስ የምንገዳደለዉ ብለዉ ለመጠየቅ ያልደፈሩ ወንድማማቾች በሁለት ፓርቲ ስር ታቅፈዉ የተጫረሱበት አገር ዉስጥ ነዉና ያለንዉ ለወደፊቱ ነገር ሁሉ በግብታዊነት ከመነገሩ በፊት በሰፊ እዉቀትና ትንታኔ ሊደገፍ እንደሚገባዉ ይሄኛዉ ትዉልድ አስተዉሎቱ ካለዉ ልብ ቢለዉ መልካም ነዉ::

ለምሳሌ “አማራ የሚባል ጎሳ (ብሄር) ስለመኖሩ የሚያሳይ ማስረጃ የለም፡፡ ልክ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ከዚህ ወጣ እዚህ ገባ እንደሚባለው አይነት ማስረጃ የለም፡፡” ብሎ መደምደም ምን ማለት ነዉ? ይሄ ሁሉ ብሄር (ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ) ባለበት አገር ዉስጥ አማራ የሚባለዉ ወገን ለብቻው ምንም የራሱ ማንነት ሳይኖረዉ እንዴት ሊኖር ቻለ? ዛሬ እንጂነር ይልቃል አክራሪ ያላቸዉ የአማራ ወገኖችስ ከየት መጡ? አንድ የሆነ የማንነት መሰረት ያልነበራቸዉ ወገኖች እንዴት ዛሬ እስከ አክራሪ አቁዋም ሊደርሱ ቻሉ? ዛሬ አማራ በደቡብና በቤኒሻንጉል ትናትና በኦሮሚያ ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ ወገኑ እየተለየ ለምን ተሳደድ ? ለምንስ ግፍና በደል ደረሰበት ? ይሄን የሚያደርጉት ሰዎችስ አማራ የሚባለዉን ህዝብ/ወገን/ጎሳ/ብሄር ነጥለዉ በሚያጠቁበት ጊዜ ምን የተለዬ ማንነት ያለዉን ወገን ነዉ እያነጣጠሩ የገፉት/የገደሉት? አንተ ተጣድፈህ ወደ ደመደምከዉ ድምዳሜ ከመሄድህ በፊት ከላይ ያነሳሁልህን ጥያቄ መልስልኝ:: አማራ የሚባል ብሄር የለም በማለቴ ኢትዮጵያዊነትን አራማጅ የሚል ዝነኛ ፖለቲከኛነትን አተርፋለሁ ካልክ ግን ፈጽሞ አታልመዉ:: ያንን ከማንም ልብ ዉስጥ አታገኘዉም:: የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ በጣም ብልህና አስተዋይ ህዝብ ስለሆነ በወደፊት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችህ ዉስጥ እዉነቱን ብቻ መንገር አለብህ:: የያዝከዉ እዉነት እዉነትም እዉነት ከሆነ በታላቅ አክብሮት ይሰማሃል ብሎም ይከተልሃል:: ካላወቅህዉም ይሄ ነገር ጥቂት ምርምር ላድርግበት ብለህ ጊዜ እንደሚያስፈልግህ ነግረህ ለጊዜዉ ግን የመረጃ እጥረት እንዳለብህ እዉነቱን መናገር ነዉ::

በቅን መንፈስ  ቃለ መጠይቅህን ሳነበዉ ጭንቀትህ ገብቶኛል:: የአንተ ጭንቀት በራስህ አንደበት እንዲህ የሚል ሆኖ ይገኛል “አማራው በጎሳ እንዲታጠር ከተደረገም ኢትዮጵያ አለቀላት ብዬ ነው የማምነው፡፡” ይህ ጭንቀትህ የእኔም ጭንቀት ነዉ:: የእኔ ጭንቀት ግን በአማራ ላይ የታጠረ አይደለም:: የሚያስጨንቀዉ ነገር ካነሳህዉ ነገር የሰፋ ነዉ::ማስተዋሉ ያልተነጠቀዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚያስጨንቀዉ ጉዳይ እያንዳንዱ ብሄር በጎሳ እንዲታጠር ከተደረገ ኢትዮጵያ አለቀላት የሚል ነዉ::

