የኢትዮጵያ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ:- የማይታረቁት ሁለቱ ጽንፎች ላይ የቆመ ጭብጥ

የኢትዮጵያ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ:- የማይታረቁት ሁለቱ ጽንፎች ላይ የቆመ ጭብጥ
———————————————————————–

የኢትዮጵያን ህዝብ አጠቃላይ የፖለቲካ ጉዳይ አንስቶ ለመተንተንም ሆን ስለመደራጀት ለማዉራት የመጀመሪያዉ ስራ መሆን ያለበት የጠራ ታሪካዊ የፕለቲካ ትንታኔ ማድረግ ነዉ:: የፖለቲካ ርዕዮተ አለም መረጣ/ፈጠራ/ እንዲሁም የፖለቲካ ፕሮግራም ነደፋ የሚጀምረዉ ከታሪካዊ የፖለቲካ /political history/ትንታኔ ነዉ:: አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሰረታዊነት የሚለያዩት በታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔያቸዉ ነዉ:: ይሄ የታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔያቸዉ ነዉ ለሚከተሉት የፖለቲካ ርዕዮተ አለም እንዲሁም የፖለቲካ ፕሮግራም መነሻ የሚሆናቸዉ:: አንዳንድ ፖለቲከኞች ግን ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ሳያደርጉ ከእነሱ በተቃራኒ የቆሙ ሀይሎች ያደረጉት የፖለቲካ ትንታኔ ላይ ቆመዉ በፖለቲካ ርዕዮተ አለምና በፖለቲካ ፕሮግራሞች ላይ ሊደራደሩ ሲሞክሩ ይታያል:: ወይም ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ አቸዉ ከሚነግራን በተቃራኒ ሌላ ጭብጥ እያመጡ ያወናብዱናል:: የጠራም የታሪካዊ የፖለቲካ ሳይኖራቸዉ ስለመደራጀት ያወራሉ:: በመሰረቱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ በማይታረቁ ሁለት ጽንፎች ላይ የቆሙ ጭብጦች ስላሉት በኢትዮጵያ ምድር ፖለቲካ የሚያራምድ ሀይል ወደ አንዱ ጭብጥ ማጋደሉ የምርጫ ጉዳይ አይሆንም::

ስለዚህ ማንም የሀገሬ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባኛል የሚል ሀይል የመጀመሪያ ስራዉ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔዉ ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ ነዉ:: ከዚያም የፖለቲካ ርዕዮተ አለም እና የፖለቲካ ፕሮግራሞቹን በጠራና በነጠረ መልክ ማስቀመጥ ይቻላል:: አንዱ ጠርዝ ላይ የቆሙት አክራሪ የኢትዮጵያ ብሄረተኞች ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ የሚከተሉትን ጭብጦች አስረግጦ ያስቀምጣል:-

ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ያላት ሀገር ናት:: ይህ የመቶ አመት ታሪክ ሌላዉ ቀርቶ የአጼ ቴዎድሮስን እና የአጼ ዮሐንስን ሀገር አንድ የማድረግ ጥረት አያካትትም::በአጼ ምኒሊክ ዘመን ላይ የኢትዮጵያን ህልዉ ሃገር መሆን ሃ ብሎ ይጀምራል:: በዚህ በመቶ አመት ታሪክ ሂደት ዉስጥ ወራሪ ብሄረሰብ እና ተወራሪ ብሄረሰቦች አሉ:: ወራሪዉ ብሄረሰብ የተወራሪዎቹን ብሄረሰቦች ባህል : እምነት: ታሪክ: ቁዋንቁዋ: እምነት እና መሰረታዊ ማንነት ሁሉ በመደምሰስ የራሱን ማንነት ጭኖባቸዋል:: በወራሪዉ ብሄረሰብና በተወራሪዎች ብሄረሰቦች መሃከል መሰረታዊ የሚባል መስተጋርበር : አንድነት : የጋራ ማንነት ብሎም ዉህድ ህዝብነትን የሚያስረግጥ ነገር አልነበረም አሁንም የለም ::

በዚህም የተነሳ አክራሪ ብሄረተኞች የብሄር ፖለቲካ ብቸኛዉ የፖለቲካ አማራጭ እንደሆነ ያምናሉ : ይህንንም ያስተምራሉ:: ከዚሁ ጋር በማያያዝም ወራሪና ገዥ የነበረዉ ብሄረሰብ ( አንዳንዴ ለማምታታት ወራሪዉን ብሄረሰብ ሳይሆን ገዥዎቹን ነዉ ጠላት መደብ የምንላቸዉ የሚሉት ዘይቤ አላቸዉ) ጠላት መደብ መሆኑን አበክረዉ ያምናሉ:: በመሆኑም የፖለቲካ ርዕዮታቸዉም እንዲሁም የፖለቲካ ፕሮግራማቸዉ የተቀረጸዉ በዚሁ ህሳቤ ላይ ነዉ:: የፖለቲካ ርዕዮታቸዉ የሚነግረን አንድ እዉነት ቢኖር ጨቁዋኝ መደብ መደምሰስና አከርካሪዉ መሰበር አለበት በማለት ነዉ:: ጨቁዋኝ የሚሉት መደብ ላይ ሲደርሱ የሶሻሊስቶችን እና የአቢዮተኞችን የማይታረቅ የመደቦች ጠላትነት ህሳቤን በማንገብ ይሰራሉ:: በሶሻሊስ ህሳቤ የተቀመረዉ አቢዮት ሁል ጊዜ ወደፊት ይገሰግሳል :: በግስጋሴዉም ጨቁዋኝ : ወራሪ እና ጠላት ተብሎ የተፈረጀዉን ብሄር አከርካሪዉን እየሰበረ አንገቱን እያስደፋ ይቀጥላል:: ሁሉ የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚመነጩት ከዚህ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ነዉ:: የፖለቲካ ትንታኔዉ ወደ ፖለቲካ ርዕዮተ አለም ትንታኔ ያመራል ብሎም የፖለቲካ ርዕዮተ አለሙ ደግሞ ወደ ፖለቲካ ፕሮግራም ያመራል::

