መስቀል ደመራ

የግማደ መስቀሉ ታሪክ
የግሸን ማርያም ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት። ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ ፣ በደላንታ ፣ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ የምትገኝ በሩአ አንድ የሆነ ዙሪያዋን በገደል የተከበበች በመስቀል ቅርጽ የተፈጠረች ልዩ ቦታ ናት። የአለም መድኃኒትን ክርስቶስን አይሁዶች ከስቀሉት በኋላ መስቀሉ ታምራትን በማድረጉ የተበሳጩት አይሁዳዊያን መስቀሉ ከተቀበረበት ቦታ ላይ ቆሻሻ አባራ በመጣል ለ300 አመታት ያህልታላቅ ተራራ አድርገው ደበቁት። ንግስት እሌኒም በእግዚአብሔር ፈቃድ አስውጥታ ቤተመቅደስ አሰርታ አስቀምጣው ታላላቅ ታምራቶችን አደረገ። ከእስራኤላዊያንም እጅ የፋርስ ንጉስ ማርኮ በወሰደው ጊዜ እስራኤላዊያን የሮማን ንጉስ ሕርቅያልን እርዳታ በመጠየቅ አስመለሱት። ከዚህም በኋላ በኃያላን ነገስታት መካከል መስቀሉን እኔ እወስድ እኔ እወስድ ተጣሉ። የኃይማኖት መሪዎችም ተሰባስበው መስቀሉ በእጣ እንድክፋፈል አደረጉ። ቀኝ እጁ የተቸነከረበትና ያረፈበትም ግማድ መስቀል ለአፍሪቃ በደረሳት ጊዜ የግብጽ (የእስክንድርያ ፓትርያርክ) ተቀብሎ ግብጽ አስቀመጠው። በግብጽም ለብዙ ዘመናት ይህል ኖረ። በኢትዮጵያዊው አፄ ዳዊት ዘመነ መንግስት የግብጽ ክርስቲያኖች ከግብጻዊያን አህዛቦች ዘንድ ስቃይ ደረሰባቸው፤ ለኢትዮጵያዊው ንጉስ ዳዊትም ስቃዩን ያስታግስላቸው ዘንድ ተማፀኑት። ንጉሱም የክርስቶስ ልጆች መከራ ደረሰባቸው ብሎ 20,000 ሰራዊት አስከትሎ ወደ ግብጽ በታላቅ ቁጣ ገሰገሱ በዚህም ግዜ ግብጻዊያን አህዛቦች ፈሩ ተንቀጠቀጡ። ንጉሱም ፈጥነው እርቅ እንድያደርጉ ካልሆነ ግን ግብጻዊያንን በታላቅ ቁጣ እንደሚያጠፋቸው መልእክት ላከ። ግብጻውያንም ፈጥነው ታረቁ። በዚህም ጊዜ ግብጻዊያን ክርስቲያኖች በንጉሱ ዳዊትና በኢትዮጵያን ክርስቲያን ወገኖች ተደስተው ለንጉሱ 12,000 ወቄት ወርቅ ለንጉሱ የእጅ መንሻ ላኩላቸው ። ንጉሱ ግን ይህንን ስጦታ መልሰው በመላክ ግማደ መስቀሉን እንድሰጧቸው በትህትና አመለከቱ። በዚህም ጊዜ የእስክንድርያ(የግብጽ) ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ተወያይተው መስቀሉን ስናር(ሱዳን) ድረስ በክብር መስከረም 21 ቀን አቀበሏቸው። ንጉሱ አፄ ዳዊትም ተመልሰው ኢትዮጵያ ሳይደርሱ በክብር አረፉ። የእሳቸውም ልጅ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደነገሰ ወደ ስናር ሂዶ ግማደ መስቀሉን አምጥቶ በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን መቅደስ አሰርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ ሌሊት በራዕይ ” አንብር መስቀልየ በድበ መስቀል( መስቀሌን በመስቀልያ ቦታ አስቀምጥ) የሚል ትዕዛዝ ከጌታ ዘንድ መጣ። ይህንም ቦታ ለሟግኘት ብዙ አድባራትን ዞሩ አላገኙምም። ንጉሱ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እግዚእብሔርን ለመጠየቅ 7 ቀን ሱባኤ ያዙ ፤ በዚህም ግዜ አምደ ብርሃን እየመራ እንደሚወስዳቸው ተነገራቸው። አምደ ብርሃኑም አየመራ በመስቀልያ በተፈጠረች ልዩ ተራራ ግሸን አደረሳቸው መስከረም 21 ቀን ደረሱ። በዚያም ታላቅ ቤተ መቅደስ አሳንጸው መስከረም 21 ቀን በዓሉን አከበሩ። ንጉሱ አፄ ዘርአ ያዕቆብም በዚህ ቀን በጽሁፍ ለምዕመናን አቀረቡ ከዚህም ግዜ ጀምሮ መስከረም 21 ቀን ይከበራል በቦታውም ልዩ ልዩ ታምራቶች ይደረጋሉ። የተራራው አቀማመጥ ከፎቶው እንደምታዩት መስቀልኛ ነው። ከእመቤታችን ክብረ በዓል በረከት ያሳትፈን አሜን። ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!
መስቀል/ ደመራ
ሸንቁት አየለ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በደሙ ፈሳሽነት ስለከበረ ጌታ ካረገ ብሁዋላ ዕዉር በማብራት :  ድዉይ በመፈወስ ተአምራት እያደረገ ቢያስቸግራቸዉ አይሁድ ተመቅኝተዉ ጎለጎታ በተባለዉ ቦታ ቀበሩት::

