የወልቃይት ሰቆቃ:- በፕሮፌሰር አስራት የትንቢት ቃል

የወልቃይት ሰቆቃ:- በፕሮፌሰር አስራት የትንቢት ቃል  

ሸንቁጥ አየለ  

 

አስራት ወልደዬስ ፖለቲካ አይወደም:: ፖለቲካ ዉስጥ ግባ ስልጣን ይሰጥህ ተብሎ በንጉሱም በደርግም ቢለመን ፖለቲካን እና ስልጣንን ሸሽቶ የሚኖር የተከበረ ሞያ ያለዉ ሰዉ ነበር::

አስራትን ሊታመን በማይችል መልክ ከራሱ ወንድሞች የዘር ማጥፋት የታወጀበት የአማራ ህዝብ እልቂት ጉዳይ ግን አይኑን ጨፍኖ ወደ ማያዉቀዉ ፖለቲካ ዉስጥ ገብቶ እንዲመሰግ አድርጎታል::

ህይወት አንዳንዴ እንዲሁ ነዉ:: ወደ ሆነ ወደ ማትወደዉ አስበህዉ ወደ ማታዉቀዉ እጅግ እሩቅ ወደ ሚመስልህ ዉቃያኖስ ዉስጥ ወስዶ ይመስግሃል::  ግን ለምንድን ነዉ የአማራ ህዝብ በራሱ ኢትዮጵያዊ ወንድሞች እንዲህ አይነት የዘር ማጥፋት የታወጀበት? ይሄ ጽሁፍ እዚህ ጉዳይ ዉስጥ አይገባም::

የሆኖ ሆኖ እያለቀ ያለዉን አማራ ማዳን የሚቻል የመሰለዉ አስራት ለአማራዉ ህዝብ ጥሪ ቢያቀርብ የአማራ ምሁራን እና ሀብታሞች እሶስት ቦታ ተከፍለዉ ማቄጣቸዉን እና ማሾፋቸዉን ሲያስተዉል በጣም ተግርሟል:: አስራትን ሊያግዙት የቻሉት እጅግ ጥቂት ወገኖች ቢሆኑበት በጣም የከነከነዉ አስራት በደብረብርሃን ስብሰባ ላይ የሚገርም ንግግር ለማድረጉ ምክንያት ሆኖታል::

አስራት የተግባር ሰዉ እንጅ የወሬ ሰዉ አይደለም:: ፍጹም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን የመድሃኒአለም ወዳጅ ነዉና ምንም ሳያጠፉ ለተገፉት ወገኖቹ ሲል እራሱን መስዋዕት ለማድረግ ዙሪያ ጥምጥም የሚሄድ ሰዉ አልነበረም::ቀጥ ያለ ሰዉ ነዉ:: አማራ መሆኑ : ኢትዮጵያዊ መሆኑ : ክርስቲያን መሆኑ አስራትን አይገልጸዉም::

ፍጹም ሰዉ እና እዉነት ወዳድ ሰዉ መሆኑ ብቻ አስራትን ይገልጸዋል::እናም በወገኖቹ የእልቂት እና የመክራ ሰዓት ሰበብ ጽንሰ ሀሳብና እና ብዙ ወሬ አላበዛም:: አንዳንዶች አማራ ማን ነዉ? ለምን በአማራ ስም ድርጅት ይቋቋማል? የፖለቲካ ፓርቲዉ ርዕዮተ አለም ምንድነዉ ወዘተ የሚሉ አስራት በህይውቱ ሙሉ አስቧቸዉ የማያዉቁትን ጥያቄዎች ያንቆረቁሩለታል:: አስራት ይገረማል:: አንዳንዴም በሆዱ እኔ ይሄን ሁሉ መቼ ሳስብበት ኖርኩ ሳይልም አይቀር::