የፖለቲካ ፕሮግራሙ ደግሞ ምንም እንኩዋን ዲሞክራሲ የሚለዉ ቃል ሲነገር ቢደመጥም ወራሪ/ ጨቁዋኝ / በዝባዥ የሚባለዉ መደብ ላይ ሲደረስ ቀመሩ ይለወና አንድን ብሄር ከሃገሩ ማባረር: እምነቱን እንደ ጨቁዋኝ እምነት መፈረጅ: ሌሎች ህዝቦች ጋር ያለዉን መስተጋብርነትና ዉህድነት መካድ ይቀጥላል:: ሲሆን የምናዬዉም ይሄንኑ ነዉ:: ይሄ የታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ስልጣን የጨበጡትም በተቃዋሚነት የተሰለፉትም የአክራሪ ብሄረተኞች አቁዋም ነዉ::

የኢትዮጵያን  ሰዉ ግራ ሲያጋባ የሚታዬዉ በተቃዋሚነት የተሰለፈ ወገን ሁሉ የኢትዮጵያውን ህዝብ አጠቃላይ ችግር የሚፈታ ይመስለዋል:: ወይም ለኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ የሚታገል ይምስለዋል:: ግን እዉነታዉ እንደዚህ አይደለም:: በተቃዋሚነት ጉራም ተሰልፈዉ የታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ አቸዉ ለኢትዮጵያ ህመምን እንጅ ፍስሃን የማይወልድ ህሳብ ያረገዙ አሉ:: በተቃዋሚነት ተሰልፈዉ በገዥነት ቁብ ካሉት ጋር የታሪካዊ ፖለቲካ ትንታኔአቸዉን ያዋሃዱ አሉ::

ፖለቲካ ካወራን ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ላይ መስማማት ወይ መለያዬት አለብን:: በዚያ ሳንስማማ ስለዚህ ወይ ስለዚያ ህዝብ ያለቀሰ ከመሰለን ጋር ሁሉ ካለቀስን ፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳባችን ችግር አለበት ማለት ነዉ:: ስለመደራጀት ከማዉራታችን በፊት በታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ላይና በዚህ ጽንሰ ሀሳብ ላይ እርግጠኛ መሆን አለብን::

ዋናዉና መሰረታዊዉ ጥያቄ አንድ ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳይ ያገባኛል ለህዝቤም አማራጭ አለኝ ካለ መጀመሪያ ማድረግ ያለበትና መጠየቅ ያለብት የራሱን ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ማካሄድ ነዉ:: አክራሪ ብሄረተኞች ባከናወኑት ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ የሚስማማ ፖለቲከኛ/የፖለቲካ ፓርቲ መጀመሪያዉኑ አማራጭ የፖለቲካ ርዕዮተ አለም እና የፖለቲካ ፕሮግራም ይዞ ቢመጣም ትርፉ ድካም ነዉ:: አክራሪ ብሄረተኞች እንደሚያምኑትና እንደሚያስተምሩን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የተፈጠረችዉ በሚኒልክ ጊዜ ከሆነ : ሀገሪቱም የመቶ አመት ታሪክ ካላት : በአንዱ ኢትዮጵያዊ ብሄረሰብ ሌሎቹ ኢትዮጵያዉያን ብሄሮች ደግሞ ተወራሪ ከሆኑ የሚሰብኩትን የመደብ ጠላትነት መቀበል: ወራሪ የተባለዉና በጠላትነት የተፈረጀዉ ብሄርም ሲቀጠቀጥ መስማማት ብሎም ብቸኛዉ የሀገሪቱ የፖለቲካ አማራጭ የብሄር ፖለቲካ ነዉ ብሎ መቀበል ግድ ነዉ ባይባልም የተሻለዉ አማራጭ ነዉ:: ግፋ ሲልም በተግባር እንዳዬንዉ አገሪቱ መከፋፈል ያለባትና ምንም የጋራ ማንነት የሌላቸዉ ህዝቦች በግድ : በወረራ እስር ቤት የገቡባት ሀገር ናትና መበታተኑዋን መቀበል አለብን::

