ገብሩ አስራት የሸፋፈናቸዉ ሐቆች
በሙሉቀን ተስፋዉ
በ2007 ዓ.ም. ከታተሙ በሀገር ውስጥ በጣም ከተነበቡት መጽሃፍት መካከል የቀድሞው የህወሓት ታጋይ ገብሩ አስራት ‹‹ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ›› አንዱ ነዉ፡፡ መጽሀፉን ብዙ ሰዎች አንብበዉ እጅግ ‹ያለ ምንም አድልኦ› ሙያዊ በሆነ መልኩ እንደተጻፈ ገልጸው ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ እንዲያነቡት የሚጋብዙ በርካቶች ናቸዉ፡፡ እኔም በእነዚህ ሰዎች ተጋብዤ 417 ገጽ ያለውን ጥራዝ አነበብኩት፡፡ ነገር ግን ብዙ የሚጎረብጡኝ ሀቆች በተፈለገዉ (በሆነዉ) መልኩ ሊገለጹ ሲገባቸዉ እጅግ ስልታዊ በሆነ መልኩ ተደፋፍነዉ ታልፈዉ በማገኘቴ ዝም ለማለት አልቻልኩም፡፡ በመጽሀፉ ላይ ያለኝን ሙሉ እይታ እንደሚከተለዉ ለማንጸባረቅ ፈለግኩ፡፡
የገብሩ አስራትን መጽሀፍ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነበበ ሰዉ የሚያውቀው ሀቅ ቢሆንም ሀገሪቱ የህወሓት ብቻ መሆኗን የበለጠ ያረጋግጣል፡፡ እንዲያው የኤርትራን ወረራ እንኳ ብንመለከት የህወሓት ፖሊት ቢሮ ምክክር ‹‹ትግራይ የምትባል ሀገር›› እንጅ ኢትዮጵያ የተወረረች አላስመሰለዉም ነበር፡፡ እርግጥ በህወሓት ፖለቲካ ሀቁ እንዲያ ነዉ፡፡ የቀሪዎቹን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ‹ውስብስ ፖለቲካ በቀላሉ የማይገባቹው› መሆናቸዉን ገብሩ አስራት አስረድቶናል (ገጽ 240)፡፡
ገብሩ አስራትን ጥርሱን ነቅሎ ካሳደገዉ ህወሓት ያጣላዉ ከትግራይ (ከኢትዮጵያ?) ለኤርትራ የተሰጠው መሬትና መለስ በኤርትራ ላይ ያለው አቋም ነዉ፡፡ ከዚያ ውጭ ከዚህ ግባ የሚባል አንድም ልዩነት የለዉም፡፡ በመጽሃፉ የተለያዩ ገጾች አልፎ አልፎ ‹‹በእርግጥ አሁን ላይ ሆኘ ሳስበዉ ትክክል አልነበርንም›› ቢልም ቅሉ ከላይ ከገልጽኩት ኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ውጭ አጥብቆ ያወገዘው አንድም ነገር አላገኘሁም፡፡
ገብሩ በመጀመሪያው ምዕራፍ የኢትዮጵያንና የአክሱምን ታሪክ ዳሷል፡፡ የገብሩ የታሪክ እይታ እንደ ትግራዊ ሆኖ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ታሪክን የሚጽፍ ሰዉ የኢትዮጵያዊነት ስሜቱ ስለሚያስቸግረዉ ለሀገሩ ማዳላቱ አይቀርም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ገብሩ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲጽፍ ገለልተኛ ለመምሰል (ለመሆን!) ቢሞክርም የትግራዊነት ስሜቱ ስላስቸገረዉ ከአድሎ ሊነጻ አልቻለም፡፡ ይህ በእርግጥ እንኳን በህወሓት እውነታ አልፎ ይቅርና ‹ሲቪል› የሚባል አይነት ሰዉ እንኳ ቢሆን ሊያስቸገር ይችል ይሆናል፡፡ ይህን ተገንዝበን የገብሩን ጽሁፍ ስንመለከት
