በሁለት ህትመት በርካታ ፍረጃዎችን ያስተናገደችዉ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ

እነዚህ የተለያዩ አመለካከቶችና አስተያዬቶች አንዳንዶቹ በፌስ ቡክ በቀጥታ የተሰጡ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ቀለም ቀንድ ላይ ለምንጽፍ ሰዎች በኢሜይል : በስልክ : በፌስቡክ መልዕክት እንዲሁም በአካል የተሰጡ ናቸዉ:: ሁሉም ፍረጃዎች : አመለካከቶች እና አስተያዬቶች የሆነ የሚያዝናና እንዲሁም የሚያስተምር ነገር ስለማያጡ በአንድ ሰብስቤ ላቀርብላችሁ አሰብኩ:: ሰዉ ወደ መድረክ ከወጣ የመጀመሪያ ስራዉ መሆን ያለበት ለመተቸት አንዳንዴም ለመወደስ መዘጋጀት ነዉ:: ወዳሴዉም ሆነ ትችቱ አንገዳግዶ እንዳይጥል ታዲያ ቅድመ የስነልቦና ዝግጅት ማድረጉ መልካም ነዉ:: አለዚያ በጥቂቱ እብጥ ደግሞም በጥቂቱ ሙሽሽ ማለት ስለሚከተል ማለት ነዉ:: እናም ከእብጠትም ሆነ ከሙሸት በራቀ መልክ የሚከተሉትን ፍረጃዎች : አመለካከቶች እና አስተያየቶች እያነበባችሁ እንድትዝናኑ ብሎም እንድትማሩ አቅርቤላችኋለሁ:: ወዲያዉም ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ምን ያህል ዉስብስብ መሆኗን ግንዛበቤትወስዳላችሁ ብዬ አስባለሁ::

ስለሆነም የቀለም ቀንድ ላይ የሚጽፉም ሆነ ሌሎች ጋዜጦች ላይ የሚሳተፉ ያገራችን ጋዜጠኞች ወይም ሀሳባቸዉን የሚያካፍሉ ግለሰቦች ብሎም ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሆነ ነገር ሊማሩበት ይችሉ ይሆናል የሚል ግንዛቤን ስለያዝኩ በቀለም ቀንድ ጋዜጣ ላይ የተሰጡ ልዩ ልዩ ፍረጃዎችን አመለካከቶችን እና አስተያዬቶችን እንደሚከተለዉ ላቀርባቸዉ ወደድሁ:: በእያይንዳንዱ አስተያዬትም ስር የእኔን የግል መልስ አብሬ አቅርቤዋለሁ:: ይህ የኔ የግል መልስ ነዉ:: አስተያዬትና አመለካከቶች በሚመጡልኝ ጊዜ የሰጠኋቸዉ መልሶች ናቸዉ::

1. የመጀመሪያዉ አስተያዬት እንዲህ ይላል:- ይህ ጋዜጣ አክራሪ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምዱ ሰዎች መሳሪያ ሊያደርጉት የተቋቋመ ነዉ ይባላል:: እዉነት ነዉ? እንደሚታወቀዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት የሚባል የጋራ ማንነት ሳይኖረዉ አንዳንድ ትምክህተኞችና ነፍጠኞች የሚያቀነቅኑትን ኢትዮጵያዊነት ለማቀንቀን መነሳት አይበጅምና ተመከሩ::ትምክህተኞች ዛሬም አከርካሪያቸዉ አልተሰበረም እንዴ?