ስለሆነም የፖለቲካ አቁዋም የሚጀምረዉ ከታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ነዉና ዋናዉ ጥያቄዉ አንድ ሰዉ / አንድ ቡድን/ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ላደራጅ ብሎ ሲነሳ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔዉን ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ አለበት:: ከአክራሪ ብሄረተኞች የተለዬ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ አለን? ካለንስ ምንድን ነዉ? የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸዉ:: ከአክራሪ ብሄረተኞች በተለዬ መልኩ እዉነተኛ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ለማድረግ የሚከተሉትን ሁኔታዎች ታሳቢ አድርጎ መያዝ ይገባል:: አንድ ሰዉ/ወገን ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ በሚያከናዉንበት ጊዜ መጀመሪያዉ ታሳቢ አድርጎ መያዝ ያለበት የታሪካዊ የፖለቲካ ሳይንቲስቶቹ እነ ስቲፈን ሊ እንደሚያስተምሩት ለቀደመዉ ዘመን አመራር ፍትሃዊ ሆኖ መገኘት አለበት,(The political historian has the constant responsibility of doing justice to the leadership of the past)::

ይህም ማለት በጋርዮሽ ስርዓተ ማህበረሰብ ወይም በፊዉዳል ማህበረሰብ ዘመን የተከወን ክዋኔን በዘመን ዲሞክራሲ ዘመን ጎትተን በማምጣት :የዚያን ዘመን መሪዎችን ድርጊት : በዚያን ዘመን የነበሩ ተቁዋማትን እንዲሁም በዚያን ዘመን የነበሩ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ህሳቤዎችን በዘመነ ዲሞክራሲ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ንፅፅር በማድረግ ያኛዉን ዘመን በዚህኛዉ ዘመን መነጽር ለመቃኘት መንደርደር አግባብ አይደለም:: ብሎም ፍትሃዊም አይሆንም:: ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔዉ ሊከዉን የሚገባዉ በዚያኛዉ ዘመን ቁመትና ወርድ ልክ ነዉ:: ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ሊደረግ የሚገባዉ በዘመኑ በነበረዉ አጠቃላይ አለማቀፋዊ: አህጉራዊ: ሀገራዊ ብሎም አካባቢያዉ ተጨባጭ ሁኔታን ባገናዘበ መልክ ነዉ:: ስለዚያኛዉ ዘመን ታሪካዊ ትንታኔ ስናደርግ በዚያ ዘመን የነበረዉን ሁላቀፍ : የሁሉንም ማህበረሰብ ስነልቦናና ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና መሰረት አድርገን መሆን አለበት::

የዚያኛዉ ዘመን ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ከተደረገ ብሁዋላም ወደ ዚህኛዉ ዘመን መሳብና ለዚህኛዉ ዘመን ፖለቲካዊ ሂደት በግብአትነት ጥቅም ላይ ሊዉል የሚገባዉ አሁንም ለዚህኛዉ ማህበርሰብ ፍትህን ሰላምን እንዲሁም የጋራ ብልጽግናን በሚያጎናጽፍ መልክ እናም ለወደፊቱ ማህበረሰብ ደግሞ የአብሮነት ዉህደትን ሊያፋጥን በሚችል መልክ ሊሆን ይገባል:: በዚህ መርህ ላይ በመንተራስ እንዲሁም ትክክለኛዉን የኢትዮጵያዉያን የአባቶቻችንን ታሪክ ብሎም ተጨባጭ የሆነዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪካዊ ሰረ መሰረት ባላዛባ መልክ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ታሪካዊ ትንታኔ ማድረግ ተገቢ ነዉ:: ይህ ሁለተኛው ጠርዝ ላይ የቆመዉና ከቀደመዉ ታሪካዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በምንም መልኩ የማይጋባ ነዉ::

ለዚህ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ መንደርደሪያና መቆሚያ የሚሆኑ ዋና ዋና የሀሳብ ምሰሶዎችም የሚከተሉት ጭብጦች ናቸዉ:-

ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ አይደለም ያላት:: ኢትዮጵያ የብዙ ሽህ አመታት ታሪክ ያላት ሀገር ናት:: ይህም እዉነት በሀገሪቱ ታሪክ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ተመዝግቦ የሚገኘዉ በመላዉ የሰዉ ልጆች ታሪክ መጽሀፍት ዉስጥ ተካቶ ይገኛል:: እንዲያዉም በታላላቅነታቸዉ የሚታወቁት የሰዉን ልጅ አጣምረዉ የሚያስተሳስሩት መጽሃፍት ትርክታቸዉን የሚጀምሩት በታላላቅ አባቶቻችን አገር በኢትዮጵያ ነዉ:: መጽሀፍ ቅዱስ ገና ኦሪት ዘፍጥረት ትረካዉን የሚጀምረዉ የኢትዮጵያ መልከ አምድርን በመግልጽ ነዉ:: እንዲሁም እስልምና ገና በጅማሮዉ ወቅት ታሪኩን የሚጀምረዉ ታላቂቱዋን የአባቶቻችንን ሀገር ኢትዮጵያን በመጥቀስና ታሪካዊ ዉለታዋን በማዉሳት ጭምር ነዉ:: እነዚህ ሁለት ታላላቅ የአለም ህዝብ መጽሀፍት የታላላቅ አባቶቻችንን አገር ኢትዮጵያን ገና ከጥንተ ነገራቸዉ በዉበትና በክብር አስረግጠዉ ገልጸዉታል:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገር እንጅ የመቶ አመት ታሪክ ያላት ሀገር አይደለችም::

ኢትዮጵያዉያን አባቶቻችን የማንንም ሀገር ወረዉ አልያዙም:: ኢትዮጵያዉያንም በመሃከላቸዉ ወራሪና ተወራሪ ብሄር የላቸዉም:: ሁሉ ኢትዮጵያዉያን በተለያዬ ወቅት ለኢትዮጵያ አንድነት ያበረከቱት አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ድርጊት በጋራ ተደምሮ ተባዝቶና ተጠቃሎ ኢትዮጵያን አሁን ያላትን ይዘት ሰጥቶአታልና የታሪካዊ ፖለቲካ ትንታኔ ሂደቱ ጥበባዊ የሆነ የተሞክሮ አስተምህሮት ቀስሞ ሲመዝ ለዚህኛዉ ትዉልድ የሚበጀዉን ለመጭዉም ትዉልድ የበለጠ የሚጠቅመዉን ማሳለጫ ግባት ማምጣት አለበት::

ለምሳሌ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን እንኩዋን ብንመለከት ግራኝ አህመድ ከምስራቅ ኢትዮጵያ ተነስቶ መላ ሀገሪቱ ለመቆጣጠር ባደረገዉ ጥረት በክርስትና እና በእስልምና ሀይማኖት መሃከል ታላቅ ግጭት ቢፈጠርም በመጨረሻም ላይ በግጭቱ ምክናያት ሀገሪቱ ተዳክማ ማዕከላዊነት አጥታ ግዛቶቹዋ እስክ አስራ ስምንተኛዉ ክፍለ ዘመን ተከፋፍለዉ ቢቆዩም አጠቃላይ ሂደቱ ግን የሚተርክልን አንድ ነገር ብቻ ነዉ:: ይህም ግራኝ አህመድ የኢትዮጵያ አንዱ ታሪካዊ ፖለቲካዊ አካል መሆኑን ነዉ:: ግራኝ አህመድ ኢትዮጵያን መአስተዳደርና መምራት የፈለገዉ እስልምናን የተቀበለች ሀገር በማድረግ ከመሆኑ በቀር እንደሌሎቹ ኢትዮጵያዉያን ሀያላንና ጦረኛ አባቶች ግራኝ አህመድም ኢትዮጵያ ሀገሩ ስለሆነች የተዋሃደች ሀገርን ፈለገ እንጅ ኢትዮጵያን ላፍርሳት አላለም::

ሆኖም ኢትዮጵያን ለማስቀጠል እሱ የመረጠዉ ኢትዮጵያ እስልምና ብሄራዊ ሀይማኖት እንዲሆን በማድረግ ነበር እንጅ ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት የሚል አላማ አንግቦ አልተነሳም:: ስለሆነም ግራኝ አህመድ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ አንዱ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል:: በአንጻሩም ኢትዮጵያ ማዕከላዊነቱዋ ተዳክሞ ከቆዬች ብሁዋላ ከሰሜን ኢትዮጵያ የተነሱት አጼ ዮሐንስ ኢትዮጵያን ከግራኝ አህመድ በተቃራኒዉ ክርስትና የገነነባት አገር እንድትሆን አህመድ ግራኝ የወሰደዉ አይነት እርምጅ ለመዉሰድ ወስነዉ ነበር:: ግራኝ አህመድና አጼ ዮሐንስ የሚያስማማቸዉ ዋናዉ ነጥብ ኢትዮጵያ ሀገራቸዉ መሆኑዋን መቀበላቸዉና የሀገሪቱን ፖለቲካም እራሳቸዉ በሚያምኑበትና ዘመኑ በሚዋጀዉ ፍልስፍና መሰረት መከወናቸዉ ነዉ:: ሁለቱም መሪዎች በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ላይ የጋራ ግንዛቤ ነበራቸዉ:: እናም በተንኮል በአላዋቂነት እንዲሁም በስሜታዊነት የተወጠሩት ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ይሄን ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ስር ቆርጠዉ ጥለዉ አጼ ምኒልክ ጋ መጥተዉ ለምን ይንተፋፈፋሉ? ብለን ስንጠቅይ ከታሪካዊ ፖለቲካዊ ትንታኔአቸዉ ሊወልዱት ያሰቡት የፖልቲካ ስላለ ነዉ::

አንድ የዚህ ዘመን የታሪካዊ ፖለቲካ ተንታኝ ተነስቶ የአጼ ዮሐንስን የፖለቲካ እርምጃ ከግራኝ አህመድ እርምጃ በመነጠል አጼ ዮሐንስን ብቻ ለመኮነን እስልምና ላይ በደል አደረሱ ለማለት ቢነሳ ፍትሃዊ ትንታኔ አይደለም:: በተመሳሳይም አንድ ሌላ ተንታኝ ግራኝ አህመድ እስልምናን የኢትዮጵያዉያን እምነት ለማድረግ ምን እንዳነሳሳዉ ጉዳዩን ኢትዮጵያ ላይ ብቻ በመወሰን ካቆመዉና በዘመኑ የነበረዉን በኦቶማን ቱርክ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ይደረግ የነበረዉን ፖለቲካዊ መስፋፋት ከዚህም ጋር ተያይዞ የእስልምና መስፋፋት አብሮ አካቶ ለመዳሰስ ካልሞከረ አሁንም የግራኝ አህመድን ታሪካዊ ፖለቲካ በፍትሃዊነት እየተነተን አይደለም::