ገብሩ የአክሱምን ሀያልነት ከነገረን በኋላ ትግራዊ ካልሆኑት የዛግዌ ነገስታት ጋር እንዲህ በማለት ያነጻጽራቸዋል፡፡ ‹ይሁን እንጅ የዛግዌ ነገሥታት በዉጭ ንግድና ግንኙነት ረገድ እንደቀደመዉ የአክሱም ስርወ መንግስት አይታወቁም (ገጽ 7)›፡፡
ከዚህ ላይ ገብሩ ይህን ያለበት ምክንያት ግልጽ ሳያደርግ በደፈናዉ አልፎታል፡፡ አዉሮፓዉያን በመስቀል ጦርነት ተወጥረዉ እያለ ‹ቀሲሱ ዮሀንስ› የሚባል ምናባዊ ሰዉ ፈልገዉ ‹የኢትዮጵያን መንግስት› እርዳታ መሻታቸዉ በእስልምና እና በክርስቲያን መንግስታት መካከል የኢትዮጵያ መንግስት ገለልተኛ ሆኖ እንዲቆይ ውትወታ የተደረገበት ጊዜ መሆኑን ገብሩ ጠፍቶት አይመስለኝም፡፡ ዛሬ አሜሪካ እንደምትፈራዉ ሁሉ ያኔም የምዕራባዉያንና የመካከለኛው ምስራቅ ከባድ ጦርነት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ‹ሀያሉ› የኢትዮጵያ መንግስት ቢገባ የሀይል ሚዛኑ ወዴት እንደሚሄድ የተረዱት ሁሉ የኢትዮጵያን መንግስት በእጅ መንሻ ደልለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ያለ መሬትን በባለቤትነት የተረከበችሁ በዚያን ጊዜ መሆኑ በውጭ ግንኙነት በኩል ከመቼዉም ጊዜ በላይ ልቀን የነበረበት ዘመን እንደሆነ ገብሩ ቢረዳዉ መልካም ነዉ፡፡ (The Sign and the Seal: Graham Hancock)
ገብሩ የኢትዮጵያን ታሪክ ከመቶ አመት ከፍ አድርጎ ከሶስት ሽህም ዝቅ አድርጎ የዛሬ 1730 አመት በአማሮች የተፈጠረ መሆኑን ‹‹… በ1270 ዓ.ም. አማርኛ ተናጋሪ በሆኑት አጼ ይኩኖ አምላክ ከተተካ በኋላ…. አዲሶቹ ነገስታት ግዛታቸዉን ኢትዮጵያ በማለት ሰየሙ…(ገጽ 7)›› በማለት የፖል ሄንዝን መጽሀፍ ዋቢ በማድረግ ይነግረናል፡፡ በመሰረቱ አሜሪካዊዉ Paul Henze የወያኔ ቀኝ እጅ እንደነበረ ለገብሩ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ነዉ፡፡ የፖል ሄንዝ መጣጥፍ እኮ ከአዲስ ራዕይ መጽሄት ብዙም የተለዩ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ የሚለዉን ስያሜ ቢያንስ ከአክሱማዊዉ ሰዉ ቅዱስ ያሬድ ድርሳት ለማየት አለመሞከር ምን ሊባል ይችላል? ገብሩ በዚህ ሁለት ነገሮችን አስተላልፏል፡፡ አንድ ኢትዮጵያ የሚለዉ በምኒልክ ባይሆንም በአማራ የተሰራች መሆኗንና እድሜዋ ደግሞ የ100 እና የ3000 አመት ድምር ውጤት አማካይ አድርጎ ‹መሀለኛነቱን› ለማሳየት ይመስላል፡፡ ሌላዉ ገብሩ የኤርትራን በጣሊያን መያዝ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ከአጼ ምኒልክ ላይ ደፍድፈዉታል፡፡ ይህ እንዲያዉም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› በሚለዉ ጽሁፋቸዉ ከአጼ ምኒልክ ይልቅ አጼ ዮሀንስን ተጠያቂ ለማድረጋቸዉ የመልስ ምት ይመስላል፡፡ ይህን ማወቅ ለሚመለከት ሰዉ የገብሩንና የፕሮፌሰርን መጽሃፍት ጎን ለጎን አስቀምጦ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
በምዕራፍ ሁለት ገብሩ የህወሓትን እንቅስቃሴ የዳሰሰበት ነዉ፡፡ ምንም እንኳ አንዳንዶቹ ላይ አሁንም ጥርጣሬ ቢኖረንም ታሪካችን ይህ ነዉ ብሎ ለሚል ሰዉ ብዙሀኑን እስካልነካ ድረስ ለኔ ብዙም ግድ የለኝም፡፡ ነገር ግን አስኪ አንድ ያልተዋጠልህን ንገረን የሚል ሰዉ ስለማይጠፋ የህወሓትን የምስረታ ቀን ለምን የካቲት 11 ቀን በ11 ሰዎች ሆነ? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ (ገጽ 35) ይህ 11 በ11 የሆነ በአጋጣሚ ነዉ የሚል ሰዉ ሊኖር ይችላል፡፡ በእርግጥም እውነታዉ ያ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በፊት ምንም እንኳ የምስረታ ቀኑ የካቲት 11 ቀን መሆኑን ብዙ ሰዎች ቢናገሩም መስራቾቹ ግን 7 ናቸዉ የሚሉም አሉ፡፡ ተስፋየ ገብረ እባብ (ገ/አብ!) የጋዜጠኛዉ ማስታዎሻ ላይ እንዲያዉም ኢህዲን (ብአዴን) ህዳር 11 ቀን ምስረታው የሆነዉ ታዘዉ እንደሆነ አስነብቦናል፡፡ የህወሓት 11 ቁጥር ከምስረታ እለት ጀምሮ እሰከ ድህረ ትግል ኢኮኖሚ ደረስ ለምን እንደሆነች ገብሩ ቢያስረግጥልን ጥሩ ነበር፡፡ እውነታዉ እንኳ ይህ ቢሆን የሚባለዉን ነገር ገብሩ አይጠፋዉምና ‹አንዳንዶች 11 ቁጥር ሆን ብለን እንደመረጥነዉ ጽፈዋል፡፡ ከአብዛኛዉ ሰሜነኛ ሰው ግምባር ላይ እና ቅንድብ ላይ በምላጭ የመተልተል (የመሸንተር) ባህል ጋር አያይዘዉ የስነ ልቦና ውጊያ ቢያደርጉትም እውነታ…› በማለት ገበሩ ቢነግረን የበለጠ እናምነዉ ነበር፡፡ ለማንኛውም ይህ ብዙ አያስጨንቀንም፡፡
ገብሩ በጅምላ የሚወቀስባቸዉን ሀቆች አንድ በአንድ ዘሏቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ድጋፍ መስጠት አለመስጠታዉ ለገብሩ ጠፍቶት አይመስለኝም፡፡ እንዲያዉም ‹ፍትሃዊ ጦርነት ነዉ!› ብለዉ የአቋም መግለጫ እንዳወጡ ቃሊቲ ያለዉ አንዷለም አራጌ ‹በያልተኬደበት መንገድ› ነግሮናል፡፡ ህወሓት ሌላ ሀገር ናት ብሎ ለሚያስባት ኤርትራ በግልጽ ከተከራከረ ስለምን የኢትዮጵያ ክፍል አካል ስለሆነዉ ‹ኦጋዴን› መወያየት አልቻለም? ብለን ብንጠይቅ መልሳችን ብዙም ዉሃ አይቋጥርም፡፡ ገብሩ ግን በመጽኀፉ ገጽ 73 ላይ ‹ ስብሃት ነጋ ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ስትሰነዝር ከደርግ ጋር