ምንም በማያዉቀዉ የአማራ ህዝብ እልቂት ላይ እሶስት ቦታ ተከፍለዉ የሚያቄጡትና የሚያፌዙት የአማራ ሀብታሞችና ምሁራን ግን ማቄጣቸዉን ቀጥለዉ ነበር:: አንድኛዉ ወገን “አስራት የጎሳ ድርጅት ማቋቋም አልነበረበትም” ይላል:: አስራት ሳይታክት ይመልሳል::”ያቀረብነዉ የመጀመሪያ የድርጅት ስም “አንዲት ኢትዮጵያ” የሚል ነበር:: ወያኔ አሁን ማቋቋም የተፈቀደዉ የብሄር ድርጅት እንጅ የሀገራዊ ድርጀት አይደለም ብላን ነዉ::ወደፊት ሊፈቀድ ይችላል:: አሁን ግን እናንተ አማሮች ስትሆኑ በኢትዮጵያዊነት ስም ድርጅታችሁን ልትቋቁሙ አትችሉም ብለዉ ከልክለዉን ነዉ:: ደግሞም እያለቀ ያለዉ ህዝብ አማራ እስከሆነ ድረስ እራሱን የሚከላከልበት ድርጅት ያስፈልገዋል:: ስለዚህ መላዉ አማራ መቋቋሙ መልካም ነዉ::” አስራት ይመልሳል::

የሚያላግጡት የአማራ ሀብታሞችና ምሁራን ግን ማላገጣቸዉን ይቀጥላሉ:: ቢሆንም ይላሉ::ቢሆንም ቢሆንም…::ግን ቢሆንም ብለዉ ቀጥሎ የሚናገሩት ሀሳብ የላቸዉም:: ግን ማልጎምጎማቸዉን ይቀጥላሉ:: ደግሞም ዝም አይሉም:: ሻዕቢያዎች እንዲህ አይነቶቹን ይመስላል አህያ የሚሏችዉ:: ክብርና ኩራት የላቸዉም:: መርህና እዉነት የላቸዉም:: ግን ይናገራሉ:: ዝም አይሉም::

ሁለተኛዉ የሀብታምና የምሁር ቡድን ደግሞ ሌላ ሀሳብ ይዞ ይመጣል:: “መፍትሄዉ ጦርነት ነበር:: አስራት ግን ዝም ብሎ ሰላማዊ ፓርቲ ብሎ ይሄው ከወያኔ ጋር ይጋፋል:: ህዝቡን ለማስጨረስ ነዉ” ይላሉ:: አስራት ይመልሳል:: “ጦርነት የሚደረግበት የታመነ መሬት ያስፈልጋል:: የታመነ የጎረቤት ሀገር ያስፈልጋል:: የመነሻ ሀብት ያስፈልጋል:: ዝም ተብሎ ጦርነት እያሉ እስክስታ አይመታም::” እያለ አስራት ያስረዳል:: እናም ይቀጥላል:: እዲህ ሲል:: “እስኪ አሁን ለምናደርገዉ ትግል የሚሆን ድጋፍ አድርጉ:: እንደራጅ:: ወያኔን አማራን አታፈናቅል: አትግደል: በአማራ ላይ ያወጅህዉን የዘር ማጥፋት አቁም እንበለዉ” ብሎ ይጠይቃቸዋል::

እነዚህኞቹም እንደላይኞቹ ለመርዳት ሳይሆን ለማዉራት እና ለመተቸት ፈጣን ናቸዉ:: የአስራትን መልስ ሰምተዉ ሲያበቁ አንድም እርዳታ ሳያደርጉ “ቢሆንም ቢሆንም ቢሆንም..” እያሉ ያልጎመጉማሉ:: የሚፈልጉት በሌላዉ መስዋዕትነት የእነሱ ሀሳብ እንዲተገበርላቸዉ ነዉ:: ያለዉን ዉስብስብ ነገር አንድም አያዉቁትም:: እነዚህ ሰዎች አልጋቸዉ ላይ ተጋድመዉ ስላለዉ ዉስብስብ የፖለቲካ ሂደት አንድም ነገር ሳያዉቁ አፋቸዉን አላቀዉ ሲያወሩ አያፍሩም::