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ይህ ጋዜጣ ከላይ የተባለዉ አላማ ካለዉ ጥሩ ነዉ:: ምናለባት አንድ አክራሪ ኢትዮጵያዊነት አራማጅ ጋዜጣ ቢኖረን ይበረታታል:: አክራሪ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ጽንሰ ሀሳብ ካለ ይሄን ሀሳብ አጥብቆ የሚያራምድ አንድ ጋዜጣ ብቅ ማለቱ መልካም ሳይሆን አይቀርም:: እና ፍረጃዉ አያስከፋም:: በኢትዮጵያዊነት የሚመካና ኢትዮጵያዊ ትምክህቱ የሆነ ቡድን ባሁን ዘመን ማግኘት ከቻልን መልካም ነዉ:: ለማንኛዉም በሂደት ጋዜጣዉን መገምገሙ መልካም ነዉ::

2. ሁለተኛዉ አመለካከት ደግሞ እንዲህ ይቀጥላል:- ይሄ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ እንደሚባለዉ የቀለም ሳይሆን የአማራ ዘዉጌነትን ለማራመድ እና የአማሮች ድምጽ ለመሆን ነዉ የተቋቋመዉ:: እናም ይሄን ጋዜጣ ታዩታላችሁ:: ኢትዮጵያዉያንን እሚወክል ሳይሆን የአማራ ዘዉጌነትን የሚያቀነቅን ጠባብ ጋዜጣ ነዉ:: አማሮች ተፈናቀሉ ምናም ከማለት የዘለለ ነገር የላቸዉም:: ለዚህ ጋዜጣ ከአማራ መፈናቀል የበለጠ ቁምነገር የለዉም:: እዉቋቸዉ አማራ ናቸዉ:: የአማራ ስብስብ ናቸዉ::አግልሏቸዉ:: አማራ በዚህ ዘመን የተጠላ ወገን እንደሆነ ሁሉ እነዚህንም ጥሏቸዉ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ይህ ጋዜጣ ከላይ እንደተባለዉ የአማራ ዘዉጌነተን ለማቀንቀን ተቋቁሞ ከሆነም አያስከፋም:: ስለ አማራ ማህበረሰብ መገፋትና መፈናቀል ተቆርቁረዉ ሊሰሩ የሚነሱ ወገኖች ካሉ ሰበአዊም ህጋዊም መብታቸዉ እስከሆነ ድረስ የሚያስከፋ ነገር የለም:: አገሩ እራሱ የሚተዳደረዉ በብሄር ፖለቲካ ጽንሰ ሀሳብ እስከሆነ ድረስ አማሮች በጋዜጣም ሆነ በፓርቲ ደረጃ በአንድነት ቢሰባሰቡና የብሄራቸዉን መብትና ጥቅም ቢያስጠብቁ የሚያስከፋ ነገር የለም:: የሚከፋም ካለ ምንም ማድረግ አይቻልም:: እናም የቀለም ቀንድ የአማሮች ጋዜጣ ነዉ የሚለዉ ፍረጃ አያስከፋም:: ለማንኛዉም በሂደት ጋዜጣዉን መገምገሙ መልካም ነዉ::

3.ይህ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ መኢአድን (የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን) ወደ ነበረበት ለመመለስ ብሎም የተበታተኑትን የመኢአድ ቡድኖች ለማቀራረብ የተቋቋመ ነዉ:: ከዚህ የዘለለ ግብ የለዉም:: መኢአድ የሚባለዉ ድርጅት ደግሞ አክትሞለታል:: መኢአድ ሞቷአል:: የሞተ ነገር ለመቀስቀስ የሚሰራ ጋዜጣን እንዳታነቡ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ይህ ጋዜጣ ከላይ የተባለዉ አላማ ካለዉ ጥሩ ነዉ:: ሊበረታታም ይገባዋል:: እንደሚታወቀዉ መኢአድ ከ 1.2 ሚሊዮን አባላትን በላይ አፍርቶ መላዉ ኢትዮጵያን በዲሞክራሲ ጥማት ያናወጠዉን የ1997 ዓም ምርጫ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን የመራ ፓርቲ ነዉ:: እናም መኢአድን ወደነበረበት ለለመመለስና የመኢአድ ሰዎችን ለማቀራረብ ተቋቁሞም ከሆነ የሚበረታታ ሀሳብ ነዉ:: እና ፍረጃዉ አያስከፋም:: ለማንኛዉም በሂደት ጋዜጣዉን መገምገሙ መልካም ነዉ::