በመሆን ጥቃቱን ለመመከት ሀሳብ አቅርበን ነበር ቢልም በድርጅቱ ታቅፎ የነበረዉ አባል ሁሉ ይህን አያስታውስም›› ይላል፡፡ እንዴት ገብሩን ያክል መስራችና የአመራር አባል ሶማሊያ ላይ የያዙትን አቋም በግልጽ መናገር አልቻለም? እኔ የሚመስለኝ ግን የሶማሊያን ወረራ ፍትሃዊነት ከደገፉት ሰዎች ግምባር ቀደም ከሆነ ለገብሩ በዚህ መልኩ ማለፉ ያዋጣዋል፡፡ እንዲህ ብለህ ነበር እኮ የሚለው ሰዉ ከተገኘ ‹አዎ አስታውሻለሁ!› ብሎ ንስሃ ለመቀበልም ለመካድም መካከለኛ መሆን ይጠቅማል ባይ ነኝ፡፡
ገብሩ አስራት የኢህዲንን /ብአዴንን ምስረታ በተመለከተ የጻፈው ልብ ብሎ ላስታዋለዉ ሰዉ ትዝብት ውስጥ ይጨምረዋል፡፡ ኢህዲን/ ብአዴንን ተልኮ አስይዞ የፈበረከዉ ራሱ ገብሩ መሆኑን መካዱ ብቻም ሳይሆን በገለልተኛነት በራሳቸዉ ውሳኔ እንዳቋቋሙት ይነግረናል፡፡ በርግጥ በዚያ ሰዓት የሰራዉን ወንጀል ቢናገር በሰው መግደል (በዘር ማጥፋት ሊሆን ይችላል!) ወንጀነኛ ሊባል ይችላል፡፡ ከዚህ ላይ ገብሩን አንድ ጥያቄ መጠየቅ ፈለግኩ፡፡ በመጽሀፍህ በገጽ 108 ላይ ኢህዲኖች የኤርትራን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነዉ፣ የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚሉትን የህወሓት ምሰሶዎች በፕሮገራማቸዉ ላይ እንዳሰፈሩ ነገረህናል! ነገር ግን እነዚህን ነገሮች የኢህአፓ ምርኮኞች በራሳቸዉ ጊዜ ነዉ የፈጠሯቸዉ እንጅ እኛ አላስገደድናቸዉም ትላለህ? የንስሃ ከፊል ስለሌለዉ ሙሉዉን ብትናዘዝ መለካም ነበር፡፡
የህወሓት ታጋይ የነበረና በአላማ ልዩነት በአዉስትራሊያ በስደት የሚገኘዉ ገ/መድን አርአያ ግን እውነታውን ‹ብአዴን ማነዉ?› በሚለዉ ጽሁፉ በደንብ አብራርቶታል፡፡ ገብሩን ጨምሮ የገብሩ አንጃ የነበረዉ አውሎም ወልዱ አብሮ ከነመለስ ዜናዊ፣ ስብሀት ነጋና አርከበ እቁባይ ጋር ሆነው የመመስረቻዉን የመወያያ ነጥብ አውጥቷል፡፡ አርያ ገ/መድን ምርኮኞቹ የህወሓትን ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹የአማራ ህዝብ የሌላው ኢትዮጵያ ጠላት ነዉ ለምትሉት እኛም አማራ ነን፤ ኩሩዉን አማራ ህዝብ በጠላትነት አትፈርጁት›› ብለው በእህና በንዴት የተናገሩም ነበሩ ይለናል፡፡ በዚህ ጊዜ ምርኮኞቹ በሶስት ተከፈሉ፡፡ አድር ባዮቹ ሀሳቡን የተቀበሉ፣ እንስብበት ብለዉ ጠፍተው ያመለጡና ከላይ የተባለዉን የተናገሩ፡፡ አንቀበለዉም ያሉትን ሰዎች ‹ስብሀት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ አርከበ እቁባይ፣ ስየ አብርሃ፣ አውሎም ወልዱ፣ ጻድቃን ገ/ትንሳይና ስዩም መስፍን በ06 በጅምላ እንዲሞቱ ፈረዱባቸዉና ወዲያውም ተፈጻሚ ሆነ ይለናል ገ/መድን አርአያ፡፡ (ብአዴን ማን ነዉ?)