እያንዳንዱ ብሄር በጎሳ እንዲታጠር ቢደረግስ ኢትዮጵያዉያንን ምን ያስጨንቃቸዋል የሚል ካለ ጥቂት መአብራሪያ ብቻ የጉዳዩን አስጨናቂነት ይገልጸዋል:: በብሄር ስም የተደራጁ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ከእነሱ ብሄር ዉጭ የሆኑ ወገኖች ሲጎዱና የመብት ጥሰት ሲደርስባቸዉ የሚታወቁበት አንድ ዝነኛ መለያ አላቸዉ :- ስሌላዉ ምን አገባኝ የምትል አባባል:: ምናልባት በብሄር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥላ ስር በአባልነት የተጠለሉ ግለሰቦች በባህሪያቸዉ ጥሩዎችና ለሰዉ ሁሉ አሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ:: ሆኖም ከእነሱ ብሄር ዉጭ ሌሎች ወገኖች ሲጎዱ እንደ ፖለቲካ አቁዋም የሚወስዱት አቁዋም አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ቆመን ለምን ይሆን ስንል እንድናስብ የሚያስገድደን ነዉ:: በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ላይ ብቅ በማለት በብሄር ፖለቲካ ስር የተጠለሉ ሰዎች (ተቃዋሚዎቹም ሆኑ ገዥዎቹ) ስለ ሌላዉ ኢትዮጵያዊ መጎዳት የሚስጡት በጣም የለዘበ መልዕት ይህ ጉዳይ እኛን አይመለከተንም የሚል ነዉ:: ብዙ ጊዜ ግን የሌላዉ ብሄር መገፋት ለእነሱ ፌሽታና ደስታ ነዉ:: እናም ጥያቄ ትጠይቃላችሁ :- እነዚህ ሰዎች ስለ እዚህኛዉ ወይም ስለዚያኛዉ ኢትዮጵያዊ የማያገባቸዉ ከሆነ: የነሱ ብሄር ሲጎዳ ብቻ ከሆነ የሚቆጩት ለምሆኑ የጋራ ኢትዮጵያዊነት መተሳሰሪያና መቁዋጠሪያዉ ምን ሊሆን ይችላል? የብሄር ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመሰርቱ የብሄራቸዉን ብዙሃን ድጋፍ ለማግኘት ይታገላሉ:: የብሄራቸዉን ብዙሃን ድጋፍ ለማግኘት በብሄራቸዉ ፊት ታምር ፈጣሪ ሆነዉ ይታያሉ:: የራሳቸዉን ብሄር ከፍ ከፍ ከማድረግ ጀምሮ የማይጨበጡ ተስፋዎችን እስከመጋት: የዚያን ብሄር ልዩነት ከማጉላት ጀምሮ የዚያን ብሄር የበላይነት እስከመስበክ ያሉትን የስነ ልቦና የጨዋታ ካርዶች ሁሉ ይመዛሉ:: ይባስ ብሎም እነሱ ከሌሉ የእነሱ ብሄር እንደሚጠፋ ይሰብካሉ ብሎም የብሄራቸዉ አባላት ከእነሱ ዉጭ አይኑ እንዳይመለከት ያስፈራራሉ::

ሆኖም በተመሳሳይ ጊዜ ዉስጥ እነሱ ለሀገር አሳቢም መሆናቸዉንም ለማሳዬት መከራቸዉን ያያሉ:: የማይመልሱት ጥያቄ ግን ለምሆኑ ሁለት ስለተለያዬ ህዝብ የሚጮሁ ፓርቲዎች የጋራ መተሳሰሪያቸዉ ምንድን ነዉ ? ሲባሉ ነዉ:: የመነሻ ፖለቲካዊ ራዕይዉ ስህተት ስሌት ላይ ቆሙዋልና በምንም መልክ በብሄር ፖለቲካ የተደራጅ ሀይል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዕኩልነት መምራት አይችልም:: ለዚህም ነዉ ከትንሽም ሆን ከትልቅ ወገን የተነሳ የብሄር ፖለቲካ አደረጃጀት አገር ሊያፈርስ ስለሚችል ዜጎችን ሁሉ የሚያስጨንቃቸዉ::

ኢንጅነር ይልቃል ይህን እዉነት በቃለ መጠይቁ ዉስጥ አልሳተዉም:: ሆኖም ትልቁን ሀገራዊ ጉዳይ ከአንድ ብሄር ጋር በማገናኘት ስህተት ሰራ:: ይሄዉም “አማራው በጎሳ እንዲታጠር ከተደረገ ኢትዮጵያ አለቀላት ብዬ ነው የማምነው፡፡” በማለት ዋናዉን ጭብጥ አሳነሰዉ:: ይህን ስጋትህን የምታስቀርበት መፍትሄ ስታፈላልግም ሌላ መሰረታዊ ስህት ሰራ::

