ተስፋዬ ገብረአብ እየደገፋችሁ ለሚመስላችሁ ኢትዮጵያዉያን
ጠላትህን እንዴት ታጠቃዋለህ ቢሉህ – ብልህ ከሆንህ ፈላስፋ እንደሚነግርህ “ጠላት አፈራለታለሁ” ብለህ ትመልሳለህ:: ወዳጅህንስ እንዴት ትጠቅመዋለሁ ቢሉህም ” ወዳጅ አፈራለታለሁ” ብለህ ትመልሳለህ:: ይህ እንግዲህ ጠቢብ ከሆንህ ብቻ የሚገባህ ነገር ነዉ:: መቼም ጥበብ የራቀዉ ሰዉ እንዲህ ያለ ጥበባዊ አስተሳሰብ አይገባዉም:: እናም እንዲህ አይነት ረቂቅ ሀሳብ ማስተዋል ለተነጠቀ ሰዉ መጻፍ ራሱ ሞኝነት ነዉ:: መጽሀፍ እንዳለ” ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት” ተብሎአልና ይህን ጽሁፍ የምጽፈዉ ለጠቢባን ኢትዮጵያዉያን ብቻ መሆኑን ከወዲሁ መግለጽ እፈልጋለሁ::
እናም ወደ መልዕክቴ እገባለሁ:: ተስፋዬ ገብረአብ አንዱን ወገን የደገፈ መስሎ ሌላዉን ወገን ጠላት በማድረግ ደገፍኩት ለሚለዉ ወገን ጠላት እያፈራለት ነዉ:: ጠቢባን እንደሚመክሩን ግን አንድ ሰዉ ወዳጅህ ከሆነ ሊያፈራልህ የሚገባዉ ወዳጅ ነዉ እንጅ ጠላት አይደለም:::
ይህ ማለት በቀላል ተጠይቅ እንዲህ ማለት ነዉ:- ጥላቻ ጥላቻን ይወልዳል:: ፍቅር ፍቅርን ይወልዳል:: እናንተ ዉስጥ እሱ ጥላቻን ሲዘራባችሁ እናንተ ለምትወልዱት ጥላቻ አቻ የሚሆን ምላሽ በጠላችሁት ወገን ዉስጥም ተረግዞ ይወለዳል:: ሁለት ወገኖች ሲጠላሉ ምን ይፈጠራል? ማንኛዉም ወገን አያሸንፍም:: ቢያሸንፍም እኩል ከተጠፋፉ ብሁዋላ ብቻ ነዉ::
አስቂኙ ነገር ታዲያ ከብዙ ጥፋት ብሁዋላ አሸናፊ የሚሆነዉ ወገን አለመታወቁ ነዉ:: መሸናነፍ በራሱ ማቆሚያ የለዉም:: ልክ ህጻናት ትንቅ ሲገጥሙ ወይም ረስለሮች/ነጻ ትግል ታጋዮች/ ሲታገሉ አንዴ አንዱ ሲጥል ሌላ ጊዜ ሌላዉ ጉልበቱን አጠራቅሞ ሲገለብጥ ማለቂያ ወደሌለዉ የእርስ በእርስ ትግል ዉስጥ መግባት እንደማለት ሊወሰድ ይቻላል:: በጥላቻ ሁለቱም ወገን ይዝላላ:: ሁለቱም ወገን ይደክማል:: መጨረሻም ማንም ወገን ሳያሸንፍ በያለበት ተዳክሞ ይዘረራል:: እንግዲህ በዚህ ሂደት ዉስጥ አጥፊ መሳሪያዎችና አጥፊ ሀሳቦች ተካተዉበትና ከምድረ ገጽ ለመጠፋፋት የሚደረገዉን ሂደት አክላችሁ አስቡት::
ጥላቻ የመጨረሻ ፍሬዉ መጠፋፋት ነዉ:: አሁን ይህ ጥልቅ አባባል ለሞኞች እንደማይገባቸዉ እሙን ነዉ:: ሞኞች የሚገባቸዉ የጥፋቱ ቀን መጥቶ እየጠፉ ባለበት ሰዓት ብቻ ነዉ:: አንድም መጥፋታቸዉ እንኩዋን አይገባቸዉም:: ፈጽመዉ እየጠፉ ባለበት ሰአት ቢያዉቁትም አላወቁትምና:: አሳዛኙ ነገር ታዲያ ሰነፎች በስንፍናቸዉ ትዉልዳቸዉ እንኩዋን እንደሚጠፋ ለማወቅ የሚያስችል አስተዉሎት የጎደላቸዉ ናቸዉና ጠላት በእነሱ ዉስጥ የሚዘራዉን ጥላቻ ተሸክመዉ መልሰዉም እየዘሩት ለዘለአለም ይኖራሉ:::