ከግራኝ አህመድና ከአጼ ዮሐንስ ታሪክ በታሪካዊ ፖለቲካ ትንታኔ ተጭምቆ የሚወጣዉና ለዚህ ዘመን የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ምርጫ ግብ አትነት ተፈልፍሎ የሚወጣዉ አንድ ጥበባዊ የተሞክሮ ትምህርት አንድ ነገር ብቻ ነዉ:: ያም በአሁኑ ዘመን ያሉ ኢትዮጵያዉያን ብሎም የመጭዉ ዘመን ኢትዮጵያዉያን ዜጎች የሀይማኖት እኩልነት የሰፈነበት እና በመቻቻል መሰረት ላይ የሚቆም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የግድ ያስፈልጋቸዋል:: ከዚህ ዉጭ በሆነ መልኩ ግን የግራኝ አህመድን ድርጊት በማንሳት ክርስቲያኖችን ሆድ ለማስባሻ : የአጼ ዮሐንስን ድርጊት በማንሳት ሙስሊሞቹን ሆድ ለማስባሻ የሚደረግ የታሪካዊ ፖለቲካ ትንታኔ ኢ ፍትሃዊ ከመሆኑም በላይ ህዝብን ለማጫረስ የሚተለም ትልም ከመሆን አይለይም:: እንዲሁም በዚህ ዘመን አለም የደረሰበትን ጽንሰ ሀሳብ ወደ አጼ ዮሐንስ እና ወድ ግራኝ አህመድ ዘመን ጎትቶ በመዉሰድ ዲሞክራሲያዉ የሀይማኖት መቻቻል ሁለቱ ኢትዮጵያዉያን መሪዎች ባለማድረጋቸዉ ለመክሰስና ለመዉቀስ መንተፋተፍ አሁንም ኢፍትሃዊ ትንታኔ ነዉ::

በተመሳሳይም የዮዲት ጉዲት የአይሁድን እምነት በምታስፋፋበት ጊዜ እና ከክርስትና እምነት ጋር ከፍተኛ ትግል በምታደርግበት ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካን እሱዋ በገባት እሴት ለመዘወርና እሱዋ በምታምንበት እምነት ለመቅረጽ ከመጣሩዋ በቀር ዮዲት ጉዲት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ፖለቲካ አካል እንዳልሆነች አድርገን እንድንቆትራት አያደርገንም:: ዮዲት ጉዲት ኢትዮጵያ እንደሀገር የመቀጠሉዋ ጉዳይ ሳይሆን እንዲለወጥ የፈለገችዉ የሀገሪቱ ብሄራዊ እሴት አይሁድነት እንዲሆን ነዉ የጣረችዉ::

እንዲሁም የኦሮሞ ባላባቶች : የትግራይ ባላባቶች : የአማራ ባላባቶች የጎንደር ቤተመንግስትን በ16ኛዉ ክፍለዘምን ለመቆጣጠር ያደረጉት የፖለቲካ ትግል የጋራ የዚህች ሀገርና የህዝቡዋ ታሪክ መሆኑ ህልዉናዋም በዚህ ሁሉ ሂደትና ዉጣዉረድ ዉስጥ መምጣቱ እየታወቀ አንድ የፖለቲካ ተንታኝና ቀማሪ ዛሬ ላይ አንዱን ህዝብ ወራሪ ሌሎችን ተወራሪ በማድረግ የኢትዮጵያን ታሪክ በመቶ አመት በመሸበብ እስክስታ የሚመታዉ ከዚህም እስክስታ መዞ የሚያወጣዉ ኢፍትሃዊ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም እማን ላይ ለመጫን ማንንስ ለማስቀጥቀጥ ነዉ የሚለዉ መመለስ አለበት::

እንዲሁም በጥንት ዘመን ኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ሰራዊት አዝምታ እስራኤልን መውረሯን እና ኢትዮጵያ ታላቁዋ ሀገር ተብላ የተጠራች የመጀመርያዋ ሀገር ኢትዮጵያ እንደነበረች የተለያዩ ጸሃፍት እነደሚከተለዉ መረጃ እየጠቀሱ ያስረዱናል:: ቀደምት እስራኤላውያን ዓለም ከተፈጠረ ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ያለውን የራሳቸውንና የዓለምን ታሪክ ጽፈውልን አልፈዋል:: ስለ ጥንታዊት ሀገራችን ኢትዮጵያም ብዙ ጽፈዋል:: የሚገርመው እስራኤላውያን በዚያን ዘመን ይፈሯት የነበረው ኢትዮጵያን መሆኑን ፣ በራሳቸው የታሪክ መጻህፍት መጻፋቸው ነው:: የነሱ ነገስታትና የታሪክ ጸሀፊዎችም ስለ እትዮጵያ ሲጽፉ ፤ “ታላቂቷ ኢትዮጵያ ወይም ታላቅ ሀገር” እያሉ ነበር የሚጽፉላት:: በእስራኤላዊው ንጉስ ዝሪ ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያውያን ሁኔታ በሚገርም መልኩ የእስራኤል ታሪክ ጸሃፊዎች እንዲህ ጽፈውታል:: በተለይ ማኬል ያሽር የተባለው ጸሀፊ:: የማኬል ያሽር መጽሀፍ ውድና የማይገኝ ቢሆንም በሱው ዘመን የነበረው የዜና መዋእል ታሪክ ጸሀፊ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ሲል በመጠኑ ገልጾታል:: 2 መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 14:9 ጉዳዩን እንዲህ ያብራራዋል::
8 ለአሳም ( የእስራኤል ንጉሥ) አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ጋሻም የሚሸከሙ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ።
9 ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው ወደ መሪሳም መጣ።
10 አሳም ሊጋጠመው ወጣ፥ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ።
11 አሳም። አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ ሰውም አያሸንፍህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያ በጥንት ዘመን የነበረች አገር ብቻ ሳትሆን ያኔ ኢትዮጵያ ገናና ሀገርም እንደነበረች ነዉ:: በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ እስራኤልን ለመያዝ አንድ ሚሊዮን ሰራዊትና ሶስት መቶ ሰረገሎች አዝምታ ነበረ:: ተወራሪው የእስራኤል ንጉስ ደግሞ የነበረው የመክላከያ ሀይል 580 ሺህ በመሆኑ ክፉኛ ፈርቷል:: እናም የኢትዮጵያን ሀይል ፈርቶ ወደ ፈጣሪው ጸሎት አደረገ:: ጸሎቱም እንዲህ የሚል ነበረ :: 2መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 14:11
11. አሳም። አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ሕዝብ ላይ መጥተናልና እርዳን አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ ሰውም
አያሸንፍህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