ለምሆኑ አሁን ኢትዮጵያ አላለቀላትም? አማራ በብሄር ተደራጀም አለተደራጀም የኢትዮጵያ ህልዉና በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ያለቀላት ተመስላለች:: ኢትዮጵያዊነት ከብሄር ማንነት ያነሰ የባጣቆየኝ ጽንሰ ሀሳብ አልሆነም? ኢትዮጵያዉያን የጋራ መሰረታቸዉን አጉልተዉና አስፍተዉ ከማጠናከር ይልቅ ሁሉም በልቡ የየራሱን የብሄር ታላቅነት እያለመ የሌላዉን ብሄር ወደ ታናሽነት ለፈርጅ ደፋ ቀና በዝቶአልና::አንዱ ብሄር በሁሉ የሀገሪይቱ ክፍል ለመኖር መሬት ወራሪ: ደን ጨፍጫፊ: የእኛን ለም መሬት ነጣቂ : ድርቅ ጠሪ በመባል በሌላዉ ወገኑ ዘንድ ሲኖር ሰቀቀን ሆኖበታልና ገና ኢትዮጵያን ፍለጋ ብዙ ርቀት እንጉዋዛለን:: እናም ኢንጅነር ይልቃል “አማራው በጎሳ እንዲታጠር ከተደረገ ኢትዮጵያ አለቀላት ብዬ ነው የማምነው፡፡” የሚለዉን ስጋቱን ለመሸሽና ኢትዮጵያ እንዳትፈርስበት አንድ አጭር መዉጫ ቀዳዳና ማምለጫ አበጃጀ:: ይህ ቀዳዳና ማምለጫዉ ደግሞ “አማራ የሚባል ጎሳ(ብሄር) ስለመኖሩ የሚያሳይ ማስረጃ የለም፡፡ ልክ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ከዚህ ወጣ እዚህ ገባ እንደሚባለው አይነት ማስረጃ የለም፡፡” ሲል ደመደመ::

እዉነታዉ ግን እንዲህ አይደለም:: ለምሳሌ የትግሬና የጉራጌ ብሄር ከአማራ ብሄር የተለዬ ምንም ታሪካዊ የመነሻ መንደርደሪያ ማስረጃ የለዉም:: ስለሆነም ትግሬና ጉራጌ ከዚህ ወጣ እዚህ ገባ የሚባል ማስረጃ አለ ብሎ መደምደምና አማራ ግን እንዲህ የሚባል ማስረጃ የለዉም ብሎ መደምደም አላዋቂነት ነዉ:: የአማራ ታሪክ ከትግሬና ከጉራጌ ታሪክ ጋር ተሳስሮ የተዋቀረ በመሆኑ የተነሳ የትግሬና የጉራጌ ታሪክ ማስርጃ አለዉ የአማራ ታሪክ ግን ማስረጃ የለዉም ማለት ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጊዜአዊ አቁዋራጭ ፍለጋም ነዉ::

አንዱን እዉነት ቆርጦ መጣል ሌላዉን አንጠልጥሎ መሄድ ማለት ይሄ ነዉ:: የአማራ ህዝብ የታሪክ መነሻ ኢንጀነር ይልቃል እንዳልከዉም ከክርስትና ጋር የተቆራኘ ነዉ:: ይህ ማለት ግን የአማራ ህዝብ ጉዳይ በሶሽዎሎጂያዊና አንትሮፖሎጂያዊ መነጽር ሲቃኝ እንደ ትግሬዉ : ጉራጌዉ : ኦሮሞዉ የጋራ ማንነት የለዉም ተብሎ ሊደመደም አይቻልም:: አንትሮፖሎጂስቶች ብሄር ብለዉ የሚሰፍሩባቸዉን መስፈርቶች ሁሉ የሚያሙዋላ የጋራ መሰረት ያለዉም ብሄር/ህዝብ ነዉና:: የአማራ ህዝብ ታሪክ ከመላዉ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ታሪክ ጋር ምን ያህል የተሳሰር መሰረት ላይ የቆመ መሆኑን ለመገንዝብና ጠቅለል ያለ መረጃ ለማግኘት የሚከተለዉን ጽሁፍ እንድታነበው እጋብዝሃለሁ:: http://www.iwooket.com/wp-content/uploads/2012/09/The-Concept-of-Amhara-from-religious-name-to-ethinic-name.pdf