ሶስተኞቹ አቂጥና አላጋጭ ቡድኖች ብቻ አይደሉም:: ሻጭና ሸቃይ ጭምር እንጅ::አስራት እና ህዝብ በሚገኙበት መድረክ ላይ አካኪ ዘራፍ ሲሉ ይናገራሉ:: ሆኖም ዞረዉ እያንዳንዱን መረጃና እንቅስቃሴ ለወያኔ ይሸጡታል:: እነዚህ ሰዎች አይደሉም:: ከሰዉ በታች ናቸዉ እንጅ:: ከሰዉ በታች ቢሆኑም ግን ሰዉን ከሰዉ በታች ለማድረግ ትክክለኞቹ የጠላት መሳሪያዎች ናቸዉ:: እነዚህ ቡድኖች መልካቸዉ ብዙ ነዉ:: ሀይማኖተኛ ናቸዉ: ምሁራን ናቸዉ:ሀብታም ናቸዉ : አርሶ አደር ናቸዉ:: ሁሉም ግን መለያቸዉ አንድ ነዉ ሆዳም ናቸዉ:: ፕሮፌሰር አስራት ይሄን ሁሉ ካስተዋሉ ብኋላ የአማራዉ ሃይል እራሱን ለማዳን እንዳልፈለገ ባስተዋሉ ጊዜ የከፈሉት መስዋዕትነት ለህዝቡም እንዳልተገለጸለት በተረዱ ሰዓት “ሆዳም አማራ አስቸገረን”:: አለ::

አስራትን ወያኔ ፈርታዋለች:: እንደ አስራት አይነት ሰዉ አስረዉ ካላስቀመጡት ብሎም በእስር ሰበብ ካልገደሉት እረፍት እንደማይሰጣቸዉ ወያኔዎች በደንብ ተረድተዋል::

ይሄንንም ገና ከጅምሩ አስተዉለዋል:: ምድረ ሆዳም ምሁርን እና ሀብታምን ወያኔ ሰብስባ ኤርትራን ለማስገንጠል ኢሳያስ አፈወሪቂና መለስ ዜናዊ እጅ ለእጅ እየተጨባበጡ ጀርባ ለጀርባ እየተሻሹ ሲዶሉቱ አንድ እዉነተኛ ኢትዮጵያዊ ሰዉ የተገኘዉና በኮንፈረንሱ ላይ የተደረገዉን ሂደት የተቃወመ አስራት ነበር:: አስራት ያኔም እግር ጥሎት እንጅ ፖለቲካ ፈልጎ አልነበረም ኮንፈረንሳቸዉ ላይ የተገኘዉ:: የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተወካይ እንደመሆኑ ዩኒቨርስቲዉን ወክሎ በተገኘበት ወቅት ነበር ኢትዮጵያ ትገንጠል እያሉ መለስና ኢሳያስ ሲዶልቱ “የኢትዮጵያን ህዝብ ሳታማክሩ ምን አግብቷችሁ ነዉ ኤርትራን የምታስገነጥሉት:: ይሄ ሂደት ስህተት ነዉ:: ብኋላ መዘዙ ብዙ ነዉ” ሲል ብቻዉን የተቃወመው:: የዚያ ሰዓት ነዉ ኢሳያስና መለስ ይሄን ኩሩ ሰዉ ሰበብ ፈልገዉ ለመግደል የወሰኑት::

አስራት አማራ ላይ የተቃጣዉን የዘር ማጥፋት እቀለብሳለሁ ብሎ ደፋ ቀና ሲል በደብረብርሃን ስብሰባዉ ላይ እንዲህ የሚል አስገራሚ ትንቢታዊ ንግግር ተናገረ:: “ዛሬ የአዳንድ አካባቢ አማራ ሊጠቃ ይችላል::ነገ ግን በሁሉም አካባቢ ይቀጥላል:: የአማራ ምሁራን እና አቅም ያላቸዉ ሰዎች ግን ገና ሆዳቸዉን ከማሰብ አልወጡም:: ሆዳም አማሮች አስቸግረዉናል:: ሆዳም አማራ እያለ እንዴት አድርገን ህዝቡን መታደግ እንችላለን? አንዱ ወደዚህ ይስባል:: ሌላዉ ወደጎን ይጎትታልል: ግማሹ ቆሞ ያልጎመጉማል:: ሌላዉ ደግሞ ሆዱን በወንድሞቹ ደም እና ጥፋት ላይ ቆሞ ይሞላል::”