ስለዚህ በገ/መድን ጽሁፍ መሰረት ገብሩ አስራት ይህን ቢናዘዝ የእረሱ ብቻም ሳይሆን የጓደኞቹን የስየን፣ የጻድቃንና የአውሎምን ይሁንታ ማገኘት ይኖርበት ይሆናል፡፡ ግን በአንድ እጅ ንጹህ ውሃን በሌላ እጁ ደምን ይዞ መጓዝ የሚቻል ስላልሆነ የገበሩ ንጹህ ውሃ በደም የጠቆረ ያደርገዋል፡፡
ገብሩን ሌላም ትዝብት ውስጥ የሚያስገባዉ ነገር ብዙ አለ፡፡ ከነጻነት በኋላ የድንበር አከላሉን በተመለከተ ዝም ማለትን መርጧል፡፡ ትግራይ የቀድሞ ስፋቷ 66 ሺ ስኩየር ኪሎ ሜትር ባይበልጥም በአዲሱ ግን ከጎንደርና ከወሎ ከፊል ግዛቶች ሂደዉ 100 ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት እንዲኖራት የተደረገበትን ስሌት ሾላ በድፍን ማለት አግባብ አልነበረም፡፡ ይህም ይሁን ብለን ብናልፈው እንኳ የገብሩ ውስጥ እምነት እንደሆነ ከመጽሃፉ ውስጥ የተለያየ ቦታ ላይ ካሉ አረፍተ ነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ወደ ኋላ ተመልሰን ገጽ 74 ላይ ደርግን ለመመከት የተዘጋቸዉን የህወሓትን ጦር ለመግለጽ ሑመራን የትግራይ ክልል እንደሆነና 5ኛውም የህወሓት ሀይል በዚያ እንደተሰለፈ ጽፏል፡፡ አሁን የህወሓት አራማጅ እንደሆነ የተገነዘብኩት ደግሞ በ1992 ክፍፍል ወቅት አዲሱ ‹ግጨዉን› በትግራይ ክልል እንዲሆን አድርገሓል ብሎ ከሰሰሰኝ ማለቱ ነዉ (ገጽ 273) ፡፡ ገጨው ማለት አሁን በምዕራብ አርማጭሆ ግዛት ያለና የህወሓት ተስፋፊዎች አሁን ላይ የእኛ ነዉ እያሉ ሁልጊዜ ግጭት የሚነሳበትን ቦታ ነዉ፡፡ ይህ ቦታ በዘንድሮ ክረምት በተነሳ ጠብ ለበርካታ ሰዎች ህይወትም ህልፈት ምክንያት የሆነ ቦታ ነዉ፡፡
ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት /GTZ/ በተገኘ ድጋፍ 22000 (ሀያ ሁለት ሺህ) የህወሓት ቀድሞ ወታደሮች በዳንሻ ሲሰፍሩ በአካባቢዉ ነባር ህዝቦች ላይ ምን እንደደረሰ አልነገረንም፡፡ ሰፈራው በዚህ አካባቢም የተደረገው የህዝቡን የጎሳ ብዛት ለመቀየር (ፖፕሌሽብ ዳይናሚክስ ለማፋለስ) የተሰራ ስራ መሆኑን ለገብሩ ብነግረው አውቆ የተኛን ሰው ለመቀስቀስ መጣር ነው፡፡ ከ1972 ጀምሮ በህወሓት ቤት እየተዘጋባቸዉ በእሳት ያለቁ ወልቃይቴዎችና ጠገዴወች አልነበሩም ገበሩ? (ገ/መድን አርአያ)፡፡
ወገንተኛነትን በተመለከተ ደግሞ የስየንና የታምራት ላይኔን ማየት በቂ ይሆናል፡፡ ለኔ ታምራትም ስየም ልዩነት የላቸዉም፡፡ ሁለቱም ሙስና ወንጀል ታስረዋል -ምንም እንኳ ከህወሓት ባለስልጣን ሙስና ያልነካዉን ሰዉ ማወቅ ከባድ ቢሆንም፡፡ ገብሩ ግን የታምራትን ትክክለኛ ሙሰኛነት አጋልጦ ስየን ነጻ አውጥቶታል (ገጽ 306) ፡፡ ታምራት ከሸኩ 8 ሚሊዮን ዶላር ተቀብሎ ስዊስ ባንክ አስቀምጧል በማለት፡፡ (ገጽ 195)