ከቀበሩትም ብሁዋላ የከተማዉ ሰዉ ሁሉ የቤቱን እና የአካባቢዉን ጥራጊ /ጉድፍ/  እየወሰደ በዚያ ቦታ እንዲያፈስ አዘዉ ስለነበር ቦታዉ ተራራ አህሎ ሲኖር በ300 ዓም መጨረሻ ላይ በቁስጥንጥያ /በሮም/ ነግሳ የነበረችዉ ንግስት እሌኒ የመስቀሉ ፍቅር ስለነበራት ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ፍለጋ አደረገች: ከዘመኑ መርዘም የተነሳ ቦታዉን የሚነግራት ብታጣ ወደ እግዚአብሄር አልቅሳ ከጸለዬች ብሁዋላ እንጨት አሰብስባ በመስከረም 16 ቀን ደመራዉን በእሳት አቀጣጥላ ከፍሙ ላይ እጣን ብትጨምርበት ጢሱ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አመልክቱዋታል:: እሱዋም አስቆፍራ አዉጥታ ወደ እሮም ሀገርስዳዋለች::

በዚህን ጊዜም ብዙ ነገስታት በኢየሱስ ክርሰቶስ መስቀል የተደረገዉን ተአምራት አይተዉ ከመስቀሉ ከፍለሽ ስጭን አሉዋት:: እሱዋም ወደ እግዚአብሄር አመልክታ/ጸልያ  በእግዚአብሄር ፈቃድ መስቀሉን ከሁለት ሰንጥቃ ግማሹን 70 ነገስታት አካፈለቻቸዉ:: ልዑል እግዚአብሄርም  ግማሹ በሁዋላ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ስለሚሄድ አስቀምጭዉ ስላላት አስቀመጠችዉ::

እርሱዋ ካረፈች ብሁዋላ ልጁዋ ቆስጠንጢኖስ እንደነገስ ግማሹን መስቀል ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ ቤተክርስቲያን ሰርቶ አስቀምጦታል:: ይህን ግማሽ መስቀል የተልያዩ ነገስታት ለራሳቸዉ ማድረግ ስለፈለጉ  በተልያዬ ወቅት እየማረኩ ከኢየሩሳሌም ፋርስ: ከፋርስ ሮም: ከሮም እስክንድርያ : ከእስክንድርያ ኢየሩሳሌም ወስደዉታል;;

የእግዚአብሄር ፈቃድ ሲደርስ በ1400 ዓም በሀገራችን የነገሰዉ አጼ  ዳዊት በሀገሬ ረሀብ ሆኑዋል እና ከመስቀሉ ክፋይ ላኩልኝ ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም እና ግብጽ ላከ:: እነሱም ከዚያ በፊት ተንበላት እየተነሱ ሲያጠፉዋቸዉ አጼ ዳዊት ይረዳቸዉ ስለነበር ግማደ መስቀሉን ልከዉለታል::

ምንጭ- ድርሳነ መስቀል :-የኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርዮስ እንደጻፉት እና ሊቃዉንት ወደ ግዕዝ ብሎም ወደ አማርኛ እንደተረጎሙት

መስቀል በደማቅ ሁኔታ በለንደን (ካምደን) ተከብሮ ዋለ

 

መስቀል ደመራ

መስቀል ደመራ

 

 

 

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.