ስለ ታቦት የሚነሱ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው

ጥያቄ፡- በዘዳ 31፣18፣32፣15፣134፣1-5፡፡2ኛዜና 5፣10 ያሉትን ጥቅሶች በመጥቀስ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሁለት ጽላቶችን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እነዚህን እልፍ አእላፋት ጽላቶች ከየት አመጣቻቸው? አራብታችሁ ቅረጹ የሚል አለ ወይ?

መልስ፡- በዘዳ 32፥19፡፡ ስንመለከት እግዚአብሔር ራሱ አዘጋጅቶ ለሙሴ የሰጠውን ሁለቱን ጽላቶች እሥራኤል ጣዖት ሲያመልኩ ስላገኛቸው ሙሴ ተበሳጭቶ ሰብሯቸዋል፡፡ነገር ግን ቸርነቱ ለዘለዓለም የሆነ እግዚአብሔር አምላክ ለሙሴ የመጀመሪያዎቹን አስመስሎ እንዲሰራ ነገረው፤ ሙሴም አስመስሎ ሠራ፡፡ ዘዳ 34፥1-5 መሥራት ብቻ ሳይሆን ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃላትም በጽላቶቹ ላይ እንዲጽፍ ሙሉ ሥልጣን ከእግዚአብሔር ተሰጠው፡፡ ሙሴም ተፈቅዶለታልና አሥሩን ቃላት በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፡፡ ዘዳ 34፥27-28 ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጽላትንም ሆነ ታቦትን እያስመሰሉ ለመሥራት ሙሉ ሥልጣንን አግኝተናል፡፡ ይህን በተመለከተ አንዳንድ አባቶች እንዲህ ይላሉ፤

‹‹አዳም እንኳን በደለ አዳም ባይበድል ኖሮ አምላክ ሰው ሆኖ በቀራንዮ ስለእኛ የመሰቀሉን፤ ስለኛ የመሞቱን የፍቅር ምስጢር አናውቀውም ነበር፡፡››

እስራኤልም በጥጃ ምስል ጣኦት አምልከው እንኳን በደሉ እሥራኤል ባይበድሉ ሙሴ በእግዚአብሔር የተዘጋጁት ሁለቱ ጽላቶች’ የሰው ልጅም እግዚአብሔር የሠራቸውን የፊተኞቹን አስመስሎ ለመሥራት ስልጣን ባልኖረውም ቢሠራም ለምን ሠራህ ለሚለው መረጃ ባላቀረበም ነበር›› ይላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ጽላትን አስመስለን፤ አባዝተን፤ አራብተን ለመሥራት መሠረታችን ሥልጣኑ ለኛ ለልጆቹ የተላለፈልን ከአባታችን ከሙሴ ነው፡፡››

ሙሴ የተሰበሩትን አስመስለህ ሁለት ጽላቶች ቅረጽ ከሚል በቀር ጽላቶችን አብዝታችሁ፤ አራብታችሁ ተጠቀሙ የሚል ቀጥተኛ ቃል አምጡ ለሚለው ግን ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የጽላትም ሆነ የቤተ መቅደስ ሥርዐት፤ የመስዋዕቱ የዕጣኑ አገልግሎት፤ በኢየሩሳሌም ብቻ ስለነበረና፤ የሌላውም አገር ሕዝብ የሚከተለው የጣዖትን ሥርዓት እንጂ የሙሴን ሥርዐት ባለመሆኑ ጽላቱ ተባዝቶ ተራብቶ ለሌላው አገር ሕዝብ አልተሰጠም፡፡ እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ውጭ አልፈቀደም የተቀደሰውን ጣዖታውያኑ አሕዛብ ያረክሱታልና ስለዚህ ስግደቱም የቤተመቅደስ ሥርዐቱም በኢየሩሰሳሌም ብቻ ነበር። /ዮሐ 4፥18-24/

በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ አሕዝቦችም ሠሎሞን ያሠራው ታላቁ ቤተ መቅደስና ሁለቱ ጽላቶች አንሰውናል፤ በርቀት የምንገኝ እኛ የመንገድ ድካም በዝቶብናልና፡፡ ስለዚህ በያለንበት ቤተ መቅደስ ሠርተን ጽላቱን አክብረን መገልገል እንፈልጋለንና ይፈቀድልን ብለው ሙሴም ከሁለቱ ጽላቶች በቀር ሌላ አልተፈቀደም ብሎ መልስ የሰጠበት ቦታ የለም፡፡