እንዲሁም አጼ ቴዎድሮስም በመሳፍንት ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያ አንድ ለማድረግ በሚቃትቱበት ዘመን እንኩዋን የሀገሬ የኢትዮጵያ አንድነት ድንበር መቆሚያዉ ለዉ የሚያምኑት አስከ እየሩሳሌም እንደነበረ ታሪካቸዉ ይናገራል:: ለዚህ ነው በግዜው የነበረ ባልቅኔ እንዲህ ሲል የተቀኘው
”ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም
አርብ አርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም”
ይህም አላማቸው ይሳካ ዘንድ የሚደግፉ ደጋፊዎቻቸው እንዲህ ሲሉ ተቀኝተውላቸዋል
አንተም ጌታ አይደለህ እኔም ያንተ ሎሌ
የየሩሳሌም ሰው ካልጫነ በርሙሌ”

ሌላዉ ታላቅ የኢትዮጵያ ንጉስ የሆነዉ ላሊበላም ኢትዮጵያዉያን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ በመንገድ ላይ ቢገደሉበት “ኢየሩሳሌምን ለመሳለም የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ወግኖቼ በአህዛብ ሲና በረሀ ላይ እየተገደሉብኝ ነውና” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸሎት እንዳደረገና በርካታ ሰራዊት እያዘጋጀ እንደነበረ የሱ ገድል ይነግረናል::

ይህ ሁሉ የታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔና ዋና ዋና የታሪካዊ ጭብጥ የሚነግረን አንድ ነገር ብቻ ነዉ:: ኢትዮጵያ የተፈጠረችዉ ከመቶ አመት በፊት ነዉ:: ፈጣሪዎቹዋም አገዎች :  አማሮች  አይሁዶች ቤጃዎች  ክርስቲያኖች : ኦሮሞዎች: ትግሬዎች  እና ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ናቸዉ:: እነዚህ ማህበረሰቦች አብረዉ ሲኖሩ አብረዉ በጋራ ቃትተዋል: መስተጋብር ፈጥረዉ ዉህድ ህዝብ ፈጥረዋል ደግሞም ለስልጣን የበላይነት ተጋለዋል:: እናም በዚህ ሁሉ ሂደት ዉስጥ ሁሉም ኢትዮጵያን ህልዉ ለማድረግ እኩል በመሳተፍ የዛሬዋን ኢትዮጵያን ፈጥረዋል::

አሁን ከዚህ ከሁለተኛው ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ ተመዞ የሚወጣው ምን አይነት የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ነዉ? ትናንት ዘመኑ በፈቅድላቸዉ መሰረት በጋራ አብረዉ በመቃተት የኖሩ ህዝቦች ሀገር ኢትዮጵያ ዛሬ ድግሞ ይህኛዉ ትዉልድ ዘመኑ የሚፈቅድለትን ፍጹም ዲሞክራሲ በመከተል አብሮ የሚበለጽግበትን ቀመር ቢያንሰላስል እንጂ ያ ብሄር ወራሪ ይሄኛዉ ተወራሪ በማለት ያ ይቅርታ ይበለኝ ይሄኛዉም ይቅርታ ይባልልኝ እያለ ታች ላይ ቢባል በሂደቱ ማንም አትራፊ ማንም ተሸናፊና አሸናፊ እንደማይኖር እሙን ነዉ የሚል ታሳቢን አስከትሎ የመጣል:: ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ እንደሚያሳዬዉ ሁሉም ኢትዮጵያዉያን ወገኖች ሀገር በመፍጠር ሂደቱ ወስጥ ዘመኑ እንደ ፈቀደላቸዉ ተሳትፈዋልና ወራሪና ተወራሪ የለም::