ሆኖም ይህ የአማራ ብሄር መኖርና አለመኖር ወይም የማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ብሄር መኖርና አለመኖር ወደፊት በሁሉም ኢትዮጵያዉያን ሙሉ ፈቃድ በጥልቅ የዉህደት መሰረት ላይ ለምትቆመዉ አንዲት ኢትዮጵያ ትልቅም ሆነ ታናሽ ቁም ነገር በዉስጡ የለዉም:: ለታሪክ ምሁራን: ለአንትሮፖሎጂስቶችና ለሶሽዎሎጂስቶች የእዉቀት መስክ ግን ጭብጥ ያለዉ የእዉቀት ክፋይ ነዉና እዉቀተን ማክበር ግዴታችን ነዉ::ነገ እጅግ የተዋሃድ እና ታላቅ ኢትዮጵያዊ ህዝብ መፍጠር የሚያልም ማንም ወገን ዛሬ ነገርን ሁሉ ባልጠራ እዉቀት ላይ ሊያቆም ከሞከረ መሰረታዊ ስህተት እየሰራ ነዉ::

አሁን ወደ ዋናዉ አስጨናቂ ነጥብ እንምጣ:: ከላይ እንዳነሳሁት ኢንጅነር ይልቃልን የሚያስጨንቀዉ ነገር እኔንም ያስጨንቀኛል:: በጊዚያዊ የጎሳ የበላይነት አብጠዉ የተነፉ ወገኖችና ማስተዋላቸዉ የተነጠቀ ሰዎች ካልሆኑ በቀር በርካታ ኢትዮጵያዉያንንም ማለትም ሁሉንም ብሄሮችን (ኦሮሞዎችን: ጉራጌዎችን : አማሮችን: ትግሬዎችን : ደቡቦችን: አፋሮችን: እንዲሁም ሌሎችንም ) የሚያስጨንቃቸዉ ጉዳይ እያንዳንዱ ብሄር/ጎሳ በየራሱ ፖለቲካዊ አጥርና ጉሮኖ እየታጠር ከእኔ በቀር ለኔ ብሄር አዋቂ የለም የሚለዉ ጉዳይና ኢትዮጵያዊነት ከብሄር ማንኔቴ ቀጥሎ የሚመጣ የባጣ ቆዬኝ ምርጫዬ ነዉ እያለ የሚቀናጣዉ አካሄድ ነዉ::

እንዲሁም ልክ የአማራዉ ብሄር በጎሳ መታጠር ለኢትዮጵያ መፍረስ ምክንያት እንደሚሆን ሁሉ የማንኛዉ ሌላ ብሄር (የኦሮሞዉ : የጉራጌዉ: የአፋሩ: የትግሬዉ :የደቡቡ : የአፋሩና ለሎችም) በጎሳ መታጠር ለኢትዮጵያ መፍረስ በቂ ምክንያት ነዉ:: ኢንጅነር ይልቃል እንደሚለዉ ግን “አማራው በጎሳ እንዲታጠር ከተደረገ ኢትዮጵያ አለቀላት ብዬ ነው የማምነው፡፡” ብሎ መሰረታዊዉን እዉነት ማድበስበስ ወይም ደግሞ አማራ የተለዬ አቅም ያለዉ ብሄር እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብና ወሳኝ የኢትዮጵያ አንድነት ጠባቂ እንደሆነ አድርጎ ለማሳዬት መሞከር ሌሎችን ብሄሮች መሳደብ ወይም የብሄር ፖለቲካ አቅምን ጥልቅ መህልቅ አለመረዳት ነዉ:: እንደዚህ ያለ አስተሳሰብ መሰረታዊ እዉቀት ላይ ያልቆም ስለሆነ ኢትዮጵያዉያንን ከማቀራረብ ይልቅ የሚያፈራቅቅ ነዉ:: ምክንያቱም ጎስኞችና ብሄረተኞች እንደሚሰብኩት አማራ የሚባለዉ ብሄር ከኢትዮጵያ አንድነት የተለዬ ተጠቃሚ እንደሆን በማንጸባረቅና በመናገር የአማራ ብሄር የሆኑ ወገኖች የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ሲያነሱ ሌሎች ኢትዮጵያኖች በጥርጣሬ እንዲመለከቱዋቸዉ የሚያደርግም ነዉና:: ሲዘልም አማራ የራሱ ሶሽዎሎጂካዊ ማንነት አለዉ ብለዉ ታሪክ እያጣቀሱ የሚናገሩ ወገኖችን በአክራሪነት መፈረጅ አጉል የገነነ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምድ ከእኔ በላይ የለም በማለት መቀናጣት ነዉ::