ስለዚህ ጠቢባን የሆናችሁ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ወደ አስተዉሎታችሁ ማዕከላዊ ጭብጥ ልታዉሉት የሚገባዉ እዉነት አንድ ነገር አለ:: ማንም ወገን እናንተን ወደ ጥላቻ የሚገፋችሁ ከሆነ የደገፋችሁ ቢመስልም ጠላታችሁ ነዉ እንጅ ወዳጃችሁ አይደለም:: የዚህ ዘመን የማህበረሰብ ግንኙነት አንዱ በአንዱ በጋራ ተሳልጦና ተዋህዶ ወደ ጋራ ብልጽግና መራመድ ቁልፍ መርሁ ነዉ:: አለሙ ተለዉጡዋል:: እጅግም ተሳስሮአል:: እጅግም ይፈላላጋል:: እያንዳንዱ የአለም ህዝብ ሌላዉን የአለም ህዝብ ይፈልገዋል:: የበለጠም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላዉን ኢትዮጵያዊ አጥብቆ ይፈልገዋል:: በዚህ የመፈላላገ ሂደት ዉስጥ ፍቅር: እዉቀትና እዉነት መርህ ሊሆኑ ይገባል:: እነዚህ ሶስት ነገሮች ሲጣመሩና የትንታኔ መሳሪያዎቻችን ሲሆኑ ዲኦንሄራዊ ዲሞክራሲ ይባላል::
ማህበረሰብ አስገራሚ ድንቅ ሀሳቦችን እያመነጨ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ወይም የተበላሸ ነገር ሲገጥም የሚታረመዉ በፍቅር : በእዉቀትና በእዉነት ብቻ መሆን አለበት:: ፍቅር ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ የእኔ አካል ነዉ ብሎ ማሰብ ነዉ:: እዉቀት ማለት አሁን አለም የደረሰባቸዉን የስነመንግስት: የሰበአዊ መብት እንዲሁም የማህበረሰባዊ ሁል አቀፍ ብልጽግና በመንተራስ የራስን ብሎም የመላዉ ወገንንም መብትና ህልዉና ለማረጋገጥ እራስን ስለወገን መስዋዕት አድርጎ ማቅረብ ማለት ነዉ:: እዉነት ማለት ደግሞ ፍቅራችንም ሆነ የእውቀት ትንታኔዎቻችን ለዛሬና ለመጻኢዉ ትዉልድ ቀጣይ ህላዌ እዉነተኛ መሰረት የጨበጡ እንዲሆኑ ማድረግ ነዉ:: ይህን በፍቅር በእዉቀትና በእዉነት የታሸ ሂደት ማለትም ዲኦንሄራዊ ዲሞክራሲ የወደፊቱ የትንታኔ ማሳሪያችን ሊሆን ይገባል:: ስለ ዲኦንሄራዊ ዲሞክራሲ በቅርቡ የማካፍላችሁ ሰፋ ያለ መጻጽፍ ይኖረኛል:: ይህም የዛሬዉ ጽሁፍም ከዲኦንሄራዊ ዲሞክራሲ ህሳቤ የተቀነጨበ ቅምሻ መሆኑን አንርሳ::
የዛሬዉን መልዕክቴን ለማጠቃለል ግን ጠቢባን ለወዳጅህ ወዳጅ አፍራለት እንደሚሉት ማንም እንደተስፋዬ አይነት ደበኛና መሰሪ ተነስቶ የሚያጣላ ነገር ቢያዉጅላችሁና አንዱ ወገን ጠላት እንደሆነ ቢሰብክላችሁ “እረፍ በመርህ ጥለንሃል” ማለት መቻል አለባችሁ:: ተከትላችሁት የጥላቻዉ መርዝን በልባችሁና በአዕምሮአችሁ ከከተታችሁ ግን እራሳችሁን ብሎም ትዉልዳችሁን እያጠፋችሁ መሆኑን አትርሱት:: ግልጽ ነዉ ሰነፍና ማስተዋልን የተነጠቀ ሰዉ ግን በዚህ አባባል እንደሚስቅ እሙን ነዉ:: ሰነፍ ነዉና:: እንዲህ አይነቱን ሰዉ ከስንፍናዉ ጋር ተዉት::
እንድገመዉ :- ጠላትህን እንዴት ታጠቃዋለህ ቢሉህ ብልህ ከሆንህ ፈላስፋ እንደሚነግርህ “ጠላት አፈራለታለሁ” ብለህ ትመልሳለህ:: ወዳጅህንስ እንዴት ትጠቅመዋለሁ ቢሉህም ” ወዳጅ አፈራለታለሁ” ብለህ ትመልሳለህ:: ይህ እንግዲህ ጠቢብ ከሆንህ ብቻ የሚገባህ ነገር ነዉ::
ሸንቁጥ አየለ (shenkutayele@yahoo.com)
Leave a Reply
You must be logged in to post a comment.