ያም ሆነ ይህ በሐዲስ ኪዳንም በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በአብ፤ በወልድ፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀው ፤ሁለተኛ የድኅነት ልደት ተወልደው የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣን ሰጣቸው። ለክርስቲያኖችም ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ እንደሚበዙና በአዲስ ኪዳን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ንጹሕ የሆነውን ቁርባን ከኢየሩሳሌም ውጭ በየቦታው ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡

1. ‹‹ ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ይከበራልና፤ በየስፍራው ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፤ ንጹሕንም ቁርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር›› ሚል 1፥11፡፡
2. ‹‹ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎ የለምን? እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ አስተማራቸው›› ማር11፥17፤ ኢሳ 56 ፥ 7፤ ኤር 7፥11 ፡፡

ይህ ትንቢት በቀጥታ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሆኑ ግልጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስም ሆነ የዕጣን፤ የቁርባን አገልግሎት እንኳን ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ላሉ አሕዛብ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በቀር ለእስራኤል ጎረቤት አገሮች እንኳ አልተፈቀደምና፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ንጹሕ ዕጣን ያለው በማቴ 2፥11፡፡ ወንጌል እንደተናገረው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰብአ ሰገል በቤተልሔም ዋሻ ለክርስቶስ ካቀረቡት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ያለን ክርስቲያኖች በክርስቶስ ስም ለክርስቶስ የምናቀርበው ቅዱስ ዕጣን ነው፡፡

ንጹሕ ቁርባን የሚለውንም በማቴ 26፥26፤ ጌታ ኅብስቱን አንሥቶ ነገ የሚቆረሰው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ወይኑንም አንሥቶ ነገ ስለብዙዎች ሀጢአት የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው ብሎ ለሐዋርያት የሰጣቸው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡ ንጹሕ የተባለው እርሱ በባሕርዩ ንጹሕ ሆኖ የእኛን የኃጢአት እድፍ ስለሚያነጻ ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን በኢየሩሳሌም ብቻ መሆን የሚገባቸው ቤተ መቅደሱ፤ ዕጣኑ፣ ቁርባኑ፣ በክርስቶስ ደም በአዲስ ሕይወት፣ በአዲስ ተፈጥሮ፤ በአዲስ ሥርዓት፣ ክርስቲያኖች ለሆንን ለዓለም ሕዝቦች በየሥፍራው (በያለንበት) እንድንጠቀምባቸው ከተፈቀዱልን በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ሁለቱ ጽላቶች ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ተባዝተው በዓለም ያለን ክርስቲያኖች በያለንበት በየቤተ መቅደሳችን ለሥጋውና ለደሙ የክብር ዙፋንነት ብንገለገልባቸውና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ብናከብርባቸው ምን የሚጎዳ ነገር ተገኘ? የሚያስደነግጠውስ ምኑ ነው? ስህተቱስ የቱ ላይ ነው?

እንዲሁም ዐሠርቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸው ሁለቱ ጽላቶች መባዛት መራባት የለባቸውም ከተባለ በጽላቶቹ ላይ የተጻፉት ዐሠርቱ ትእዛዛት መባዛት የለባቸውም፡፡ ከኢየሩሳሌምም መውጣት የለባቸውም ማለት አይደለም? ትእዛዛቱም ተከለከሉ ማለት ነውና፡፡

በጽላቶች ላይ የተጻፉት ትእዛዛት በእግዚአብሔር ፈቃድ በፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ በሚገኙ ክርስቲያኖች እጅ ገብተዋል፡፡ ይህም ያስደስታል እንጂ አያሳዝንም፡፡ ይህ ከሆነ ለሥጋውና ለደሙ (ለክርስቶስ) ክብር ሲባል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ጽላቶች ምን በደል አስከተሉ፥ እግዚአብሔር ለቀደሙ አባቶቻችን በታቦቱ አድሮ የሠራላቸውን ድንቅ ሥራ እያስታወስን እግዚአብሔርን ከማመስገን ውጭ ደግሞም ጌታ ስለ ጸሎት ሲያስተምረን ‹‹አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ውስጥ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን›› በሉ ብሏል፡፡ በዚህ መሠረት በዮሐንስ ራዕይ 11፥19 ላይ ታቦቱን በሰማይ አሳይቶናል፡፡ ስለዚህ የሙሴ የቃል ኪዳኑ ታቦት በሰማይ እንዲገኝ፤ በሰማይ እንዲሆን፤ በሰማይ እንዲታይ ፈቃዱ ከሆነ፤ በምድርም እንዲሆን ፈቃድህ ይሁን ብለን ብንጠቀምበት ስህተቱ ምን ይሆን?

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.