ይህ አካሄድም የኢትዮጵያ አንድነት ጭብጥ ከአማራ ህዝብ ጋር ብቻ የተለዬ ጉዳይ እንዳለዉ ስለሚያንጸባርቅ ብሄረተኛና ጎሰኛ ፖለቲከኞች አያችሁ አይደል እነ ኢንጂነር ይልቃል የሚሰብኩትን ስብከት በማለት ይጠቀሙበታል:: ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ወደሚወደዉና ወደሚናፍቀዉ ታላቅና ዉህድ አንዲት ኢትዮጵያን የማየት ራዕይ ለማምጣት የሚቻለዉ የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ከዚህ ወይም ከዚያኛዉ ብሄር ጋር የተገናኘ አለመሆኑን ማሳመን ሲቻልና ሁሉም ኢትዮጵያዉያን ብሄሮች በጎሳ ፖለቲካ ዉስጥ ገብተዉ እንዳይቀረቀሩ አስረግጦ ሁሉን ማስረዳት ሲቻል ብቻ ነዉ:: ብሄረተኛና ጎሰኛ የፖለቲካ አደረጃጀት ከኢትዮጵያ መንደር እንዲከስም የሁሉም ኢትዮጵያዉያንን ሙሉ ነብስ : ስሜት አዕምሮና ራዕይ የሚገዛ የፖለቲካ ፍልስፍና መከተል ብቸኛዉ አማራጭ ነዉ::ለዚህም ነዉ ከተግባራዊ የፖለቲካ እንቅስቅ በፊት የነጠር ፖለቲካዊ ፍልስፍና ወሳኝ ስለሆነ የነገ ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የሚያስጨንቀዉ ወገን ሁሉ አጠብቆና አጥልቆ ሊሰራበት የሚገባ ዋና ጉዳይ ነዉ የምለዉ::

መልዕክቴ ሲጠቃለል አንድ ጭብጥ አለዉ :- መሰረታዊዉ ጥያቄ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሄረሰብ ከጎሳ የፖለቲካ አደረጃጀት አጠር ዉስጥ ወጥቶ አገሪቱን ከመፍረስ እንዴት ሊታደጋት ይችላል? ኢትዮጵያዉያን ብሄሮች ማለትም ኦሮሞዎች: ጉራጌዎች : አማሮች: ትግሬዎች :

ደቡቦች: አፋሮች: እንዲሁም ሌሎችም የልዩነት ታሪካዊ መሰረታቸዉን ሳይሆን የጋራ የታሪክ ጭብጣቸዉን እንዲያስተዉሉና በጋራነት ወደ በለጠ አብሮነት ዉህደት እንዲሄዱ ለማስቻል ምን የፖለቲካ ፍልስፍና ለዚህች ሀገር ይበጃል ብሎ ማንሰላሰል ቁልፍ የሆነዉ የዚህ ዘመን ምሁራን : ፖለቲከኛ እና ዜጋ ያልተመለሰና ያልተፈታ የቤት ስራ ነው:: በምን መልክ ወደፊት የጠለቀና የጸና ዉህደትን ለማምጣት እንችላለን ብሎ ማንሰላሰል አገራዊ የፖለቲካ ፍልስፍና እናራምድ የሚል ሀይል ጥያቄ ነዉና በአንተ በኢንጅነር ይልቃልም ቢሆን መመለስ ያለበት ነጥብ ይሄዉ ነዉ:: የኢትዮጵያን አንድነት ጉዳይ ከአንድ ብሄር ጋር በማገናኘት ይሄ ብሄር በጎሳ ከተደራጀ አገር ይፈርሳል ብሎ መናገር ግን ታላቅ የፖለቲካ ዕጸጸ ነዉና ለወደፊቱ ይታረማል ብዬ የጠነከረ ተስፋ አለኝ:: ተከግባራዊ የፖለቲካ እንቅስቅ በፊት የነጠረ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ወሳኝነት በእዉቀት ቢጤን መልካም ነዉ::

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.