4. ይህ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ አክራሪ የሆነዉ የመኢአድ ክንፍ ማለትም እነ ማሙሸት አማረ የሚመሩትን መኢአድን ማዕከል አድርጎ የተቋቋመ ነዉ:: እነ ማሙሸት አማረ ደግሞ የሰሜን ሸዋ ጎጠኞችና ጸረ ዲሞክራሲ ናቸዉ:: እናም ይሄን ጋዜጣ ጋዜጣ አትበሉት:: ወንዘኛ ጋዜጣ ነዉ:: ዘረኛ ጋዜጣ ነዉ:: የሰሜን ሸዋ ስብስብ ነዉ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ይህ ጋዜጣ ከላይ እንደተባለዉ እነ ማሙሸት አማረን ማዕከል አድርጎም ከተቋቋመ አበረታች ነዉ:: ማሙሸት አማረ ከ 12 አመት በላይ በበርካታ እስር ቤቶች ገና በወጣት እድሜዉ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የማቀቀ ጀግና ነዉ:: ገና ቁንጢጥ መጣ ብሎም የሚሸሽ ሰዉ አይደለም:: አመትና ሁለት አመት ታሰርሁ ብሎም ትግል ካሁን ብኋላ እርሜ የሚል ግለሰብ አይደለም:: የ1997 ዓም ህዝብ ያስደመመ ምርጫ የመራዉ የእነ ማሙሸት አማረ የማይናወጥ የማደራጀት ስራ ነዉ:: ብልጦች ለዚህና ለዚህ መሰል ሰዎች እዉቅና ቢሰጡም ባይሰጡም እዉነቱ ይሄዉ ነዉ:: ደግሞም አንዳንድ ብልጦች በአፋቸዉ ዲሞክራትና ታጋይ ነን እያሉ እንደሚከረባበቱት ብሎም ታዋቂነትን ለማግኘት እንደሚባትቱት ታጋዮች ለእዉቅና የሚሮጥ አይደለም:: ማሙሸት እዉነትን እዉነት ሀሰትንም ሀሰት ብሎ የሚናገር ሰዉ ነዉ:: በዚህም እዉነተኛ ባህሪዉ በጣም የተጠቃ ሰዉ ነዉ:: ሆኖም ይሄም ፍረጃ አያስከፋም:: የሰሜን ሸዋ ስብስብ የሚለዉም አባባል አያስከፋም:: ሰሜን ሸዋን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ለማስወጣትና ለማጥፋት በርካታ ቢሊዮን ዶላርም ቢመደብም እዉን አለሆነም:: ስለተሞከረ እንዲሁም አሁንም ስለቀጠለ ዉጤቱ የዜሮ ድምር ሆኖ ቀጥሏል:: እንደተባለዉም የተባለዉ አላማ ያለዉ ጋዜጣ ከሆነም ጥሩ ነዉ:: እናም ፍረጃዉ አያስከፋም:: ሰሜን ሸዋን ጭራቅም ሰይጣንም ወይም መልአክም አድርጎ የመፈረጅ መብት ለዬትኛዉም ወገን ክፍት ነዉ:: የፈለገዉ የፈለገዉን አመለካከት መከተል መብት ነዉና ይሄ ፍረጃም አስከፊ አይደለም:: ለማንኛዉም በሂደት ጋዜጣዉን መገምገሙ መልካም ነዉ::