በጥቅሉ ግን አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማንኛዉም አይነት የፖለቲካ ድምዳሜ : የፖለቲካ ዕዮተ አለም : የፖለቲካ ፕሮግራም ተመዞ የሚወጣዉ ከታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል:: የኢትዮጵያም ታሪካዊ የፖለቲካ ትንታኔ በሁለት ጠርዝ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን አብሮ መገንዘቡ ማንም ሰዉ ለሚወስደዉ የፖለቲካ አቁዋም ማጣቀሻ ወሳኝ ግብአት ብቻ ሳይሆን መቆሚያም ተደርጎ እየቀረበ መሆኑን ማዉሳቱ መልካም ነዉ::

እርግጥ ነዉ ሶስተኛ እና እነዚህን ሁለት ጠርዝ ላይ የቆሙ የፖለቲካ ታሪካዊ ትንታኔዎች ወደጎን በማድረግ ለዚህ ትዉልድና ለመጭዉ ትዉልድ ይበጃል የሚባለዉን የፖለቲካ አማራጭ ማስላቱ ይሻላል የሚል አካሄድ የሚያራምድ ወገን ሊኖር እንደሚችል ታሳቢዉን አለመዝጋቱ ጥሩ ነዉ:: አሁን ባለዉ ሁኔታና አክራሪ ብሄረተኞች የመጀመሪያዉን የታሪካዊ ፖለቲካዊ ትንታኔ አጥብቀዉ በሚያስተጋቡበት ሁኔታ ግን ሶስተኛዉ አማራጭ የጠበበ እድል ያለዉ ይመስላል::

ይሄንን አማራጭ አሁን ባለዉ ሁኔታ ተስፋዉን የሚያቀጭጩት በርካታ ምክንያቶችም አሉ:: አንድም አክራሪ ብሄረተኞች ዋናዉን ስልጣን ብቻ ሳይሆን የተቆጣጠሩት በተቃዋሚነትም ከፍተኛዉን የፖለቲካ መድረክ ተቆጣጥረዉታል:: አክራሪ ብሄረተኞች ዋና መለያቸዉ ደግሞ ሁል አቀፍ አካታችና አቻቻይ ነገር አምርረዉ መጥላታቸዉ ነዉ:: አንድም በኢትዮጵያ ታሪካዊ አገርነት እናምናለን ብለዉ ወደ ፖለቲካው የገቡት ሀይሎች የሚፈልጉዋትን ኢትዮጵያ ተጠይቃዊ በሆነ መልክ ቁልጭ አድርገዉ አስቀምጠዉ ወደ አንድ ማዕከል በመሰባሰብ ሳይንሳዊ ፖለቲካ ከመከወን ይልቅ በስሜት ብቻ ለአክራሪ ብሄረተኞች መልስ የሚመስል ነገር በመምወርወር ላይ መጠመዳቸዉ:: አንድም አሁን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በስፋት የተቆጣጠሩት በግራም በቀኝም ያሉ ሀይሎች በአንድ ወቅት በደመኝነት የተነካኩ መሆናቸዉና አሁንም የሶሻሊዝምን “ሁለት ተቃራኒ መደቦች ተቻችለዉ አይሄዱም : ስለሆነም ወይ እነሱ ይጠፋሉ ወይ እኛ እንጠፋለን” የሚል ነቀርሳ የሆነን አመለካከት የታጠቁ በመሆናቸዉ ነገሩን ይበልጥ ዉስብስብ ያደርገዋል::

ይህ ብቻ ሳይሆን ለስልጣን ለጥቅምና ለዝና ሲማልሉም ሲማልዱም የሚኖሩ ፖለቲከኞች አንድም ከድህነት ለማምለጥ አንድም ኢትዮጵያ ባህላዊ እሴት ዉስጥ ተሰንቅሮ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ሰብዕና አልፋታም ያለዉንና የተዛባዉን የስልጣን ትርጉዋሜአቸዉን ለማሙዋላት ሲወራጩ መገኘታቸዉ የዚህን የሶስተኛዉን አማራጭ እንዲቀጭጭ የሚያደርገዉ ጉዳይ ነዉ:: ከሁሉም በላይ አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ፖለቲካዊ መነጽር ሲቃኝ ፖለቲካዉን ባለ ዐዕምሮ የሆኑት ታላላቅ የሀገሪቱ ዜጎች : እንዲሁም የተሻለ የመማር እድል ያጋጠማቸዉ ዜጎች ብሎም የተሻለ ኑሮ እየመሩ ያሉ ዜጎች ሊደፍሩት ስላልፈለጉ ፖለቲካዉ ብዙም በእዕዉቀት ላልጎለመሱ ወይም የተዛባ ስነባህሪ ላላቸዉ ሰዎች በሩ በስፋት ወለል ብሎ ስለተከፈተ ያለመርህ ፖለቲካ እንሰራለን የሚሉ ፍትህን ሳይሆን ግፍን ለመዝራት የተዘጋጁ ፖለቲከኞች በፖለቲካዉ ውሱጥ በቀኝም በግራም መነንሰራፋታቸዉ ለዚሁ ለሶስተኛዉ አማራጭ የቀጠነ አማራጭነት አስተዋጽኦ ያደርጋል::