ገብሩ የትግራይ ክልል ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ መልኩ አልተጠቀመችም ብሎ የሚከራከርበትም አስተዛዛቢ ነዉ፡፡ የኢፈርት ኩባንያዎች ለባለስልጣናቱ እንጅ ምንም ለህዝቡ የፈየዱት የለም ይላል (ገጽ 350)፡፡ ከዚህ ላይ ሁለት ነገሮችም ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛው ባለስልጣናት እንደፈለጉ ያደርጓቸዉ ነበር ማለት የኤፈርት ስራ አስኪያጅ የነበረው ስየ አብርሃ በትክክልም ሙሰኛ እንደነበር ገበሩ ሳያውቅ ከዚህ ላይ መሰከረ ማለት ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ነገር ደግሞ ቢያንስ እነኚህ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ለአካባቢው ሰዉ የስራ እድል መፍጠራቸዉ ጥቅም አይደለም ወይ? የሚሉ ይሆናሉ፡፡
የገብሩ ጨዋታ ይቀጥላል፡፡ ‹‹ ሆኖም እነዚህ ኩባንያዎች ባይኖሩ ኖሮ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀበትና የሰው ሀይል ለመጠቀም የሚሹ ኩባንያዎች በአካባቢው መተከላቸዉ አይቀርም ነበር፡፡ ታዲያ ትእምንት ባይኖርስ ይህን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም የሚፈልጉ ኩባንያዎች መተከል የትግራይን ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ ያደርገዋል ማለት ነዉ?› ሲል ይሞግታል (ገጽ 350)፡፡ ገብሩ አስራት ሆይ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሰው ሀይል የለም? የተፈጥሮ ሀብት የለም? ነዉ መለስ እንዳለው ‹ከወርቃማው› አካባቢ መምጣትህን ልትነግረን ፈልገህ ነዉ?
ገብሩ አያይዞም ‹እዚህ ላይ መታወስ ያለበት ኢህአዴግ ጨቋኝ ፓርቲ ቢሆንም ትግራይን ብቻ የሚወክል እንዳልሆነና ከኢትዮጵያ የተፈጠረ እንደሆነ ነዉ›› ሲል ያሳስባል፡፡ ይህ እውነትም ውሸትም ነዉ፡፡ አዎ ኢህአዴጋዉያን ኢትዮጵያውያን እስከ ሆኑ ድረስ ከኢትዮጵያ አብራክ የወጡ ፈላጭ ቆራጮች ናቸዉ፡፡ ሌላዉን ልተወው፡፡
በአጠቃላይ የገብሩ አስራትን መጽሀፍ እንዲህ ስገመግም ጥሩ ጽፏል እያሉ ሲያሞግሱ የነበሩ የገብሩ ጀሌዎች መንጫጫታቸዉ አይቀርም፡፡ ሆኖም ከመንጋው ጋር አንድ ለመሆን በሚል ስሌት እውነታን መሸፋፈን ባህሌም እምነቴም አይፈቅድም፡፡
ሰላም
መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
Leave a Reply
You must be logged in to post a comment.