5. ይህ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ የጎጃምና የጎንደር ወንዘኞች ተሰብስበዉ ያቋቋሙት ነዉ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- የጎጃም እና የጎንደር ልጆች እንደተባለዉም ይሄን ጋዜጣ ሰብሰብ ብለዉ ካቋቋሙት ጀግነዋል ማለት ነዉ:: ሊበረታቱም ይገባቸዋል:: እንኩዋን ጎጃምና ጎንደርን ከሚያህል ሰፊ አካባቢ የተሰባሰቡ ሰዎች ከአንድ አራት ኪሎ የሚሰባሰቡ ልጆች ሰብሰብ ብለዉ ጋዜጣ ቢያቋቁሙና የሚያምኑበትን ለህዝብ ቢያካፍሉ ሊበረታታ ይገባዋል:: ዋናዉ ሀሳብ ለህዝብ መቅረቡ ነዉ:: ህዝብ ደግሞ የወንዘኞች ሀሳብን ወይ ይጥለዋል ወይም ይወደዋል:: ጎጃሞችና ጎንደሮች እባካችሁ ሰብሰብ እያላችሁ ጋዜጣ አቋቁሙ:: ዋናዉ ልዩ ልዩ ሀሳብ የሚንሸራሸርበት ሚዲያ መፈጠሩ ነዉ:: እናም ፍረጃዉ አያስከፋም:: ለማንኛዉም በሂደት ጋዜጣዉን መገምገሙ መልካም ነዉ::

6. ይህ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ወያኔ/ ኢህአዴግ የምትደጉመዉ ጋዜጣ ነዉ:: አምታችና አሰመሳይ ጋዜጣ ነዉ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ይሄም ፍረጃ አያስከፋም:: ወያኔ/ኢህአዴግ ካሏት በርካታ ሚዲያዎች በተጨማሪ አንድ አዲስ ጋዜጣ ቢኖራትስ ምናለበት:: እንደተባለዉም ወያኔ/ኢህአዴግ ካላት ተዝቆ የማያልቅ ብር ዉስጥ ጥቂት ዛቅ አድርጋ ይሄን ጋዜጣ ብታቋቁመዉ ምን አለበት? ይሄ 16 ገጽ ያለዉ ጋዜጣ 56 ገጽ ያለዉን አዲስ ዘመንን አጋዥ እንዲሆን እና አንዳንድ በአዲስ ዘመን አልሸጥ ያሉ አስተሳሰቦችን ለመሸጥ ያግዝ ይሆናል:: እናም ይሄም ፍረጃ አያስከፋም:: ሀገሩ በሙሉ በወያኔ/ኢህአዴግ መዳፍ ስር ባለበት ዘመን ደርሶ አንድ ጋዜጣ በወያኔ/ኢህአዴግ ድጎማ ተቋቋመ ብሎ ማዘን አይገባም:: እናም ፍረጃዉ አያስከፋም:: ለማንኛዉም በሂደት ጋዜጣዉን መገምገሙ መልካም ነዉ::

7. ይህ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብን የግንዛቤ ማዕከል በማድረግ የተቋቋመ ነዉ:: ስለሆነም ሁሉንም አስተያዬቶች በነጻነት የሚያንሸራሽር ነዉ:: ለዚህ ማሳያዉም ባለፈዉ ሳምንት እንዲሁም በዚህ ሳምንት በሀሳብ የተለያዩ ቡድኖችን በማቅረብና አፋጣጭ ጥያቄዎችን በማንሳት እያከራከረ የሀሳብ ልዩነቶችን ማሳዬቱ ነዉ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- አዎን ጋዜጣዉም በፊት ለፊቱ ላይ በገሃድ የሚያዉጀዉ እንዲህ ብሎ ነዉ:: በእዉቀት : በእዉነት: በእምነት እናም በፍቅር ለህዝባችን ሁል አቀፍ ግንዛቤ ከፍታ ሳናሰልስ እንሰራለን:: እናም ስለቀለም ቀንድ እንደዚህ ያለ ግንዛቤን የያዙ ወገኖች ፊት ለፊት የተጻፈዉን ስላነበቡ ሊመሰገኑ ባይገባቸዉም ግንዛቤያቸዉ ከፍታ ላይ የደረሰ በመሆኑ ግን ሊደነቁ ይገባል:: እናም የጋዜታዉን አላማ አግኝታችሁታል ብራቮ ቢንጎ ቢባሉ መልካም ሳይሆን አይቀርም::