የሀገሪቱ ፖለቲከኞችም የመሰባሰቢያ ምክንያታቸዉ ወንዝ: ዘር: ብሄር: ጽዋ: ዘመነ መሳፍንታዊ ቀመር ላይ በመቆም ማን ማንን መራ የሚል ህሳቤ ጭምር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚመጣዉ ዉስብስብ ጉዳይ ፖለቲካዉን ለመደገፍ ዘጭ እንተፍ የሚሉ ወገኖች ምንም ይሁን ምን የአካባቢያቸዉን ወፍ መሰል ፖለቲከኛ በፖለቲካዉ መሰላል ላይ የተወጣጣ ሲመስላቸዉ ሲደግፉት የነበረዉን ሀሳብ እርግፍ አድርገዉ ጥለዉ ወደ ወንዛቸዉ ሰዉ: ወድ ብሄራቸዉ ፖለቲከኛ ፊታቸዉን ማዞራቸዉ አብሮ የሚወሳ ነዉ:: ይህም ማለት አኝከህ አኝከህ ወደ ዘመድህ ዋጥ የሚለዉ ፖለቲካዊ ብሂል እንዲጠናከር አብሮ ማሳለጫዊ ሆኑዋል:: ይህ እዉነት እንዲገንም 30 ሚሊዮን ህዝብ ያለዉ ብሄርና 30 ሽህ ህዝብ ያለዉ ብሄር እኩል እኩል ክልል ተብለዉ እኩል ድምጽ እንኩዋን ሳይሆን የ30 ሽሕ ሕዝብ ተወካዉ የበለጠ በሚኖረዉ የጠነከረ ጎሳዊ ትሥር ጉልበቱ ሲጎለብት ያስተዋሉ ሁሉ የእኛስ ብሄር ለምን ሲሉ መዋተታቸው ያለ እዉነት ነዉ:: 

እነዚህና እና ሌሎችም ቅንጭብጫቢ እሴቶች የሀሳብ ፖለቲካ በሀገሪቱ ላይ ስር እንዳይሰድ የፖለቲከኞቹን አነስተኛ ቀመር ቀስፎ ከመያዙም በተጨማሪ የደጋፊዎቹን ቀልብ ከፋፋይ መንደርደሪያ ጫካ ናቸዉ:: ይሄዉ ጉዳይ ታዲያ በወፍ በረር እንኩዋን ውይይት ሳይደረግበት በደፈናዉ በዝምበል ዝምበይ እንዲቀጥልም መደረጉ የዚህ ትዉልድ የሶስተኛዉን አማራጭ ጉዳና አቀጫጭ ግብአት ሆኖ ተዘግቦአል::

ይህ ሶሥተኛ አማራጭ ከፍተኛ የሆነ የሀሳብ ፍጭት ተደርጎበት የሚወጣዉን የፖለቲካ ጭብጥ ለማራመድ ታላቅ ዐእምሮ እንዲሁም በመርህ ላይ የቆመ ታማኝ ስነባህሪ ያስፈልገዋል:: እንድ አጃቢነትም የአመራር ስነባህሪ ቀረጻ አንሰላሳሊ እና ምሁር የሆነዉ ፕሮፌሰር ኮቮይ እንደሚተነትነው አሁን በመላዉ አለም የተንሰራፋዉ ፖለቲካ ያለ ር ዕዮተዓለም ሀይማኖት ያለ ሀይማኖታዊ መስዋ ዕትነት በአፍ ብቻ በመላዉ አለም የሚነበነብ አዎንታዊ ስነ ልቦና መርበቡና መላዉ አለም አጨናባሪ በሆነዉ የለበጣ አዎንታዊ ህሳቤ መነባንብ መዋጡ እንዳለ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ስነልቦናዊ ይዘት ስንዘምት ግን የፕሮፌሰር ኮቬይ ምልከታ በሰፋ ሁኔታ የሀገሪቱን ወገኖች በቁጥጥር ስር ማዋሉ ሌላዉ ተያያዥ ጣጣ ነዉ:: የሆነ ሆኖ ለዚህ የሶስተኛ አማራጭ እድል መጥበብ በምክንያትነት የተጠቀሱት አሰናካይ ምክንያቶች በአንደኛዉና በሁለተኛዉ የታሪካዊ ፖለቲካ ጠርዝ ላይ ተንጠልጥለዉ ፖለቲካዉን እንከዉናለን ለሚሉት የሀገሪቱ ፖለቲከኞች አደናቃፊ ምክናያቶች አይደሉ ማለት ግን አይደሉም:: ሆኖም እንደ ሶስተኛዉ አማራጭ ፈታኝ የሆነ ችግር ሆነዉ አይመዘዙባቸዉም ለማለት እንጅ::

በአጠቃላይ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ሶስተኛዉ አማራጭ አሁን ባለዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ የቀጨጨ ዕድል ያለዉ መስሎ ይታያል:: ሆኖም ወደፊት በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ዉስጥ ለም መሬት አያገኝም ማለት ግን አይደለም:: ያኔ ምናልባትም ሰፊ የሆነ አማራጭ ሆኖ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የሚንሰላሰለዉ ይሄዉ አማራጭ ይመስለኛል:: ለምሆኑ ይህ አማራጭ ምን ሁኔታ ሲሙዋላ ነዉ የኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ አማራጭ ሆኖ የሚወጣዉ የሚለዉን ጭብጥ “የኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ አማራጭ: መቼና እንዴት” በሚለዉ ጽህይፌ ዉስጥ ለመዳሰስ ሞክሬ አለሁ:: ይህን ጽሁፍ ለማንበብ ቀጥሎ ያለዉን ሊንክ መጫን ነዉ::

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.