የአስራት ትንቢት ቀጥሏል:: ትናት ከመላ ሀገሪቱ ይባረር የነበረዉ አማራ ግፍ ሳያበቃ ፍትህ ሳያገኝ አንድ የሚሰፍርበት ቦታ ሳይሰጠዉ ዛሬ ደግሞ ወልቃይት እያነባ ነዉ:: የወልቃይትን ነገር ሳስበዉ የአስራት ንግግር ይታሰበኛል:: እንዲህ የሚለዉ ::”… ሆዳም አማራ እያለ እንዴት አድርገን ህዝቡን መታደግ እንችላለን? አንዱ ወደዚህ ይስባል:: ሌላዉ ወደጎን ይጎትታል:: ግማሹ ቆሞ ያልጎመጉማል::አንዳንዱም የማይጨበጥ ሀሳብ እያመጣ ትግሉን ከማገዝ ይልቅ ትግሉን ያደናቅፋል::ብዙሃኑ ደግሞ ህዝቡን የማዳን ስራ የኛ የግል የቤት ስራችን ይመስለዋል መሰለኝ በሜዳ ሲያገኘን በርቱ እንግዲህ ብሎ ጉዳዉን ሁሉ ወደኛ ገፍቶት በገንዘብም በሀሳብም : በተሳትፎም ሳያግዘን ወደ ግል ጉዳዉ ይሮጣል:: ሌላዉ ደግሞ ሆዱን በወንድሞቹ ደም እና ጥፋት ላይ ቆሞ ይሞላል::”

እዉነት ነዉ:: የሆነውም አሁን እየሆነ ያለዉም ይሄዉ ነዉ:: ወልቃት ላይ እየደረሰ ያለዉን ችግር ባንድ ጊዜ ቀጥ ማድረግ ይቻል ነበር:: ግን ነበር ሆኖ ቀረ:: ለምን? አስራት እንዳለዉ አንዱ ወደዚህ ይስባል:: ሌላዉ ወደጎን ይጎትታል:: ግማሹ ቆሞ ያልጎመጉማል::አንዳንዱም የማይጨበጥ ሀሳብ እያመጣ ትግሉን ከማገዝ ይልቅ ትግሉን ያደናቅፋል::ብዙሃኑ ደግሞ ህዝቡን የማዳን ስራ የተወሰነ ሰዉ የግል የቤት ስራ ያደርገዉና በርቱ እንግዲህ ብሎ ጉዳዉን ሁሉ ወደ ሆኑ ሰዎች ገፍትሮ በገንዘብም በሀሳብም : በተሳትፎም ሳያግዝ ወደ ግል ጉዳዉ ይሮጣል:: ሌላዉ ደግሞ ሆዱን በወንድሞቹ ደም እና ጥፋት ላይ ቆሞ ይሞላል:: ይባስ ብሎ አንዳንዱ እንዲህ ቢያደርጉት እንደዚያ ቢፈጥሩት ብሎ ሳያፍርና ስያይቀፈዉ ባፉ ሙሉ እየተቸ ይናገራል::

ዲሞክራሲ ሰላም ብልጽግና መከበርና አጠቃላይ ማህበራዉ ብልጽግና ያለብዙሃኑ ተሳትፎ ይመጣል ብሎ ማሰብ ተረት ተረት ነዉ:: በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በምዕራባውያንም በምስራቃዉያንም እንዲሁም በሁሉም አቅጣጫ ለራሳቸዉ የግል ጥቅም ብቻ ቀስፈዉ በያዙዋት ሀገራት ጥርስ ዉስጥ የገባ ሀገር ህዝቡ እራሱን ማዳን ካልቻለ ዙሪያ ገባዉ ገደል ነዉ::

እናም ለወልቃይት ጩህት በቂ መልስ መስጠት ያልተቻለዉ ለዚህ ነዉ:: በወልቃይት ላይ ግን ግፉ አይቆምም:: ነገሩ ይቀጥላል:: ሌሎች አካባቢዎች ትናንት ሲያለቅሱ ነበር:: ዛሬ ወልቃይት:: ነገ ደግሞ ሌሎቹ አካባቢዎች:: ለምን? ከላይ እንደተባለዉ ነዉ::

Archives

Copyright and Disclaimer

Copyright © 2010 - 2015 Kefale Alemu

Copyright © [2010]. KAlemu, All Rights Reserved.