8. ስምንተኛዉ አመለካከት ደግሞ:- ይህ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ለምን እንደተቋቋመ እናቃለን::በቂ መረጃ አለን:: ዋናዉ ጋዜጣዉ የተቋቋመዉ የቀለም አቢዮትን በኢትዮጵያ ለማምጣት ነዉ:: ይህ ነገር ፈጽሞ የሚሳካላችሁ አይደለም:: አርፋችሁ ተቀመጡ:: ስሙን እራሱን የቀለም ቀንድ ያላችሁት የቀለም አቢዮት ለማምጣት ግብ ስላላችሁ ነዉ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ይህ ጋዜጣ ይሄን የተባለዉን የቀለም አቢዮት ግብ አድርጎ ተቋቁሞ ከሆነ የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል እንዳይሆን ስልጣነ መንበሩን የጨበጠዉ ሀይል ቢጠነቀቅ ጥሩ ነዉ:: አቢዮት በጋዜጣ ይመራል የሚል ታሳቢ የያዘ ወገን ካለም ቀላል አቋራጭ ነዉና የሚደነቅ ስልት ነዉ:: ወይም ስለ አቢዮት መሰረታዊ ባህሪ ያልተረዱ ሰዎች ጋዜጣ አቋቁመዉ አቢዮትን ስትፈነዳ ለመመልከት አልጋቸዉ ላይ ተጋድመዉ ከናፈቋት ወይም የአቢዮት ካባ ሊደርቡ ከፈለጉ ሞኝ አለዚያም ብልህ ናቸዉና የሚፈጥሩትን አቢዮት ከመጠበቅ ዉጭ አማራጭ የለም::የሆነ ሆኖ ይሄም ፍረጃ ቢሆን የጀግና ካባ ስለሚያለብስ መጥፎ አይደለም:: እናም ፍረጃዉ አያስከፋም:: ለማንኛዉም በሂደት ጋዜጣዉን መገምገሙ መልካም ነዉ::

9. በዚህ ጋዜጣ ላይ የሚሰጠዉ አስተያዬት ጊዜዉን የጠበቀ አይደለም:: ጊዜ ተሰጥቷቸዉ የሚሰሩት ስራ ሊመዘን ይገባል እንጂ እንዲህ በፍጥነት በልዩ ልዩ አሉታዊ ታሳቢ ልናሸማቅቃቸዉ አይገባም::ገና በመጀመሪያ እትም ጀምሮ አሁን ደግሞ በሁለተኛዉ እትም ምን አይነት ጥላቻ ቢኖር ነዉ ይሄ ሁሉ ፍረጃና ማዋከብ? ይሄ አግባብ አይደለም::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ይሄንኑ አስመልክቶ አንድ ወዳጃችን ሽንጡን ገትሮ እንዴት እንደተከራከረልን ከሚከተለዉ ሊንክ ላይ ተመልከቱልን:: https://www.facebook.com/photo.php?fbid=503627179769227&set=a.115015965297019.17980.100003658484610&type=

1&comment_id=503857679746177&offset=0&total_comments=25&ref=notif&notif

_t=photo_comment_tagged :: ይሄ ወዳጃችን ወሰንሰገድ ይባላል:: ጊዜ ይሰጣቸዉ እንጂ የሚለዉ አቋሙ ያስመሰግነዋል:: በርካታ አስተያዬት ሰጭዎችም ሀሳቡን የተጋሩት ይመስላሉ:: ቢያንስ እኔ በግሌ አመስግኘዋለሁ:: ገና በአንድ እና ሁለት እትም ይሄ ሁሉ ዉርጅብኝ ምንድን ነዉ ሲል ይሞግታል:: የቀለም ቀንድን በዘዉጌነት: በቀሽምነት: በወንዘኝት ፈራጅ ወገኖችን (አንዱን ወንድማችንን ማለቴ ነዉ) እረ እባካችሁ እያለ ይሞግታ:: እኔም የወሰንን ጽሁፍ ካነብብሁ ብኋላ ይህች የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ምን ታምር ይዛ ቢሆን ነዉ ይሄን ያህል የተለያዩ ፍረጃ እና አመለካከቶችን ለማስተናገድ የበቃችዉ ስል ጥያቄ ጭሮብኛል:: ቢሆንም የወሰን ነጥብ በዉስጤ ምቾት ሰጥቶኛል:: በሁለት እትም ብቻ ብዙ ለመፈረጅ መብቃቷም ወይ ጉድ ሳያስብል አይቀርም::

10. አያያዙ ያስታዉቃል:: በቅርቡ ከገበያ ዉጭ የሚወጣ ጋዜጣ ነዉ:: አይዘልቅም::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- ታዲያ ይሄ ምን ይደንቃል:: ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያላት ልዩ ልዩ ሀሳቦችን ለማስተናገድ አቅም መፍጠር እስካልቻለች ድረስ ይሄ እየጀመሩ በመሃል ማቋረጥ ይቀጥላል:: ግለሰቦች የቻሉትን ይሞክሩና ያልቻሉትን ለሀገርና ለህዝብ አስረክበዉ ይተዉታል:: ዋናዉ መሞከር ነዉ:: ትልቁ ጥፋት ያለመሞከር ነዉ:: ስንት ተወንጫፊ ሰይፍ ባለበት ሀገር ስንት ነበልባል የሆኑ ጋዜጦች ተዘግተዋል:: ገናም ይዘጋሉ:: እና ይሄም አባባል የሚያስከፋ ፍረጃ አይደለም::

11. አይዟችሁ ሁሉንም ፍረጃዎች : ችግሮችና አሉታዊ አስተያዬቶች ተቋቁማችሁ የህዝባችን ድምጽ ሆናችሁ እንደምትቀጥሉ አንጠራጠርም:: በሚያስፈልገዉ ሁሉ ከጎናችሁ ነዉ::

የኔ መልሰ ደግሞ እንዲህ የሚል ነዉ:- አይዞን ! ዱለኞች በዱላቸዉ ካላስቆሙን የሀሳብ ፍጭት እንኳን አያስቆመንም:: መፈረጅም ጥሩ ነዉ:: በነገር ሸንቆጥ የሚያደርግ ወዳጅ መኖሩም መልካም ነዉ:: የሚታነጽ ከሁሉም ነገሮች እየተማረ ይታነጻል:: ሁሉንም አስተያዬቶች በጸጋ እንቀበላቸዋለን:: የትኛዉንም ፍረጃ እንቀበላለን:: ደግሞ ለመፈረጅ ማን ይፈራል? እንኳን መፈረጅ ጀግኖቹ ስንት መከራ ገጥመዉ ያልፉ የለም:: ይህችማ ኬክ መብላት ናት:: እኛ በልባችን ህዝብ ያለን ወገኖች ነን:: ህዝብ ያለን የምትለዋን በደንብ አስምሩልኝ እማ:: እናም እንላለን :- በእዉቀት : በእዉነት: በእምነት እናም በፍቅር ለህዝባችን ሁል አቀፍ የግንዛቤ ከፍታ ሳናሰልስ እንሰራለን:: ደግሜ አንድ ማስታወሻ ልባችሁ ዉስጥ ልከተብ እማ :- እኛ በልባችን ህዝብ ያለን ወገኖች ነን:: ህዝብ ያለን የምትለዋን ደግማችሁ በደንብ አስምሩልኝ እማ:: በዚህች ነጥብ ዙሪያ ጊዜዉ ሲደርስ ሰፊ ገለጻ እንደማደርግላችሁ ቃል እገባለሁ:: ጊዜዉ ሳይደርስ ግን አይደለም:

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.